የዎላይታ ህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲጠበቅ ሳይሰለቹ የሚሟገቱ የመብት ተሟጋቾች ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት ይላሉ ❓

በዎላይታ እና አከባቢው በተለይም ባለፉት አምስት አመታት ህገመንግስታዊ በክልል የመደራጀት መብት እንዲከበር ወጣቶች፣ ምሁራን፣ በመንግሥት መዋቅር የሚገኙ ባለስልጣናት፣ የፓለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም የተለያዩ ህብረተሰብ ክፍሎች በቀጥታ ሆነ በተዘዋዋሪ የትግሉ አካል በመሆን የህይወት መስዋዕትነት በመክፈል፣ አካል በማጉደል፣ ከስራና ከስልጣን በመነሳት፣ ለእስርና ለስደት ህይወት በመዳረግ መስዋዕትነት ከፍሏል።

መስዋዕትነት የከፈሉት ጉዳይ ለጊዜው ባይመለስም መንግስት በራሱ መንገድ ለህዝቡ ይበጃል በሚለው በማቀድና በማስፈፀም የአደረጃጀት ጥያቄ ምዕራፍ በመዝጋት “ደቡብ ኢትዮጵያ” የተባለ አዲስ ክልል በይፋ መስርቷል።

በአከባቢው የሚገኙ ህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲጠበቅ ሳይሰለቹ የሚሟገቱ የመብት ተሟጋቾች የአደረጃጀት ጥያቄ ብቻ ሳይሆን ከወትሮው በተለየ ሁኔታ መንግስት ለህዝብ መስራት አለበት ባላቸው የተለያየ ጉዳዮች ላይ የነቃ ተሳትፎ በማድረግ በርካታ የመንግስት አቅጣጫዎችን እስከማስቀየር ድረስ በጎ ሚና ተጫውተዋል።

ለምሳሌ ሁሉም ነገር ለጊዜው መስመር ባይዝም ከተልዕኮው ውጪ የዩኒቨርስቲውን ስልጣንና ሀብት በመጠቀም ለህብረተሰቡ የመፍትሄ አቅጣጫ ጠቋሚ መሆን ሲገባቸው በአከባቢውን ፓለቲካ ውስጥ ጠልቃ በመግባት ድብቅ ፍላጎታቸውን በማራመድ መዝረፍና ማዘረፍ፣ በአከባቢው መንግስት ትኩረት እንዳያደርግ “የማይሰራ የውሸት ፕሮጀክቶች ይሰራሉ” የሚል የማዘናጋት ወሬ በማባዛት፣ የሀሳብ ልየነት ያላቸው የለውጥ ኃይል በማሰርና በማሳሰር እንዲሁም ከስራና ከኃላፍነት ተባርረው እንዲሰቃዩ በማድረግ የተሰማሩ የዩንቨርስቲው ከፍተኛ አመራሮች እንዲሁም ለህዝብ አንድነት አደጋ የደቀኑ ቀንደኛ ተዋናዮች ከስልጣን ተወግደው የህግ ተጠያቂነት እንዲኖር የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጨምሮ ሌሎች የአከባቢው የለውጥ ናፋቂዎች እና የውስጥ አርበኞች ባደረጉት የሞት ሽረት ትግል ጉዳዩ የሀገር አጀንዳ እስከመሆን ደርሶ እርምጃ ተወስዶባቸዋል። ምንም እንኳን ከኃላፊነታቸው የተነሱ ሰዎች ቦታ የተተኩ ግለሰቦች አካሄድና ተያያዥ ተግባር ብርቱ ትግል የሚጠይቅ የቤት ስራ ከፊት ቢኖርም።

ሌላው ከዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ በተጨማሪ የዎላይታ ዞን መንግስታዊ መዋቅር ከሌሎች አከባቢዎች በብዙ መንገድ የሚለይ ነገር አለው። ስልጣን በትውውቅ፣ በዝምድና እንዲሁም በጥቅማጥቅም ትስስር የተመሠረተ በመሆኑ በአከባቢው ዘመድ የለለው ተገቢውን አገልግሎት ማግኘት የማይችልበት፣ ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት በከፍተኛ ውጤት የተመረቀ እያለ የአመራር ዘመድ ያለው ያለውድድር ወረቀት በግዢ ያመጣ የሚቀጠርበት፣ ጉቦና ብልሹ አሰራር የተለመደ አሰራር እየሆነ የመጣበት ሁኔታ ውስጥ ይገኛል።

በተጠቀሱ ጉዳዮች ዙሪያ ባለፉት ጊዜያት የተለያዩ በመረጃ የተደገፉ ተጨባጭ መረጃዎችን ለእናንተ ስናደርስ እንደነበር ይታወቃል። አሁን አሁን እንደዛ አይነት መንግስታዊ ስልጣን በመያዝ ህገወጥ የግልና የቡድን መዋቅር በመዘርጋት ህብረተሰቡን እያሰቃዩ የሚገኙትንና ከተለያዩ የለውጥ ናፋቂ ኃይል ጋር በቅንጅት ባደረግነው መራር የሚዲያ ትግል “የዋናዎቹ ቀንድ” የተሰበረ ቢሆንም እስካሁን ህብረተሰቡ ከፌደራል እስከ ቀበሌ ድረስ በስውር እነሱ ከፈጠሩት አደገኛ ህቡዕ አደረጃጀት ቀንበር ነፃ ባለመውጣቱ ዘርፈብዙ ችግር እያስከተለ ይገኛል።

እንደሚታወቀው የዎላይታ ዞን በሀገሪቱ ከየትኛውም አከባቢ በላይ ወደ ሁለት መቶ ሺህ የሚጠጋ ከታወቁ ከፍተኛ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁ የስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙበት ነው። በጨቅላ ዕድሜያቸው ከእናታቸው ተለይተው በሀገሪቱ ጎዳናዎች ሁሉ የስቃይ ህይወት እየገፉ የሚገኙት ህፃናት ፍልሰትም የችግሩ ስፋት የሚያመለክት ይሆናል። በአከባቢው በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት የወጣቶች የስራ ዕድል ከፍ የሚያደርጉ እንዱስትሪና ሌሎች ተቋማት አለመኖር ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶታል።

በአከባቢው ያለውን ፀጋ በመጠቀም ሀገር ውስጥና ውጪ የሚገኙትን እንዲሁም ሁሉንም ህብረተሰቡን ለአንድ አላማ በማሳለፍ ችግሩ ከስሩ እንዲቀረፍ ለማድረግ የመምራት፣ የማስተባበርና የማስተዳደር ብቃት ያላቸው በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎች እንዳይኖር ግለሰቦች በጥቅምና በዝምድና ተሳስረው ከፍተኛ ችሎታና ልምድ ያላቸው በየትኛውም ኃላፍነት ቦታ እንዳያገለግሉ በማግለል የዘረጉት አደረጃጀት ከፍተኛ ማነቆ እየፈጠረ ይገኛል።

ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ህዝብን ለማገልገል ኃላፊነት ወስደው በጥቅምና በዝምድና ሰፊውን ማህበረሰብ በመግፋት የራሳቸው የሆነ ጥቂት አደረጃጀት በመዘርጋት ዘርፈብዙ ችግር እያስከተሉ የሚገኙትን በማስወገድ በእውነተኛ ለውጥ የሚተጉትን እንዴት መተካት ይቻላል❓

በአከባቢው ላለፉት አምስት አመታት በአጋጣሚ በተገኙ የለውጥ ኃይሎች ከውስጥ የመነጨ ህዝባዊ ውግንና አስተባባርነት በአንድነት ለአንድ አላማ ያለ ምንም ልዩነት በሚያስደንቅ ሁኔታ ቆመው የነበረውን ህዝብ በድንገት የበተነውን ኃይል በመለየት በድጋሚ መስመር በማስያዝ ረገድ የህዝብ ጥቅምና ክብር እንዲጠበቅ ሳይሰለቹ የሚሟገቱ የመብት ተሟጋቾች ቀጣይ ትኩረት አቅጣጫ ምን መምሰል አለበት❓የአዲሱ ክልል ሆነ የዞን አመራሮች እንዲሁም በአከባቢው የምንቀሳቀሱ ፓለቲካ ፓርቲዎች ይሄንን ህዝባዊ አላማ ከግብ ለማድረስ ቅንጅታዊ አሰራር እንዴት ማመቻቸት አለባቸው❓

እንዲሁም የዎላይታ ምሁራን፣ ፓለቲከኞች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም በየደረጃው ተሰምነት ያላቸው ግለሰቦች ባለፉት እራት አመታት በዞኑ የፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ ለሀገራቸውና ለአጎራባች ህዝቦች ጭምር በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል የሚለው ሀሳብም ለጊዜው ምላሽ አላገኘምና በያለንበት ጊዜ ሳንሰጥ ልንወያይበት የሚገባ አንገብጋቢ ጉዳይ መሆኑ አከራካሪ አይመስለንም።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *