በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር(ዎህዴግ) በዛሬው ዕለት የአቋም መግለጫ አውጥቷል። ሙሉ መግለጫ እንደሚከተለው ቀርቧል።

“(ዎህደግ) ለዎላይታ ሕዝብ ሁለንተናዊ ለውጥ ማለትም ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲረጋገጥ በሰላማዊ መንገድ የሚታገል ፓርቲ መሆኑን መላው የዎላይታ ህዝብ የሚገነዘበው ጥሬ ሀቅ ነው።

ይሁን እንጂ ሰሞኑን በመንግስት ሚዲያዎች “የከሸፈው ሴራ” በሚል በተሰራው ዶክመንተሪ ውስጥ “በዎላይታ ውስጥ በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች የሚደገፍ” የትጥቅ ትግል የተገለፀበትን ሐረግ ሰምተናል።

ለዚህም እንደማሳያ የቀረበው አንድ ግለሰብ/የዎላይታ ነፃነት ግምባር አመራር ነኝ ባይ በማቅረብ እንዲሁም የጦና ብርጌድ በመባል በሚታወቅ ቡድን ውስጥ አባል እንደሆነ እንደገለፀም ሰምተነዋል።

ከዚህም ባሻጋር በርካታ ጉዳዮችን ያነሳ ከመሆኑም በላይ ይህንን ቡድን የሚደግፉ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ተቃዋሚ ፓርቲዎችም እንዳሉ አያይዞ ጠቅሷል።

ስለሆነም ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ተወያይቶ አቅጣጫ ለማስቀመጥ ሲባል የዎላይታ ዴሞክራሲያዊ ግምባር የሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ሚያዚያ 23/2016 ዓ.ም አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ የሚከተለውን የአቋም መግለጫ አውጥቷል።

  1. ዎህደግ የዎላይታ ህዝብ ፍጹም ሰላማዊና ሌሎችን ልያስተምር በሚችል መንገድ ሰላማዊ ትግሉን የሚያካሂድ ከመሆኑም በላይ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል ተኪ የሌለው የትግል ስልት መሆኑን በጽኑ የምያምን፣ ጠብመንጃ አንስቶ መታገል ጊዜው ያለፈበትና ዘመኑን የዋጀ አለመሆኑን በመገንዘብ ሰላማዊ የሀሳብ ትግልን ያበረታታል።
  2. የዎላይታ ህዝብ ስነልቦናዊ አፈጣጠሩ ፈርሃ እግዚአብሔር ያለበት እና ለሰላማዊነት ቅድሚያ የሚሰጥ ድንቅ ሕዝብ በመሆኑ ከሕዝቡ ተፈጥሯዊ አፈጣጠር አንፃር የትጥቅ ትግል ተቀባይነት የሌለው መሆኑን ዎህዴግ ያምናል።
  3. ዎህዴግ ሰላማዊ የፖለቲካ ትግል አማራጭ ለዚህ ሀገር ብቸኛ መታገያ መንገድ መሆኑን የሚያምን በመሆኑ ከዚህ ውጭ የሚደረጉ የትኞቹም የትግል አማራጮች አክሳሪና አውዳሚ ስለሆነ ወደ ሰላማዊና የሀሳብ ፖለቲካ ትግል እንዲመጡ አጥብቆ ያሳስባል።

በመጨረሻም ከዚህ አቋም በተቃራኒ በየትኛውም መንገድ ሰላማዊ የዎላይታ ሕዝብ ትግልን ወደሌላ አቅጣጫ በመቀየር ሕዝቡንና አከባቢውን ለማጠልሸት የሚደረግ የትኛውንም እኩይ ተግባር የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ግምባር/ዎሕዴግ በጽኑ የሚያወግዝ መሆኑን እየገለጽን የፓርቲያችን አባላት፣ ደጋፊዎች እንዲሁም መላው የዎላይታ ሕዝብ በተለይ የዎላይታን ሕዝብ ነባር ማንነቱን የሚያጠለሽ በአከባቢው ያልተለመደ እንቅስቃሴ በንቃት እንዲከታተል ዎህደግ አጥብቆ ያሳስባል።”
ከሠላምታ ጋር!!!

የዎህዴግ ሥራ አስፈፃሚ
ሚያዝያ 23/2016 ዓ.ም
ዎላይታ ሶዶ፤ ኢትዮጵያ Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *