የዎላይታ ዞን ከክልሉ እና ከፌደራል መንግስት በተላለፈው አስቸኳይ ትዕዛዝ ሚዲያዎች ህገወጥ መግለጫ እንዳይቀርፁ መከልከሉ ተገለፀ።

በተጠረጠሩበት ህገወጥ ተግባር ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩና እንዲወገዱ ውሳኔ የተወሰነው የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር የነበሩት አቶ ተስፋዬ ይገዙ በዎላይታ ሶዶ ሌዊ ሪዞርት ካረፈበት ሩም (ክፍል) የዎላይታ ቴሌቪዥን በመጥራት የክልሉ ሆነ የዞኑ መንግስት ሳያውቅ ከህግና ስርዓት ውጪ በሆነ መንገድ በዛሬው ዕለት መግለጫ ለመስጠት ያደረገው ሙከራ በዞኑ መንግስት ትዕዛዝ እንዳይሰጥ መደረጉ ተነግሯል።

ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከስፍራው የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው የዎላይታ ዞን መንግስት ከክልሉ እና ከፌደራል መንግስት በተላለፈው ትዕዛዝ መሠረት በውሳኔ የታገደው አመራር ሆን ብለው በመንግሥትና በህዝብ መካከል ግጭትና ጥርጣሬ እንዲፈጠር በማንአለብኝነት በመነሳት በዛሬው ዕለት የዎላይታ ቴሌቪዥን፣ የደቡብ ሬዲዮና ቴለቪዥን ድርጅት ተወካይ ጋዜጠኛ እንዲሁም በአከባቢው የሚገኙ ሬዲዮ ጣቢያ ጋዜጠኞች መግለጫውን ተከታትሎ እንዲያስተላልፉ ወዳረፈበት ክፍል ያለ ህጋዊ አካሄድ ቢጠራም ሊሳካ አለመቻሉ ተገልጿል።

እስከ ቦታው ድረስ ሌሎች የተጠሩ ሚዲያ ባለሙያዎች ያልተገኙ ቢሆንም የዎላይታ ቴሌቪዥን ስራ አስኪያጅ ባለሙያዎችን ይዘው በሌዊ ሪዞርት ወስጥ ግለሰቦች ለማደር በሚይዙበት ክፍል ላይ ቢሮ በማስመሰል አዘጋጅቶ መግለጫ ወደሚሰጥበት ቦታ ሲደርስ የዎላይታ ዞን መንግስት ከክልሉ እና ከፌደራል መንግስት በተላለፈው አስቸኳይ ትዕዛዝ መሠረት እንዳይገቡ ከልክሎ እንዲመለሱ ማድረጉንም ከስፍራው ምንጮች አረጋግጧል።

የዞኑ መንግስት በዚሁ ህገወጥ ተግባር ላይ ለመሳተፍ ሙከራ ባደረጉ አመራሮችና ባለሙያዎች ላይ የተለያዩ እርምጃዎችን ለመውሰድ አስቸኳይ ስብሰባ እያደረገ እንደሆነም ተገልጿል።

በዎላይታ ዞን የመንግስትን መዋቅር ተክተው በአበ-ልጅነት ኔትወርክ፣ በአከባባዊነት ኔትወርክ፣ በትውውቅ እና በጥቅም እንዲሁም በቤተሰባዊ ኔትዎርክ ካደረገው ህቡዕ አደረጃጀት ጋር በቀጥታ ግንኙነት ባላቸው አመራሮች ላይ የፈደራል መንግስትና የክልሉ መንግስት በገለልተኛ ቡድን ማጣራቱን ተከትሎ በተጠረጠሩበት ህገወጥ ተግባር ከኃላፊነታቸው ታግደው እንዲቆዩና እንዲወገዱ ውሳኔ መተላለፉና በጉዳዩ ዙሪያ ውዝግብ መፈጠሩ ይታወቃል።

በዚሁ ህገወጥ አደረጃጀት ላይ እርምጃ እንዲወሰድባቸው የተወሰነው ውሳኔ ከከፌደራል በተመደበ ገለልተኛ አጣሪ ቡድን የተደረገው ሪፓርት ለክልልና ለፈዴራል መንግስት መቅረቡን ተከትሎ ቢሆንም “ዎላይታ ስለሆንኩ ተገፋው” በሚል እንዲሁም ብሄርን ከብሄር ጋር ለማጋጨት “ክልሉ ፈርሷል” እያሉ ህዝብን ለአመጽ እየቀሰቀሱና ጥሪ እያቀረቡ እንደሆነም መዘገባችን ይታወሳል። Wolaita Times

በናትናኤል ጌቾ ቤታሎ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *