አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የአለምአቀፉ INBAR የተሰኘ ተቋም ዋና ዳይረክተር በመሆን መሾማቸው ተገለፀ።

በቅርቡ የመንግስት ኃላፊነትን በግል ምክንያት የለቀቁት አምባሳደሩ ዋና መስሪያቤቱን በቻይና አድርገው ከ50 በላይ ሀገራት ላይ በተለያዩ ጉዳዮች ዘላቂ ልማትን በማበረታት እየሰራ በሚገኘው አለምአቀፉ ተቋም ዋና ዳይረክተር በመሆን የተሾሙት።

ተቋሙ እ.ኤ.አ. በ 1997 ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በዓለም ዙሪያ በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ ሰዎች እና አከባቢዎች ላይ በቀርከሃ ምርት፣ የተራቆተ መሬት ወደነበረበት በመመለስ፣ በአቅም ግንባታ ስራዎች እና በአረንጓዴ ልማት ዘርፍ በርካታ ተግባራትን እያከናወነ የሚገኝ እንደሆነ ተገልጿል።

በቻይና ከሚገኘው ከተቋሙ ዋና መስሪያ ቤት በተጨማሪ ማስተባባሪያ ቢሮችን በካሜሩን፣ በኢኳዶር፣ በኢትዮጵያ፣ በጋና እና በህንድ በማድረግ ከ45 በላይ ሀገራት እየሰራ የሚገኘው ይሄው ተቋም በግብርና፣ በምግብና ገጠር ልማት፣ በአቅም ግንባታ፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ በልማት ትብብር፣ በትምህርት፣ በሥርዓተ-ፆታ እኩልነት እና ሴቶችን ማብቃት፣ በተፈጥሮ ሀብት አስተዳደር፣ በሰላምና ልማት፣ በግሉ ዘርፍ ልማት፣ በስነ ተዋልዶ ጤና እንዲሁም በምርምር ዘርፎችም ላይ ዘርፈብዙ ስራ እየሰራ የሚገኝ ግዙፍ አለምአቀፍ ተቋም እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

በተለያዩ ሀገራት በዲፕሎማሲያው ዘርፍ ኢትዮጵያን በብቃት ያገለገሉት አምባሳደር ተሾመ ቶጋ የኢትዮጵያ መንግስት በሰጠው አውንታዊ ምላሽ ታክሎበት ከቀናት በኃላ አዲሱን ስራቸውን በቻይና ቤጂንግ ከሚገኘው ዋና መስሪያቤት በማድረግ ይጀምራሉ።

አምባሳደር ተሾመ በቅርቡ እንደ አአ ከጥር 6 ቀን 2023 እስከ መጋቢት 13 ቀን 2024 የኢትዮጵያ ብሄራዊ መልሶ ማቋቋሚያ ኮሚሽን ኮሚሽነር የነበሩ ሲሆን በረጅም የሙያ ዘመናቸው የመንግስት ልማት ድርጅቶች ሚኒስትር እና የወጣቶች ሚኒስትርን ጨምሮ በኢትዮጵያ መንግስት ውስጥ ከፍተኛ የአመራር ቦታዎችን ተሳትፈዋል።

አምባሳደሩ በዲፕሎማሲው በሁለትዮሽ እና በባለብዙ ወገን ደረጃ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሲሆን በጋና፣ ግብፅ፣ ኬንያ፣ ፈረንሳይ፣ ቤልጂየም እና ቻይናን ጨምሮ አገራቸውን በአምባሳደርነት በስድስት ሀገራት እና በሶስት አህጉራት እንዲሁም በብራስልስ ለሚገኙ የአውሮፓ ህብረት ተቋማት እውቅና ተሰጥቷቸው በዩኔስኮ እንዲሁም በUNEP እና UN-Habitat የኢትዮጵያ ቋሚ መልዕክተኛ ሆነውም አገልግለዋል።

በተጨማሪም 120ኛውን የኢንተር-ፓርላማ ዩኒየን (አይፒዩ) አጠቃላይ ጉባኤን ጨምሮ በርካታ አለም አቀፍ ጉባኤዎችን መርተዋል እና 30ኛውን የአፍሪካ ፓርላሜንታሪ ህብረትን (APU)ን፤ እንዲሁም በተለያዩ አለም አቀፍ ኮንፈረንሶች ላይ በመሳተፍ በመንግስትም ሆነ በዲፕሎማሲው መስክ ያካበቱትን ልምድ አመራር፣ የዕቅድ፣ የማሻሻያ እና የፖሊሲ ማውጣት ልምድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረክታል ሲል ተቋሙ ባወጣው ዘገባ አስታውቋል።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *