በዞኑ ፓርቲው ከሚከተለው ዕሳቤና አሰራር ውጭ የተዘረጋው መዋቅር በአስቸኳይ እንዲፈርስ የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ አባላት ጠየቁ።

በዎላይታ በዛሬው ዕለት በሁሉም መዋቅሮች የተጀመረው የብልፅግና ፓርቲ አባላት ጉባኤ ከወትሮው በተለየ መንገድ የለውጥ ሀሳቦችና ከፍተኛ ቅሬታ ጥያቄዎች የተንፀባረቀበት መሆኑን ከየአካባቢው የደረሰን መረጃ አመላክቷል።

ኮንፍራንሱ “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪህ ቃል በዞኑ በሚገኙ በሁሉም ቀበሌዎች የተጀመረ ሲሆኑ አባላቱ የዎላይታ ህዝብ በሌብነትና በጥቅም ትስስር በተደራጀው የኔትወርክ ቡድን ምክንያት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት እንዲሁም በደል እየደረሰበት ስለመሆኑ በስፋት አንስተዋል።

የአመራሩ ምደባ ከብልጽግና ዕሳቤ እና አሰራር መሪህ ውጭ በአቤ-ልጅ ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም ላይ የተመሰረተ የቤተሰባዊ ኔትወርክ በመሆኑ በየአካባቢው በተደራጀ ሁኔታ በከተማ እና በገጠር መሬት ዘረፋ፣ የህዝብ ሀብት ምዝበራ፣ ቃል የተገቡ ልማት አለመጀመር፣ እ-ፍታሀዊ የስልጣን ድልደላ፣ የተጀመሩና ለመጀመር የታቀዱ የተለያዩ ልማቶች የሚበጀተውን ገንዘብ ለአመታት እያጓተቱ ያለጠያቂ ተከፋፍለው መብላት እየተለመደ የመጣ እስኪሆን መድረሱንም አባላቱ አንፀባርቀዋል።

“ዎላይታ ላይ ልጆቻቸዉ ወደ ጎዳና ሳይወጡ በተወለዱበት አካባቢ የአባትና የእናት ፍቅር እያገኙ ቢያድጉ አይጠሉም፡፡ ግን ይህ እድል የለም፡፡ ከህፃናት ጀምሮ በየጎዳናው ለስቃይና ለስደት ኑሮ ተገዷል። የሚማሩ ልጆችም ተስፋ ቆርጠዉ በየሠፈራቸዉ ከተመረቁ 5 ዓመት እና በላይ የሆናቸዉን ከመቶ ሺህ በላይ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ድግሪ ምሩቃን እና አሁንም ሥራ አጥ ሆነዉ በአከባቢው ምንም አይነት የስራ ዕድል የለም፦ ይህ ችግር ደግሞ የሚመነጨው የአከባቢውን ችግር ለመቅረፍ በመንግሥት አመራርነት የተመደቡ ግለሰቦች የራሳቸውን ጎሳና ዘመድ ብቻ ለመጥቀም እየሰሩ መሆኑ በፓርቲው ላይ እምነት እንዳንጥል እያደረገ ነው” ሲሉም አባላቱ ቅሬታ አቅርበዋል።

እንደ መረጃ ምንጮቻችን ገለፃ በኮንፈረንሱ ቀድሞው ለህዝቡም ለፓርቲውም እኩይ አላማውና ድርጊቱ ገሃድ የወጣበት የኔትወርክ ቡድኑ በተለይ የመንግስት ሰራተኛውንና ሌሎች አባላትን በአበልና በጥቅማጥቅም ዝም ለማሰኘት የተደረገ ሙከራ በርካታ ቦታዎች ላይ የከሸፈ ሲሆን አባላቱ በግልጽ ቋንቋ በዞኑ የህዝብ የልማትና የመልካም አሰተዳደር ጥያቄዎቹ በአበልጃዊና እና ጎሳዊ የስልጣን መረብ ተደፍቀው ምላሽ እንዳያገኙና ህብረተሰቡ በተጨባጭ በአይኑ እያየ ባለው አስናዋሪ ድርጊታቸው “በመንግስት ላይ እምነት ለመጣል እንኳን እየተቸገረ ነውና እውነትም የብልፅግና ፓርቲያችን ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ የሚሰጥና የራሱ ፓርቲ ስም ጭምር የሚያጎድፍ እነዚህ ቡድኖች በዘረጉት የማይመጥን የግለሰቦች ኔትወርክ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ እርምት እርምጃ እንዲወስድ” የሚል ሀሳብም በሁሉም አከባቢዎች ያለልዩነት ማለት በሚቻል ደረጃ ተንፀባርቋል።

ይሁን እንጂ በአከባቢው ባልተለመደ ሁኔታ አባላት ጠንከር ያለ ትችትና ቅሬታ በተለይም የዎላይታ አመራር ምደባ ስርዓት ብልጽግና ፓርቲ ከሚከተለው ዕሳቤና አሰራር ውጭ ዞኑ ለተለያዩ ችግሮች ስለመጋለጡ ተጨባጭ ማብራሪያ በማሰማታቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከኮንፈራንስ አዳራሽ በማውጣት ማሳር፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ማድረግ እንዲሁም በአመራሮችና ፀጥታ አካላት ተገደው ይቅርታ ጠይቀው ከእንደገና ለተሰበሰቡ አባላት “ባለፉት ጊዜ በአካባቢያችን አስደማሚ ለውጥ ተመዝግቧል” ብለው እንዲያወሩ ስለመደረጉም ከተለያዩ ምንጮች የደረሰው መረጃ ያመለክታል።

በቀጣይም የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ሲባል በሚያሳፍርና ህዝቡን በማይመጥን አካሄድ በአከባቢው መንግስታዊ መዋቅር በአቤ-ልጅ ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም ላይ የተመሰረተ የቤተሰባዊ ኔትወርክ እንዲሁም እነኚያ የተዘፈቁበትን የኪራይ ሰብሳቢነት ተግባር ለመታገል በአሁኑ ወቅት ያለልዩነት የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ በተመለከተ እየተከታተልን በተጨባጭ መረጃና ማስረጃ በማስደገፍ የተከሰቱ ዘርፈብዙ ችግሮች እስኪፈቱ ድረስ እንደሚናቀርብ ለመግለጽ እንወዳለን።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *