
እነኚህ ከታች በምስሉ የሚታዩት በትናንትናው ዕለት ወደ ጎረቤት ሀገራቸው ዩጋንዳ አቅንተው ፕሬዝዳንት ዮሄረ ሙሰቬኒ እያስጎበኙ የሚገኙት የጎረቤታችን ኬኒያ ፖለቲከኞች ናቸው። አንዱ የወቅቱ የሀገሪቱ ፕረዚዳንት ዶክተር William Samoei Ruto ሲሆን ለሌላኛው ታዋቂ የሳቸው መንግስት ተቀናቃኝ Raila Odinga ናቸው። ሁለቱም ከተለያዩ ብሄር የተገኙ ናቸው። በሀገራቸው ክብርና ጥቅም ላይ ምንም ልየነት የላቸውም። በኢትዮጵያ ቢሆን በፓለቲካ አመለካከታቸውና ልዩነታቸው አብረው እንዲህ መቆም ይቅርና በደም የሚፈለጉ አቋም ያላቸው ናቸው። የሁለቱን ታዋቂ ፓለቲካኞች ምሳሌ በምክንያት ለማንሳት ወድጄዋለሁ።



በኬኒያ ውስጥ በፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ወደ ጦርነት መግባት የለም። በፓለቲካ አስተሳሰብ ምክንያት መታሰር መሰደድ በጭራሽ አይታሰብም። ዜጎች እንደፈለጉት መንግስትን በአደባባይ ሆነ በየትኛውም መንገድ የመተቸት ዕድል አላቸው። እንዲያውም አምና በታሪክ አጋጣሚ እኔ በሚዲያ ስራ ምክንያት እስራትና እንግልት ስለገጠመኝ ከእነ ቤተሰቤ ኬኒያ በስደት በመጣሁበት ወቅት በሀገሪቱ ታላቅ ህዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ሲካሄድ በአይኔ አይቼዋለሁ።
የተቃዋሚ ፓለቲካ ፓርቲዎች አሁን ላይ ሀገሪቱን እየመራ የሚገኝ መንግስት “ለህዝቡ በገባው ቃል መሠረት እየሰራ አይደለም” በሚል ህዝባዊ ሰልፍ ለማድረግ ጥሪ ያደርጋሉ። ጥሪ ማድረግ ብቻ ሳይሆን ህዝባዊ ሰልፍ በሀገሪቱ ሰፊ ሽፋን ባላቸው ቴለቪዥን እና ሬዲዮ ያለማንም ጠልቃ ገብነት ቀጥታ ስርጭት እየተላለፈ ይካሄዳል። ለሰልፉ የወጡ ዜጎች ሀሳባቸውን ያለማንም ከልካይ በተለያዩ መንገዶች ይገልፃሉ። ይሄንን ለምን ተናገርክ ተብሎ እስርና እንግልት የለም። ለምን መንግስት ከሚፈልገው ውጪ ተብሎ ሚዲያዎች አይዘጉም ጋዜጠኞች አይታሰሩም። ይልቁንስ መንግስት ራሱን ወደ አደባባይ ሰልፍ በመውጣት የሚተቹ ዜጎቹን ቤታቸው እስኪመለሱ ድረስ በቂ ጥበቃ ያደርጋል።
ወደ ሰልፉ የሚወጡ ዜጎችም የእከሌ ብሄር እንደዚህ አደረገ ሳይሆን ስራቸውን ለይቶ ይተቻሉ ይቃወማሉ። ከ70 በላይ የተለያዩ ብሄሮች ባሉባት ኬኒያ የብሄር ጥላቻ ሆነ ግጭት አይታሰብም። የተሻለ ሀሳብ ያለው ይደመጣል። ከተሸነፈም በሀሳብ የበላይነት እንጂ የበላይነት የለም። ፓለቲከኞች ለህዝብ ይጠቅማል የሚለውን ሀሳብ ፊትለፊት ይጋፈጣሉ እንጂ እርስበርስ ይከባበራሉ።
ሰሞኑን የቀጣይ ለአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበርነት ለመወዳደር እየተዘጋጁ የሚገኙ የኬኒያ ታዋቂ የመንግስት ተቀዋሚ ራይላ ኦድንጋ እንዲያሸንፉ በሀገሪቱ ሚዲያዎችና በመንግሥት ደረጃ በርካታ የድጋፍ ቅስቀሳ ስራዎች እየተሰሩ ነው።
ኬኒያ ሰላማዊና የሀሳብ የበላይነትን ተቀብላ የተለያዩ ምስራቅ አፍሪካ ላይ በኢትዮጵያ ጉዳይ ጭምር የሚሰሩ አለምአቀፍ ሚዲያዎች፣ የተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማትና ስደተኞች ምንም ስጋት ሳይሰማ የሚኖሩባት የነፃነት ምድር ናት። ሀገሬ ኢትዮጵያ ይሄንን ፀጋ መቼ ታመጣ ይሁን ብዬ ሁለ እመኛለሁ።
ኬኒያ ውስጥ አንድ የመጀመሪያ ድግሪ ምሩቅ መነሻ ደመወዝ በትንሹ እስከ 50 ሺህ ሽልንግ ወይንም በኢትዮጵያ እስከ 40 ቪህ ብር የሚጠጋ ማለት ነው። አብዛኛዎቹ ኬኒያዊያን ለተሻለ ትምህርት ወይንም ስራ ወደ አውሮፓ ወይንም አሜሪካ ቢሆዱ እንጂ ወደ ስደት አይሄዱም። ኬኒያ በአፍሪካ ምንም አይነት ጦርነት የማይካሄድባት፣ የተረጋጋ ኢኮኖሚ ያላት፣ በሀገሪቱ በሁሉም አከባቢዎች በፍትሀዊነት የተሻለ መሠረት ልማት የገነባች፣ ከ70 በላይ ብሄርና 68 ቋንቋ እያላት የብሄር ጥላቻ ሆነ ግጭት የማይታሰብባት በምስራቅ አፍሪካ ብቸኛዋ ሰላማዊ ሀገር ነች። በርካታ ያልጠቀስኩት ጉዳዮች አሉ።
እናም በየቀኑ ለሀገሬ የምመኘው፦ ኢትዮጵያችን አሜሪካ ሆነ አውሮፓ ወይንም ያደጉ ሀገራት የደረሱበት ዕድገት ለመድረስ እያለች በቅዠት ከማቀዷ በፊት ይህች ጎረቤት ሀገር ኬኒያ የደረሰችበትን የፓለቲካ ልዩነትን በጦርነት ሳይሆን በጠረጴዛ ዙሪያ የመፍታት፣ ፓለቲካኞች በብሄር ኮታ ሳይሆን የተሻለ ሀሳብ ያለው ስልጣን የሚይዝበት፣ ሚዲያዎች ሆነ የተለየ ሀሳብ ያላቸው ያለምንም ገደብ ሀሳባቸውን በነፃነት የሚገልፁበት፣ በሁሉም አከባቢዎች በፍትሀዊነት የተሻለ መሠረት ልማት የገነባችበትን እንዲሁም ከየትኛውም ጎረቤት ሀገራት ጋር በፓለቲካ ምክንያት ጥላቻ ውስጥ ያልገባችበትን ምርጥ ተመክሮ ለመድረስ ቢሰራ መልካም ነው እላለው።

ሀገሬ ኢትዮጵያ ሁሉም ነገር እያላት በየወቅቱ በሀሳብና በፓለቲካ አመለካከት ልዩነት ምክንያት ብቻ በሰላማዊ ውይይት ከመፍታት ይልቅ ወደ ጦርነት ሜዳ እየገባች ለበርካታ ትውልድ የሚበቃ ልማት መስራት የሚያስችለውን ገንዘብ እያወደመችና የዜጎቹን ህይወት በከንቱ እንዲያልፍ እያደረገች የሀገሪቱ ዕድገት ከአለም ወደኃላ እንዲቀር እያደረገች ነውና ሩቅ ቦታ ሳንሄድ ከጎረቤት ኬኒያ ፓለቲካ ተምረን ወደ ሰላማችንና ዕድገታችን እንመለስ👐 #Ethiopia #kenya
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተፃፈ