በዎላይታ ዞን ውዝፍ የወር ደመዝ ያልተከፋላቸውን ለመጠየቅ ሰልፍ የወጡ የመንግስት ሰራተኞች ድብደባና እስራት ገጠማቸው።

በትናንትናው ዕለት የሶስት ወር ደሞዝ ባለመክፈሉ አደጋ ላይ ወድቀናል የሚሉ የዎላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ መንግስት ሰራተኞች በሰላማዊ ሰልፍ እስከ ክልሉ ርዕሰ መስተደድር ቢሮ ድረስ የሄዱ ሲሆን ጥያቄያቸውን ይዘው ወደ አደባባይ እንዲወጡ ያስገደዳቸው የወረዳውን ሆነ የዞኑን መንግስት በተደጋጋሚ ቢጠይቁም በቂ ምላሽ ባይሰጥም በድጋሚ ዛሬ ወደ ዞኑ የሄዱትን ፓሊስ እንዲያባርርና እንዲታሰሩ መደረጉን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

ቅሬታ አቅራቢዎቹ እየሆነ ያለው ነገር የመንግስት ሠራተኛን ከእነ ቤተሰቦቹ ጭምር ለረሃብና ችጋር በማጋለጥ ወደ ጎዳና እንዲወጡ የማድረግ ስልታዊ አሠራር ነው። ብሎም የተማረ የሠው ሃይልን በማዳከም ሌላውን የማህበረሰብ ክፍልን ለመዝረፍና ለመጨቆን ሆነ ተብሎ እየተሠራ ያለ አምባገነናዊነትና ማሀይምነትን ለማስፋፋት ምቹ አጋጣሚዎችን ሁሉ አሟጠው የመጠቀም ህዝብን የማማረር አደገኛ ተልዕኮ ነው” በሚል ያምናሉ።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል የሠራተኛውን እና ቤተሰብ ህይወት ለመታደግ ደሞዝና የተለያዪ ጥቅማጥቅም በማስከበርና በመክፈል፣ ትውልድ የማስቀጠል አስቸኳይ እና ቀዳሚ የነፍስ አድን ሥራ እንዲሠራ ስንል እኛም ሆንን ቤተሰቦቻችን ከሞት አፋፍና ጣር ላይ ሆነን እንደአንድ የመንግስት ሠራተኛ ጩሄታችንን ስናሠማ፣ በተራበ አንጀትና በደከመ ጉልበታችን በጠወለገ ድምፃችን ነው” ስሉ የሰልፉ አስተባባሪዎች ገልጿል።

በተቃራኒው የዎላይታ ዞን ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብቻ ከ 3 ነጥብ 2 ቢሊየን ብር በላይ ገቢ መሰብሰቡ የተገለፀ ቢሆንም በአከባቢው ልማት ስራዎች ቆሞ በአብዛኛው መዋቅር ደመዝ መክፈል አለመቻሉ ለበርካቶች “ለምን” የሚል ጥያቄ ፈጥሯል።

በዎላይታ ዞን በታሪክ ታይቶ በማይታወቅ መንገድ ደሞዝ ለመንግሥት ሰራተኞች ባለመክፈሉ ምክንያት በአብዛኛው መዋቅር ትምህርት ቤቶች፣ ጤና ተቋማት እንዲሁም አገልግሎት ሰጪ መንግስታዊ ተቋማት አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውን ተከትሎ ተገልጋይ ህብረተሰብ ክፍሎችም ከፍተኛ ችግር ውስጥ ስለመግባታቸው ከተለያዩ ምንጭ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያሰባሰበው መረጃ ያመለክታል።

ደሞዝ ባለመክፈሉ “አደጋ ላይ ወድቀናልና እኔም የመንግሰት ሠራተኛ ነኝ ልጆቼንና ቤተሰቦቼን አድኑልኝ” የሚል ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

የፌዴራል መንግስት መፍትሔ ሊሰጥ ይገባል። በዎላይታ ዞን ዉስጥ ለሚገኙ መምህራን፣ የጤና ባለሙያዎች፣ የሌሎች ሴክተር መሥሪያ ቤቶች ሰራተኞች በ3/4 የከተማ መስተዳድሮች ዉስጥ ከሚገኙት በስተቀር ከወርሃዊ ደመወዛቸዉ ግማሽና ከዚያ በታች እየተቆራረጠ መከፈል ከጀመረ አራት ዓመታት ተቆጥረዋል።

ይባስ ብሎ ቀደም ሲል ግማሽና ከግማሽ በታች በየወሩ ይከፈል የነበረዉ ደመወዝ ዘንድሮ  ለ2/3 ወራት የዉሃ ሽታ ሆኖ በመቅረቱ  የመንግስት ሰራተኞችና ቤተሰቦቻቸዉ ለከፋ ችጋር ተዳርገዋል። በጣም አብላጫዎቹ ት/ቤቶች እና ጥቂት የማይባሉ የጤና ተቋማት ተዘግተዋል። በዞኑ ዉስጥ በመሠረተ ልማት፣ በማህበራዊ ልማት፣ በድህነት ቅነሳ ተግባራዊ እንቅስቃሴ ከተቋረጠ 4 ዓመታት ተቆጥረዋል።

ዞኑ በከፍተኛ ሰብዓዊ፣ ማህበራዊ፣ ፋይናንሻልና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ ዉስጥ ገብቷል። በዞንና ወረዳ ደረጃ ያለዉ አመራር አካል የዚህ ኪሳራ መንስኤዉ ምን እንደሆነ ለመናገር ፈቃደኛ አይደለም። ከቀጣይ የበጀት ዓመታት እና ከግል ባለሐብቶች እየተበደረ የሰራተኞችን ወርሃዊ ደመወዝ እያንጠባጠበም ቢሆን ሲከፍል ነበር።

ዘንድሮ ግን የብድር ምንጮችም ያሟጠጠ ይመስላል። አመራሩም የመንግስት ሰራተኛዉና ቤተሰቡ በአጠቃላይ የዞኑ ሕዝብ ግራ ተጋብቷል። ወይንም ተስፋ ቆርጧል። ለዚህ ችግር በአፋጣኝ ዘላቂ መፍትሔ ካልተበጀ አደገኛ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል። ለችግሩ ዘላቂ መፍትሔ ከዞኑ አመራር ይመጣል ብሎ መጠበቅ ስህተት ስለመሆኑ ብዙዎቹ ይስማማሉ።

ለዚህ ቀዉስ ዘላቂ መፍትሔ የማምጣት አቅምና ኃላፊነት ያለዉ ብልጽግና መራሹ የፌዴራል መንግስት ነዉ። ዞኑ የመንግስት ሰራተኛ ደመወዝ መክፈል ያልቻለዉ ከዓመታዊ በጀቱ የአፈር ማዳበሪያ ዉዝፍ ዕዳ እየተቆረጠ ስለሚወሰድ ነዉ ተብሎ ይነገራል።

ይሁንና ዉዝፍ ዕዳዉን ቆርጦ የሚወስደዉ  የፌዴራል መንግስት ዞኑን ለከፍተኛ የበጀት ጉድለት ዞኑን ለምን ይዳርጋል? ከአፈር ማዳበሪያ ዉዝፍ ዕዳ ከየበጀት ዓመቱ ተቆርጦ የሚወሰደዉ ገንዘብ መጠን የወላይታን ዞን ለከፍተኛ የበጀት ጉድለት በማይዳርግ መልኩ ለምን አይሆንም? ዞኑ የመንግስት ሰራተኞች ወርሃዊ ደመወዝ መክፈል አለመቻሉና ለአንገብጋቢ ፐብሊክ አገልግሎቶችና ፕሮጄክቶች ዜሮ በጀት መሆኑ ገዥውን ፓርቲና መንግስት አይገደዉም? አያሳስበዉም ወይ❓

ይባስ ብሎ ለሰራተኞች ደመወዝ ከቀጣይ ዓመታት በጀቱ በብዙ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እየተበደረ Cycle of budget deficit and indebtedness መዳረጉ አሉታዊ አንድምታዉን ገዥዉ ፓርቲና መንግስት በጥልቀት እየተገነዘበ ለዞናዊ ሁኔታዉ የመፍትሔ እርምጃ ያልወሰደዉ ለምንድነዉ❓በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠረዉ የወላይታ ሕዝብ የገጠመዉ ቀዉስ የፌዴራሉ መንግስት ቀዉስ አይደለምን?

ገዥዉ ፓርቲና መንግስት ዞኑን ለቁልል የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ዳርገዋል የሚባሉትን አጭበርባሪ ባለስልጣናትና ጥገኛ ባለሀብቶችን እስከዛሬ ድረስ በጉያዉ ሸሽጎ ለምን ያዘ❓ መንግስት ዉዝፍ የአፈር ማዳበሪያ ዕዳ ሙሉ በሙሉ ወይንም በከፊል ለምን አይሰርዝም?

በመጨረሻም ገዥዉ ፓርቲና መንግስት የዞኑ መንግስት ሰራተኞች በዚህ ዓመት ያልተከፈላቸዉን ደመወዝ አግኝተዉ ወደ መደበኛ ሥራቸዉ እንዲመለሱ እና እስከ በጀት ዓመቱ መዝጊያ ድረስ ወርሃዊ ደመወዛቸዉ ሳይንጠባጠብ ማግኘት የሚያስችል ልዩ የፋይናንስ ድጎማ እንዲያደርግና ዞኑን ከበጀት ኪሳራና ከብድር አዙሪት በዘላቂነት እንዲላቀቅ ዘንድ ልዩ የበጀት ፖሊሲ ተግባራዊ እንዲያደርግ ዘንድ በአክብሮት እናሳስባለን።

እነኚሁ አሁንም ደሞዝ ባለመክፈሉ “አደጋ ላይ ወድቀናልና እኔም የመንግሰት ሠራተኛ ነኝ ልጆቼንና ቤተሰቦቼን አድኑልኝ” የሚል ጥሪ በማሰማት ላይ ይገኛሉ።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *