ዩኒቨርሲቲው በአረካ ከተማ ለሚያስገነባው የግብርና ካምፓስ ማስፋፊያ እና የምርምር ልዕቀት ማዕከል 50 ሄ/ር መሬት ከወላይታ ዞን አስተዳደር መረከቡን የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር አስታወቀ፡፡

የትምህርት ተቋማትን በማስፋፋትና ተደራሽ በማድረግ የህብረተሰቡን በትምህርት የመልማት ፍላጎት ለማሟላት በተጠና እና በተቀናጀ መልኩ አበክረን እንሰራለን ሲሉም የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ታከለ ታደሰ ተናግረዋል፡፡

ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በ10 ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅዱ ውስጥ ኮሌጆችን ከዋናው ጊቢ በማውጣት ካምፓሶችን ለማስፋፋት ዕቅድ ይዞ እየሰራ መሆኑን የዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕ/ር ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰ ገልጸዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በዛሬው ዕለት ከማኔጅመንት አባላት ጋር በነበራቸው ውይይት ከዩኒቨርሲቲው የትኩረት መስኮች አንድኛው ግብርና መሆኑን አውስተው፤ ለዘርፉ ዕድገት በተቀናጀ መልኩ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
ዩኒቨርሲቲው በ2022 ዓ.ም ቴክኖሎጂ መር የግብርና ልህቀት ማዕከል እንዲሆን የተያዘውን ራዕይ እውን ለማድረግ ከወዲሁ የቅድመ ዝግጅት ስራ እየተሰራ መሆኑንም ፕ/ር ታከለ ታደሰ አሳውቀዋል፡፡
ይህንን ራዕይ እውን ለማድረግ እንዲያስችል ዩኒቨርሲቲው ከወላይታ ዞን አስተዳደር 50 ሄ/ር መሬት ርክክብ ማድረጉንም ፕሬዛዳንቱ አሳውቀዋል፡፡
በአረካ ከተማ በሚገነባው በዚህ የግብርና ካምፓስ ማስፋፊያ እና የምርምር ልዕቀት ማዕቀል ከግንባታ አንጻር በመጀመሪያው ምዕራፍ G+3 ሁለት መማሪያ ህንጻዎች ፣ G+6 ሁለት የተማሪ ማደሪያ ህንጻዎች፣ 3 ሺ ተማሪዎችን የሚይዝ አንድ ካፍቴሪያ፣ አንድ ቤተ-መጽሐፍት እንዲሁም አንድ የመምህራን መኖሪያ አፓርታማ ለማስግንባት ዕቅድ መያዙን ፕ/ር ታከለ ጠቁመዋል፡፡
የግንባታው ሂደት ከሐምሌ ወር 2013 ዓ.ም እንደሚጀምር ዕቅድ መያዙን ፕሬዝዳንቱ ተናግረው፤ በአካባቢው የግብርና ካምፓስ ማስፋፊያ እና የምርምር ልዕቀት ማዕከል መገንባቱ የመማር ማስተማር ስራውን ምቹ ከማድረግ ባሻገር ለአካባቢውን ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትየጎላ ድርሻ ይኖረዋል ብለዋል፡፡


ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በ 7 ኮሌጆች እና በ 3 ትምህርት ቤቶች 38 ሺ ተማሪዎችን በመደበኛ እና በተከታታ የትምህርት መርሃ ግብር እያስተማረ የሚገኝ ሲሆን፤ አብዛኛው ተማሪ በዋናው ጊቢ በተጨናነቀ መልኩ እየተማረ እንደሚገኝም ፕሬዝዳንቱ አሳውቀዋል፡፡


በዩኒቨርሲቲው ስትራቴጂክ ዕቅድ በተቀመጠው አግባብ ኮሌጆችን ከዋናው ካምፓስ በማውጣት የትምህርት ማዕከላትን በየአካባቢው ማስፋፋት ችግሩን እንደሚቀርፍ ፕ/ር ታከለ ተናግረዋል ሲል የዩኒቨርስቲው ኮሙኒኬሽን ዳይሮከተሬት ዘግቧል፡፡