በዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ የቆሙ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ላይም ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ አለመኖሩ የዩንቨርስቲውን ማህበረሰብ እያሳሰበ እንደሆነ ተነግሯል።

የዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ በሀገሪቱ ውስጥ ካሉት አብዛኛዎቹ ዩኒቨርሲቲዎች በከፋ ደረጃ ስሙ ከአሰተዳደራዊ ብቃት ጉድለት፤ ምዝበራና ሌብነት እንዲሁም የሴራ ፓለቲካ ተልዕኮ አስፈፃሚነት ጋር በተያያዘ ሲነሳ ከቆየ በኃላ ብዙ መቶ ሚሊየን የህዝብ ገንዘብ ከፋይናንስ ሥርዓት ውጭ መመዝበሩ በኦዲት ተጣሪቶ በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ሥልጣን በተሰጠው ጉዳዩ በሚመለከተው ኮሚቴ በኩል ለህዝብ ይፋ መደረጉ ይታወቃል፡፡

በሙስናና በብልሹ አሰራር ምክንያት በተነሱ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ ፕረዚዳንትና ምክትል ፕረዚዳንቶች ከኃላፊነት ተወግደው በትምህርት ምንስቴር በኩል አድስ አመራሮችን በብቃታቸው አስፈትኖና አወዳድሮ ሳይሆን ከተለያዩ ዩንቨርስቲዎች በምደባ ኃላፊነት ቦታ ተሰጥቷቸው እንደነበርም ይታወሳል።

የአሰራር ብልሹነት ዩኒቨርሲቲው ከተመሰረተ አንስቶ የዩኒቨርሲቲው የበላይ አመራር በብቃቸው ሳይሆን በፖለቲከኞች ጥቆማና ግለሰቦቹ ለካድሬዎች በሚኖራቸው ቅርርብና ታማኝነት ከያሉበት ተጠርተው የተመደቡ በመሆናቸው ለአመራርነት ተሹመው የተረከቡበትን ቢሮ መደበኛ ስልጣን ጊዜያቸውን በብቃት አጠናቅቀው ያስረከቡ ሳይሆን በአብዛኛዎቹ ላይ ክስ ሳይቀርብባቸው ወንበራቸውን ተነጥቀው ለመውጣት የተገደዱ እንደሆነ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡

ከላይ በጥቂቱ በተገለፀው ነጥብ ምክንያት ተቋሙ በአደረጃጀት አንጻር ሀገሪቱ ውስጥ ካሉት በተለምዶ ሶስተኛ ትውልድ ዩኒቨርሲቲዎች ከሚባሉት ምድብ ቢሆንም በተቋማዊ ቁመናው ግን ከአነዚህ ያነሰና አራተኛ ትውልድ ተርታ የሚመደብ እንዲሆን በማድረግ አሁን ላይ ዩኒቨርሲቲው በመዘጋትና አለመዘጋት መሀል እየተንገዳገደ እንደሚገኝ አንድ በዩንቨርስቲው ከፍተኛ ተማራማሪ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

እንደ ተመራማሪው ገለፃ በምዝበራ የተዘፈቀው አመራር እንዲነሳ ከመታገል በላይ ወሳኝ እርምጃው አዲስ ማነጅመንት መተካት ያለበት ግልፅ የሆነ የሀላፊነት ቦታዎች የሚመጥን መስፈርት ወጥቶላቸው እና ይህም በማስታወቂያ በብዙሐን መገኛኛ በግልፅ ይፋ ተደርጎ መስፈርቱን የሚያሟሉት ተወዳድረው  ቦታን አሸናፊው ተለይቶ ሲረከበው ቢሆንም ያ ባለመሆኑ የችግሩን ሁኔታ እያባባሰው እንደሆነ ጠቁመዋል።

ከአዲሱ የትምህርት ጥራት አገር-አቀፍ የትምህርት ሚንስቴር የትኩረት አቅጣጫ ጋር በተያያዘ አሁን ካሉን ዩኒቨርሲቲዎች የተወሰኑት በሚቀጥሉት ጥቂት ዓመታት ሙሉ በሙሉ ባይዘጉ እንኳን ከደረጃቸው ዝቅ ብለው ለመቀጠል እንደሚገደዱ አሁን እየተስተዋለ ያለው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ቁጥር እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ መቀነሱ፤ ተማሪዎች ወደ ተቋሞቹ በምርጫቸው ሊመጡ ያለ መሆኑና መሰል ተጨባጭ ሀቆች ከበቂ በላይ የሚያስረዱ ሲሆን ምናልባት ሳይዘጉ መትረፍ የሚችሉት ዩኒቨርሲቲዎች ከፍተኛ የሆነ የአመራር ብቃት፤ አርቆ-አስተዋይነትና ተቋማዊና ማህበረሰባዊ ተቋርቋሪነት የተላበሰ ማነጅመት ጥረት ቢሆንም አሁን ላይ ነገሮች ከዚሁ በተቃራኒ እየሄዱ እንደሆነም ተመራማሪው አክለዋል፡፡ 

በሌብነትና ምዝበራ የተሳተፉት ግለሰቦች ከሀላፊነት ስለመታገዳቸው እንኳን ምንም በይፋ ሳይገለፅ ሌባ በአዲስ ሌባ፤ መዝባሪ በሌላ መዝባሪ፣ ብቃት-አልባ ማነጅመንት እንዲሁም ለህብረተሰቡና ተቋሙ ራዕም ሆነ ተቋርቋሪነት በሌለው ደንታ-ቢስ መንገደኛ በተለመደው ከሩቅ የተጠራሩት የቆሸሽዉን የዩኒቨርስቲ ገጽታ የማደስና የመገንባት ኃላፊነት ቅድሚያ ሰጥተው መስራት ሲገባቸው ተቋሙን የባሰ ችግር ውስጥ እየከተቱ እንደሆነ መታዘባቸውንም በመጠቆም በአሁኑ ወቅት ዩንቨርስቲው የበፊቱን ስህተት ማረም ይቅርና በፊት የነበሩ ጥቂት የተግባር እንቅስቃሴዎችንም ጭምር በማቆም ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

ከዚህ በፊት “ዩንቨርስቲው ለዲዛይን ብቻ በርካታ ገንዘብ ያወጣባቸው የአባላ አባያ ሳሜር ሲቲ ፕሮጀክት፣ የዩንቨርስቲው ኮምፕረሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ የአረካ የግብርና ልህቀት ማዕከል፣ የቦዲቲ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ልህቀት ማዕከል እንዲሁም በአከባቢው በየቦታው በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ እንሰራለን” በሚል ይፋ የተደረጉ ፕሮጀክቶች እንዲሰሩ አዲሱ አመራሮች እንቅስቃሴ አለማድረግ ብቻ ሳይሆን በሌሎች ዘርፎች ላይም ምንም አይነት ተስፋ ሰጪ ተግባር ውስጥ አለመግባታቸው የዩንቨርስቲውን ማህበረሰብን በከፍተኛ ሁኔታ እያሳሰበ እንደሆነም እኚሁ ተማራማሪ ገልጸዋል።

ለመዝረፍና ለማዘረፍ የተነቃበት ሌባ ሲባረር በምስጢር ያልተነቃ ዝምተኛ ሌባ የመጣ ይሁኑ❓

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *