“መንግስት ሀገሪቱ ወደ ከፋ ትርምስ ሳትገባ ሰሞኑን በአሜሪካ የተላለፈ ጥሪ ተቀብሎ ወደ ሃቀኛ ድርድር እንዲገባ” የፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ አሳሰበ።

በወቅታዊ ሁኔታ ላይ ከሀገሪቱ የተወጣጡ 13 የተለያዩ ተፎካካሪ ፓለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ አስቸኳይ መግለጫ እንደሚከተለው አውጥቷል።

“ሃቀኛ፣ አሳታፊና ተኣማኒ አገራዊ መግባባትና ዕርቅ ለነገ የማይባል የዛሬ ጥያቄ ነው። ለኮከሳችን መነሻ የሆነውና ምክክር ከጀመርንበት ጊዜ ጀምሮ ያለመሰልቸት ስንጠይቀው የነበረው የጋራ ጥያቄኣችን ወቅታዊነቱና ትክክለኛነቱ ከምንጊዜውም በላይ በአገራችንና ዓለምአቀፍ መድረክም እየተረጋገጠ ቢገኝም ለመለየት የሚያስቸግሩት ገዢው ፓርቲና መንግስት በተለመደው የአጀንዳ ነጠቃ፣ አግላይና ጠቅላይ ሥልጣኑን ማራዘም ዓላማው ባደረገ ‹‹ካፈርኩ አይመልሰኝ›› አካሄዱን አጠናክሮ ቀጥሎበታል፡፡

በዚህም የፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ የሚታየው የሰብዐዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ረገጣ ከሰላማዊ ህዝብና የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎችማሳደድ፣ አፈናና እስራት ወደ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እስራትና ግድያ በማደጉና የሰላማዊ ትግል በር መዘጋቱ፣ በመፈናቀልና ሥራ አጥነት፣ እንዲሁም ድምጽን የማሰማት አፈና ታግዞ ህዝብን በተለይም ወጣቱን ከስደት በተጨማሪ ‹ጥራኝ ዱሩ› ሃሳብን ተመራጭ በማድረግ ትንቅንቁንና አውዳሚ ውጤቱን እያጠናከረው ነው፡፡

በዚህ ላይ የጦርነት ኢኮኖሚው በውጪ ኢንቨስትመንት እርዳታና እገዛ ድርቅ ከመመታቱም ወቅታዊ እውነታውን፣ የህዝብን ህይወትና የኑሮ ውድነቱን ያላገናዘቡ ግዙፍ የቢሊዮን ዶላሮች የቅንጦት ፕሮጀክቶች ታግዟል፡፡

ይህ የፖለቲካና ማኅበረ-ኢኮኖሚ እውነታው ትናንት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደረቅ ስሞታና ጩሄት ነው። ከሚባልበት አሳልፎ መንግስታዊ መዋቅሮችን ጨምሮ በአገር ቤትና ዓለም አቀፍ መብት ጠበቆችና ተከራካሪዎች እንዲሁም ሚዲያዎች በስፋት እንዲያስተጋቡት ተጨባጭና ግልጽ ማስረጃ ሆኗል፡፡

በዚህ ሂደት ገዢው ፓርቲ/መንግስት የፖለቲካ ፓርቲዎችና ባለድርሻ አካላት ለረጅም ጊዜ ሲያቀርቡ የነበረውን የመግባባትና ዕርቅ ጥያቄ ለማዳፈን ከጥያቄው ባለቤቶች በላይ ስለ አስፈላጊነቱ በመስበክ በምላሹም የፖለቲካ ፓርቲዎች ያሰሙትን ጥያቄና ተቃውሞ ለመሸፈን ጥር 28/2011 አዋጅ ቁጥር 1102/2011 በማውጣት “የእርቀ ሰላም ኮሚሽን አቋቋምኩ” በሚል እንቅስቃሴ ቢጀምርም ምንም ውጤት ሳያመጣ ኮሚሽኑ ከከንቱ ድካምና ሃብት ብክነት በኋላ ድምጹን ሳያሰማ መክሰሙ የሚታወስ ነው፡፡

ሆኖም ጥያቄው ተጠናክሮ በመቀጠሉ እንደገና በ2013 ሁለተኛ አጋማሽ ‹‹ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን›› በሚል ሥያሜ በአዋጁ በኮሚሽኑ ዓላማ (አንቀጽ 5) ላይ ‹‹የኮሚሽኑ ዓላማ በኢትዮጵያ ህዝቦች መካከል ፍትህ፣ ብሄራዊ አንድነትና መግባባት፣ እንዲሁም እርቅ እንዲሰፍን መሥራት ነው›› ለሚለው ማስፈጸሚያ ከተሰጠው ሥልጣንና ተግባራት (አንቀጽ 6) ‹‹ተደራሽ፣ አሳታፊ ሁሉም አካል እኩል ተደማጭ የሚሆንበት የዕርቀ ሰላም ውይይት መድረክ ማዘጋጀት›› የሚለውን በማያሟላና የኮሚሽኑን አባላት ከአዋጁ መንፈስ ውጪ በመሰየም ኮሚሽኑን ለፖለቲካ ፍጆታና ዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ግንኙነት ማሻሻያና ብድርና ዕርዳታ ማስገኛ እና ለሥልጣን ማራዘሚያ እየተጠቀመበት ነው፡፡

ከዚህ አልፎም በትጥቅ ትግል ከሚፈታተኑት ጋር ከህወኃት የማይተገበር ዕርቅ በማውረድ፣ -ስምምነት ሊያስደርስ የማይችል ቅድመ ሁኔታ በማቅረብ፣ እንዲሁም በሌለ ሽግግር ‹‹የሽግግር ፍትህ አዋጅ›› በማውጣት የዘላቂ ሠላምና መረጋጋት፣ ዕርቅና አገራዊ አንድነትና ተቆርቋሪነት ለማሳየት ጥረት እየተደረገ ቢሆንም ከንቱ ድካም ሆኖ እንኳን ለዘላቂ መፍትሄነት ለፕሮፖጋንዳ ዓላማውም መዋል አልቻለም፡፡ ይህ በሆነበት ዛሬም የሀገራዊ ውይይት ኮሚሽኑ ቆም ብሎ አካሄዱን እንዲጠይቅና እንዲመረምር ስላልተፈቀደለት በያዘው ኢተኣማኒና አግላይ ጉዞው እየገፋ ነው፡፡

በመሆኑም በአገራችን በተጨባጭ የሚታየው እየሰፉና እየተስፋፉ የመጡት የትጥቅ ትግሎች፣ ኢኮኖሚ ድቀትና ጣራ የነካ የኑሮ ውድነትና ሁለንተናዊ ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ ከመቼውም ጊዜ በከፋ ሁኔታ ቀጥሏል፡፡ በሰሞኑ በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሃመር በተገኙበት በአሜሪካን አምባሳደር ኤርቪን ማሲንጋ የተገለጸው የመንግስታቸውን ‹‹ፖሊሲ›› በሚመለከት ያቀረቡት መግለጫ ለዚህ ተጨማሪ አስረጂ ነው፡፡

ኮከስ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በላከው በዚሁ የአገራችን ነባራዊና ወቅታዊ ተጨባጭ ሁኔታ እና በአምባሳደሩ የተገለጸውን የመንግስታቸውን ፖሊሲ ገምግሞ የሚከተሉትን አቋሞች ወስዷል፡፡

1ኛ/ የአሜሪካ መንግስት ከወትሮው በዲፕሎማሲ ቃላት የተድበሰበሰ አካሄድ ወደ ሃቀኛ አረዳድና ግልጽ አገላለጽ መሸጋገሩ አበረታች እርምጃ ነው፡፡ በመሆኑም ላቀረበው ምክረ ሃሳብ ተፈጻሚነት ከኢትዮጵያ ህዝብ ሠላማዊ ትግል ጎን እንዲቆም፣ በባለድርሻዎች በተለይም በገዢው ፓርቲ ላይ፣ አዎንታዊ ተጽዕኖ በማሳረፍ ዘላቂ ሠላምና የፖለቲካ መረጋጋት፣ አገራዊ አንድነትና ቀጣይነት ያለው ዕድገትና ልማት፣ ጤናማና በመከባበር ላይ የተመሰረተ ማኅበራዊ ግንኙነት እንዲመሰረት የወዳጅ ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክት፣

2ኛ/ ገዢው ፓርቲ/ መንግስት ለህዝባዊ ጥያቄውና በተመሳሳይ ለአሜሪካ መንግስት ምክረ ሃሳብ በተለመደው የማደናገርና ከተጨባጭ እውነታው በተቃራኒ የሚያደርገው ጥረት በምንም መንገድ እውነታውን ለመሸፈንና የፖለቲካና ባለድርሻ አካላትን ህዝባዊ ጥያቄም ሆነ የዓለምአቀፍ ማኅበረሰቡን መረዳት ሊያዳፍን አይችልም፡፡

በመሆኑም መንግስት አገሪቱ ወደ ከፋ ትርምስ፣ ህዝቦቿን ወደ ድቅድቅ ጨለማ ከመገፋት አደጋ ለመታደግ የአሜሪካ መንግስት በአምባሳደሩ በኩል ባስተላለፈውን መልዕክት ከማንም በላይ ተጠቃሚ በመሆኑ ጥያቄውንና ጥሪውን ተቀብሎ ወደ ሃቀኛ ድርድር እንዲገባ አጥብቀን እንጠይቃለን፡፡

3ኛ/ በሁለቱም ወገን የሚደረገው የነፍጥ ትንቅንቅ የሚያስከትለው የወንድማማቾች ህይወት መቀጠፍ፣ የአገርና ህዝብ ሃብት ውድመትና ማኅበራዊ ምስቅልቅሎሽ እንዲገታ ጊዚያዊ የተኩስ አቁም በማድረግ ለዘላቂ ሠላምና መፍትሄ በነጻነት ለሚደረግ ሁሉን አቀፍ አሳታፊ፣ ሃቀኛና ተኣማኒ ብሄራዊ መግባባትና ዕርቅ መድረክ በአፋጣኝ ማድረግ ለነገ ይደር የማይባል አስቸኳይ ተግባር መሆኑን ስንገልጽ ለተግባራዊነቱ ዝግጁነታችንን እናረጋግጣለን፡፡”

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኮከስ
የካቲት 14/2016፣
አዲስ አበባ
#ኢትዮጵያ Wolaita Times

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *