በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን ያለልዩነት የተነሳውን “ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ” ይደግፋሉ የተባሉ ግለሰቦች እየታሰሩ ስለመሆኑ ተገለፀ።

የዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊና ህገመንግስታዊ መብት ተጠቅሞ በዎላይታ ዞን ውስጥ የሚስተዋለውን የመልካም አስተዳደር ችግሮችን መናገር፣ መንግስታዊ ሌብነትና ብልሹ አሰራርን ማጋለጥ እንዲሁም በአከባቢው መንግስታዊ መዋቅር በአቤ-ልጅ ኔትወርክና ጥቅም ላይ መመስረቱን በተመለከተ በአሁኑ ወቅት ያለልዩነት የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ማህበራዊ ሚዲያዎችን በመጠቀም ይፋ ለማድረግ የሚሞክሩና በእንቅስቃሴው ተሳትፈው አላቸው የተባሉ ግለሰቦች ከያሉበት ያለምንም ህጋዊ መጥሪያና አሰራር እየታሰሩ ስለመሆኑ ከየስፍራው የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።

ወጣቶቹና የመብት ተሟጋቾች የጅምላ እስራትና አፈሳ ለቤተሰቦቻቸው ጭምር እንዳይነገር ተብሎ በማስፈራራት በአረካ፣ ክንዶ ኮይሻ፣ ዳሞት ወይዴ፣ ሶዶ፣ ቦዲቲ ከተማ እንዲሁም ሌሎች መዋቅሮች ላይ የተጀመረ ሲሆን አንዳንድ የታሰሩ ግለሰቦች የሚያርፉበት እስርቤት ከመደበኛ ፓሊስ ጣቢያ ውጪ ስለመሆኑም ከአይን እማኞችና በአከባቢው ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተል ምንጭ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያስረዳው።

በትናንትናው ዕለት “ቃልን በተግባር ለኢትዮጵያ ብልጽግና” በሚል መሪህ ቃል በዞኑ በሁሉም ቀበሌዎች በተካሄደው ህዝባዊ ኮንፈረንስ ላይ አባላቱ የዎላይታ ህዝብ በሌብነትና በጥቅም ትስስር በተደራጀው የኔትወርክ ቡድን ምክንያት ከፍተኛ የመልካም አስተዳደርና የዴሞክራሲ እጦት እንዲሁም በደል እየደረሰበት በመሆኑ በዞኑ “ፓርቲያችን ከሚከተለው ዕሳቤና አሰራር ውጭ የተዘረጋው መዋቅር በአስቸኳይ እንዲፈርስ፤ በአስናዋሪ ድርጊታችሁ በመንግስት ላይ እምነት ለመጣል እንኳን እየተቸገርን ነውና የፓርቲውንም መልካም ስም የሚያጎድፍ የግለሰቦች ኔትወርክ ጉዳይ ላይ አስቸኳይ እርምት እርምጃ እንዲወስድ” በሚል የዎላይታ ዞን ብልፅግና ፓርቲ አባላት ያለልዩነት በይፋ መጠየቃቸውን መዘገባችን ይታወሳል።

በተቃራኒው በአከባቢው ባልተለመደ ሁኔታ አባላት ጠንከር ያለ ትችትና ቅሬታ በተለይም የዎላይታ አመራር ምደባ ስርዓት ብልጽግና ፓርቲ ከሚከተለው ዕሳቤና አሰራር ውጭ ዞኑ ለተለያዩ ችግሮች ስለመጋለጡ ተጨባጭ ማብራሪያ በማሰማታቸው አንዳንድ ቦታዎች ላይ ከኮንፈራንስ አዳራሽ በማውጣት ማሳር፣ ማስፈራሪያና ዛቻ ማድረግ እንዲሁም በአመራሮችና ፀጥታ አካላት ተገደው ይቅርታ ጠይቀው ከእንደገና ለተሰበሰቡ አባላት “ባለፉት ጊዜ በአካባቢያችን አስደማሚ ለውጥ ተመዝግቧል” ብለው እንዲያወሩ ከማድረጋቸው ባሻገር በዛሬው ዕለት ደግም “ለምን እንደዛ ተናገራችሁ ? ” ተብሎ እስርና እንግልት እየደረሰባቸው ስለመሆኑ ከተለያዩ ምንጮች እየደረሰ የሚገኘው መረጃ ያመለክታል።

የዎላይታ ዞን ከየትኛውም አከባቢ በላይ ሚዲያዎች፣ ህዝብ ውግንና ያላቸው አመራሮች፣ የመብት ተሟጋቾች እንዲሁም ወጣቶች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊ እና ህጋዊ መብት ተጠቅመው በአከባቢው የሚስተዋሉ መንግስታዊ አሰራርና ብልሽት ላይ በሰላማዊ መንገድ ትችት በሚያደርጉበት ወቅት በህገወጥ መንገድ በማፈን፣ በማሰር፣ ያለጥፋታቸው ፍርድቤት እንዲመላለሱ በማድረግ እንዲሁም በስደት ከአከባቢው እንዲሸሹ የሚያስገድድ መሆኑን በተደጋጋሚ መግለፃችን ይታወሳል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ በአከባቢው ዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ተፈጥሯዊና ህገመንግስታዊ መብት ተጠቅሞ ህገወጥ አደረጃጀትን ለመታገል በአሁኑ ወቅት ያለልዩነት የተነሳውን ህዝባዊ የለውጥ እንቅስቃሴ ላይ ለመሳተፍ በሚሞክሩ ግለሰቦች ላይ የሚደርሰውን የትኛውንም ጫና እንዲሁም አጠቃላይ ሂደት በተመለከተ ተከታትሎ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሰፊ ሽፋን የሚሰጥ ሲሆን የትኛውም ጠቃሚ ጥቆማዎች ካሉ ማድረስ እንደሚቻልም በዚህ አጋጣሚ እንገልፃለን።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *