
በጋሞ ዞን ቦንኬ ወረዳ ባለቤቱን ገድሎ ቤት ውስጥ የቀበረ ግለሰብ 24 ዓመት ፅኑ እስራት ተፈረደበት።
የ21 ዓመቷ ሟች ሊዲያ ጎባ እና ባለቤቷ በ2009 ዓ.ም ጋብቻ መስርተው አንድ ወንድ ልጅ ወልደው ሁለተኛ ልጃቸውን ካረገዘች ወራት ተቆጥረዋል።
በቦንኬ ወረዳ በተለምዶ ጤና ጣቢያ ሠፈር ግንቦት 17/2012 ዓ.ም ጧት 4፡00 ሠዓት አካባቢ በባልና በሚስት መካከል በተፈጠረ አለመግባባት ሠድባኛለች በሚል ምክንያት አንድ ጊዜ በዱላ አንገቷ ላይ ከመታት በኋላ በስለት የተለያየ የሠውነት ክፍሏን በመቆራረጡ ሕይወቷ አልፏል።
ሕይወቷ ማለፉን ያረጋገጠው ተከሳሽ አብርሃም አስከረኗን ቤት ውስጥ ጥሎ ወደ አርባምንጭ ከተማ ሄዶ በማግስቱ ከምሽቱ አራት ሠዓት ገደማ በአካባቢው ባልተለመደ ሁኔታ አስከሬኗን ቤት ውስጥ ቆፍሮ ይቀብራል።
ግንቦት 24/2013 ዓ.ም የሟች ቤተሰቦች ልጃቸው ሊዲያ ጎባ ከአካባቢው መጥፋቷን ለወረዳው ፖሊስ ይጠቁማሉ ፖሊስ በደረሰው ጥቆማ መሠረት ቤቱን ሲፈትሽ አስከረኗ ቤት ውስጥ በማግኘቱ ተቆፍሮ እንዲወጣ በማድረግ ባለቤቷን በቁጥጥር ስር በማዋል ምርመራ ሲያካህድ ድርጊቱን መፈጸሙን ያምናል።
ከፖሊስ የቀረበለትን የሰው እና የሠነድ ማስረጃ ይዞ የጋሞ ዞን ዐቃቤ ሕግ በጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሠረተ።
ጉዳዩን በጥልቀት የተመለከተው የጋሞ አካባቢ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የካቲት 12/2013 ዓ.ም ባስቻለው ችሎት ተከሳሽ አብርሃም ሙሉጌታ በቀረበለት የሰውና የሠነድ ማስረጃ ጥፋተኛ ሆኖ አግኝቶታል።
ወንጀሉ ከ25 ዓመት እስከ ሞት የሚያስቀጣ ቢሆንም የቤተሰብ አስተዳዳሪና ከዚህ በፊት የወንጀል ሪከርድ የለሌበት በመሆኑ የጥፋት ማቅለያ ተደርጎለት በ24 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ ወስኗል ሲል የጋሞ ዞን ፖሊስ መምሪያ ዘግቧል።