የአካባቢያችን ሁኔታ ከሀገሪቱ ፓለቲካ ሁኔታ አንፃር ሳይሆን ከእኛው ለህዝብ ይበጃል በሚለው ትግል አካሄድ ሁኔታ አንፃር ሳስብ ሁልጊዜ በአእምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎችና ቁጭት አለኝ። በግለ የረጅም አመት የፓለቲካ ተሳትፎ ሆነ በውስጡ የማለፍ ልምዴ በጣም ጥቂት አመት ቢሆንም ባለፉት አምስት አመታት በህዝባችን ላይ የደረሰው በደልና የመብት ጥያቄ መነፈግ የፈጠረውን ህዝባዊ ትግል እንደ አንድ የብሄሩ ተወላጅ ብቻ ሳይሆን እንደ ባለሙያም እያንዳንዱን ነገር በቅርበት የመከታተልና የመታዘብ ዕድሉን በሰፊው ሰጥቶኛል።

በዚያ ሁሉ የመጣንበት ጉዞ መካከል በሀገር ውስጥ ከተበዳዩ ህዝብ መካከል በመኖር የችግሩን ጥልቀት ተመልክቻለሁ፣ በተመሳሳይ ለህዝብ መብት ይታገላሉ ከተባሉ ከታች እስከ ላይ ድረስ ከሁሉም ወገኖቼ ጋርም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ የመነጋገር፣ የመመካከር እንዲሁም በጋራ የመስራት ዕድሉንም አግኝቼ አይቸዋለሁ።

በተቃራኒው ደግሞ ከሁኔታዎች አለመመቻቸት የተነሳ ከሀገር ውጪ በስደት ሆይኜም በህዝብ ጉዳይ ያገባቸዋል ከሚለው ከታች እስከ ላይ ድረስ ከሁሉም ከሀገር ውስጥ ሆነ በተለያዩ አለም ክፍል ከሚገኙ ወገኖቼ ጋርም ቀጥተኛና ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለህዝብ ክብርና ተጠቃሚነት ጠቃሚ መረጃዎችን የመለዋወጥ፣ የመነጋገር፣ የመመካከር እንዲሁም በጋራ የመስራት ሰፊ ዕድል ተጠቅሜ በነፃነት የበኩሌን ለመወጣት ጥረት እያደረኩ እገኛለሁ።

እሱ ብቻ ሳይሆን በአካባቢያችን የነበረው በህዝብ ጉዳዮች ላይ ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ ሁኔታ ምቹ ባለመሆኑ የመስራት አቅም እያለሁ ተገፍቶ የተቀመጠው ወንድሜ ታጁራ ላምቤቦ በሰው ሀገር ብቻዬ ከሚሆን አብሮኝ ለትግላችን ተጨማሪ አቅሜ በመሆን ያግዛል በሚል ወደ እኔ እንዲመጣ ከሌሎች የአላማ ደጋፊ ከሆኑት ጋር በመተባበር እንዲመጣም ጭምር አድርገናል።

ይሄው የህዝብ በደል የወለደው ትግል ከህፃን እስከ አዋቂ አሰልፈው ከመቸውም ጊዜ በላይ በአከባቢው ህዝብ ማህበራዊና ፓለቲካዊ ጉዳዮች ላይ በንቃት በማሳተፍ የተለመደው “የህዝብ ጉዳይን መንግስት በተመቸው መንገድ በራሱ ይፈፅማል” በሚል በአብዛኞቹ የሚወሰደው አካሄድ ተቀይረው “የህዝብ ጉዳይ እኔንም ያገባኛል” በሚለው ሙግት ተቀይረው የተደረገው እልህ አስጨራሽ ትግል ለጊዜው የተወሰነ ጥቂት ፍሬ ቢያሳይም ለወደፊቱ ግን ተስፋ ሰጪ ትልቅ ልምድና በህዝብ ጉዳይ ላይ ንቁ ተሳትፈው ለማድረግ የሚያስችል አቅምና የስነልቦና ወኔ አስታጥቆ ማለፉን እረዳለሁ።

የትግሉ ጉዞ በጥቂቶቹ ላይ በግለሰብ ደረጃ የህይወት መስዋዕትነት፣ የአካል መጉደል፣ ከስራ መፈናቀል፣ የፍትህ መጓደል፣ ስደትና እስራት ቢያተርፍም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ዛሬም ነገም ከጎኑ ለመቆምና ሊካራከርለት የሚችል ትውልድ እንዲፈጠር በጎ ሚና መጫወቱም አይካድም።

እርግጠኛ ሆይኜ በድፍረት መናገር የሚችለው ነገር ቢኖር በዎላይታ ባለፉት አምስት አመታት ውስጥ የተከሰቱ የፓለቲካ ውጣውረድ አይነት የዎላይታ ህዝብ ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለ 135 ዓመታት ወዲህ ያልተከሰተ በታሪክ ድርሳናት ላይ ለቀጣይ ትውልድ ብቻ ሳይሆን ለእኛ ትውልድ መማሪያነትም ጭምር እንዲሆን ተሰናድቶ መቀመጥ ያለበት ታሪካዊ ክስተት ነው ብዬ አምናለሁ።

በዚሁ ሁሉ ትንቅንቅ ጉዞ ውስጥ የአካባቢያችን ሁኔታ ከሀገሪቱ ፓለቲካ ሁኔታ አንፃር ሳይሆን ከእኛው “ለህዝብ ይበጃል” በሚለው ትግል አካሄዳችን አንፃር ሳስብ ሁልጊዜ በአእምሮዬ የሚመላለሱ ጥያቄዎችና ቁጭት አለኝ።

እሱም፦ ዋናው የህዝብ ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ በውስጣችን አንድነት ተፈጥሮ ሁሉንም በየአቅጣጫው የየራሳቸው ሀሳብ ልዩነት ያላቸውን በፍቅርና በዋናው ህዝብ ጉዳይ ላይ በጋራ እንዲሰለፍ በአክብሮትና በዲፕሎማቲክ አካሄድ ከማቅረብ ይልቅ እንደ ጠላት በመቁጠር የማሳደድ፣ ስም በማጥፋት የበለጠ እንዲርቅና በተቃራኒው እንዲቆም የማድረግ፣ በውስጣችን የእነሱና የእኛ አይነት ክፍፍል ቡድን የመፍጠር፣ የሀሳብ ልዩነት ያለው ግለሰብ እስኪጠፋ ብቻ ከታገልን በኃላ ዋናው ውጤት የሆነውን የህዝብ ጥቅም መርሳት፣ ግለሰቦች በስልጣን እያሉና ከስልጣን ሲወርዱም የህብረተሰባችን አካል መሆናቸውን በደምብ አለመገንዘብ የተፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ካደረጉ ነጥቦች ውስጥ የሚካተት ነው።

በተለይም እውነተኛና ሀቀኛ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ውሸትና ጠልፎ የመጣል እንቅስቃሴ ማካተት፣ ከህዝብ ጥቂት ይልቅ የራስ ጥቅም ብቻ አብዝቶ መጮህና የፈለግነውን ሲገኝ ዝምታ መምረጥ፣ በየደረጃው የሚገኙ ህዝብን በመንግሥት ደረጃ ስልጣን ያላቸውን ወደ ህዝባቸው እንዲቀርቡ በሚያስችል መንገድ ከመስራት ይልቅ የበለጠ እንዲርቁ ዘመቻ በመክፈት በእርስበርስ ጥላቻ በሚፈጠረው አንድነት ማጣት ምክንያት ለሶስተኛ ወገኖች ጥቅም አሳልፎ እንዲሰጥ ማድረግ፣ ትኩረታችንን በዋናው ህዝብ ጉዳይ ማድረግን ትተን በትግል ሂደቱ ላይና በሚከሰቱ ጥቃቅን ጉዳዮች ምክንያት እርስበርስ መናናቅና የትግሉን አቅጣጫ ወደ ግለሰቦች በማድረግ አላማችንን መሳት ይጠቀሳሉ።

ሌላው እርስበርስ አለመደማመጥና ለታላላቆቹ በተለይም ልምድ ያላቸው በህዝብ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም አበርክተዋቸውን እንዲያወጡ ማድረግን መዘንጋታችን እስራኤላውያን ከግብፅ ለመውጣት 40 ቀን ብቻ የሚፈጀውን ጉዞ በመንገዱ በነበረው በራሳቸው እርስበርስ አለመስማማት ምክንያት በ40 አመት እንዳሳኩ ሁሉ ለእኛም ዛሬ ላይ ከላይ በጥቂቱ የጠቀስኳቸው የቤታችን ጉድለቶች አንድነትን በማጣታችን ምክንያት ገናና የነበረው ህዝብ በከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛልና ቆም ብለን አስተውለን በቁጭት የመጣንበትን መንገድ ገምግመን መፍትሔ ሊናበጀው ይገባል እላለሁ።

ምናልባት ይሄንን ፅሁፍ የሚያዩ አንዳንድ ሌሎች ወገኖች “እንዴት የዎላይታ ህዝብ ልዩ አድርገህ ታቀርባለህ” የሚሉ አይጠፋም። አዎ የዎላይታ ህዝብ ጉዳይ ልዩ ነው። አዎ የዎላይታ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከየትኛውም ሀገራቱ ክፍል የተለየ መልክ ያለው ነው። አዎ የዎላይታው ችግር በሀገሪቱ ትግራይ በተካሄደ እና በአማራ ክልል እየተካሄደ ከሚገኘው እርስበርስ ጦርነት የበለጠ የባሰ ነው እላለሁ።

በሀገሪቱ በተደረጉና እየተደረጉ ባለው ጦርነት ከየትኛውም ብሄር በበለጠ ከፊት ተሰልፈው መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙት ከዎላይታ ስለመሆናቸው መከላከያ ሚኒስትር ስለቁጥራቸውና መስዋዕትነታው ምስክር ነው። በሀገሪቱ ከተሞች በየጎዳናው በአባታቸው በእናታቸው አቅፍ ሆነው ማደግና መማር የሚገባቸው ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች በአከባቢው ምንም የስራ ዕድል ባለመፈጠሩ ምን እየሰሩ እንደሆነ ለፈጣሪ ብላችሁ አልተመለከታችሁም እንዴ? በዎላይታ ከመንግሥት ዩንቨርስቲ ከዲግሪ የተመረቁ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ስራአጥ ወጣቶች ስለመኖራቸው የማያውቅ ኢትዮጵያዊም አለ እንዴ⁉️

ለመሆኑ ትናንት ከአንድ ሰው ዕድሜ በፊት ከራሱ የተደራጀ ሀገር የነበረው በኢትዮጵያ ስር ከሌሎች ጋር በእኩልነትና በፍትሀዊነት የሚገባውን ተከልክሎ የሚገባኝ ይሰጠኝ እያለ እየጮኸ የሚገኘው መደመጥ የለበትም እንዴ❓ አዎ የዎላይታ ህዝብ በደልና ከክብሩ ዝቅ ብለው እየኖሩ ያለበት ሁኔታ ልዩ ያደርገዋል። የህዝብ ትግሉና የሁልጊዜ ሙግት መነሻም ለሌላው ካለው ጥላቻ የመነጨ ሳይሆን በሀገሪቱ ህግ ጥላ ስር የሚገባውን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው።

ወደ ዋናው ነጥቤና ወደ ራሳችን ጉዳይ ለማጠቃለል ሲመለስ፦ በተለይም ሁሉም እያለን በሀሳብ ልዩነት ምክንያት በስልጣን ባሉት እና ከስልጣን በወረዱት ላይ የምናደርገው፣ እርስበርስ ክፍፍል በሚያሰፋ አኳኃን ጠልፎ የመጣል የትግል አካሄድ እነሱን በሚተኩ ግለሰቦች ላይም አሉታዊ ጫና በመፍጠር ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለግላቸውና ለሾመው ፓርቲ ብቻ እንዲያገለግሉ፣ በእርስበርስ ጭቅጭቅና ጥራጥሬ መሀል ሶስተኛ ወገን ጠልፎ እንዲጥል፣ በህዝብ ላይ የተደቀነው ዘርፈብዙ አንገብጋቢ ጉዳዮች በወቅቱ መፍትሔና ትኩረት እንዳያገኙ እንዲሁም ከአካባቢያችን ተተኪና ልምድ ያለው አመራር እንዳይወጣ የሚያደርግ አደገኛ ልምምድ እየፈጠረ ነውና በጊዜ የለንም መንፈስ የትግል አካሄዳችን ከሀገሪቱ ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በተገቢው መመርመርና ማስተካከል ያስፈልጋል ብዬ ይሄ ጉዳይ የሚመለከታቸውን በሙሉ በከበረ ፍቅር እማፀናለሁ።

ስላነበባችሁ አመሰግናለሁ🙏

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ
ካለሁበት ከታላቅ ሰላምታ ጋር🙏
ሰኔ 27/2016 ዓ.ም

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *