ለህብረተሰቡ ችግር ፈቺ ሀሳቦችን በማመንጨት የመፍትሔ አቅጣጫ ማመልከትን አላማው አድርጎ ተመስርቶ የነበረው የዎላይታ ምሁራን ማህበር መጥፋቱ ማሳሰቡን የአከባቢው ተወላጆች ገልጸዋል።

በአከባቢው በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች የሰለጠኑ በርካታ ምሁራን ያለበት በመሆኑ ምሁራን ሙያቸዉን፤ ዕዉቀታቸዉንና ገንዘባቸዉን በማቀናጀት በበጎ የልማት ተግባራት ቢያዉሉ ህዝቡን ስር ከሰደደ ድህነትና ተጋላጭነት በማላቀቅ ረገድ ከፍተኛ ሚና መጫወት እንዲችሉም የምሁራን ማህበር ማቋቋም አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ከአምስት አመት በፊት በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

አንድ በምስረታው ዕለት ተሳታፊ የነበረው ግለሰብ በጉዳዩ ዙሪያ ከዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ጋር በነበረው አጭር ቆይታ እንደገለፁት የማህበሩ መቋቋም ለዎላይታ ብቻ ሳይሆን ለአጎራባች ህዝቦችም ለሚያጋጥሙ ችግሮች የመፍትሄ አቅጣጫዎችን ማመልከት የሚችል መፍትሄ አመንጪ ተቋም ጭምር ይሆናል በሚል ተስፋ ከተለያዩ ቦታዎች በተለያዩ ሙያ ዘርፍ የተሰማሩ የዎላይታ ምሁራን በታሪካዉ ዕለት በዎላይታ ጉታራ አዳራሽ ተገኝተው በጋራ መምከራቸውን አስታውሰዋል።

ለህብረተሰቡ ችግር ፈች የሆኑ ምርምሮችን ለማከሄድ መነሳሳታቸዉንና በየተሰማሩበት የየድርሻቸዉን ለመወጣት ቃል ገብተው ያለፉ ጥፋቶችንና ስህተቶችን ትቶ ለህብረተሰቡ ጥቅም ሲባል በቅንጅት መስራት እንደሚገባ በመተማመን ማህበሩ በሚያተኩርበትና ሁሉንም በሚያሳትፍ አኳኃን ሀገር ወስጥና ከሀገር ውጭም በተለያዩ አለም ሀገራት የሚገኙ የብሄሩ ተወላጅ ምሁራንን የሚያሳትፍ ሥረዎችን እንዲሰሩ ኃላፍነት ተጥሎባቸው የሚመሩ አካላት መመረጣቸውንም ተሳታፊው አስረድተዋል።

በተመሳሳይ መንገድ አንድ የማህበሩ አመራር በመሆን ተመርጠው የነበረውን በጉዳዩ ዙሪያ ለምን ማህበሩ በርካታ የህዝብ አደራ ተሸክሞ አላማውን ማሳካት አልቻለም ብቻ ሳይሆን ሙሉበሙሉ እንቅስቃሴ አቆመ? በሚል ለተጠየቁት “የችግሩ መነሻ ምክያቶች የተለያዩ ቢሆንም ከውስጣችን የሚመነጭ የአንድነት ዕጦትና ለህብረተሰቡ ችግር መፍትሔ ለመሆን የመሰጠት ቁርጠኝነት ባለመኖሩ ነው” ብለዋል።

የማህበሩ አባል አክለውም “ይሄው ዘርፈብዙ ችግር ለገጠመው ህዝብ ችግር ፈቺ መፍትሔ ለማመልከትና ያንንም በዕውቀት ለመፍታት በበርካቶች ተስፋ ተጥሎበት ከየትኛውም ፓለቲካ አመለካከት ልዩነት በታሪካዊ ዕለት የተቋቋመው ማህበር አላማ ወደ ግብ ያልደረሰው በእኛው ድክመት ወደፊት መጓዝ ያልቻለ እንጂ እውነት ለመናገር የሚጠበቅብንን ማድረግ ብንችል ኖሮ አይቆምም ነበር” በሚል በቁጭት ገልፀዋል።

አሁንም ጊዜው አልረፈደም ያሉት ምሁሩና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ የማህበሩ አመራር የነበረው “ወቅቱ ህዝባችን ከመቸውም ጊዜው በላይ በበርካታ ውስብስብ ችግሮች የተጋለጠበትና የእኛን ዕገዛ በሚያስፈልግበት አንገብጋቢ ወቅት ነውና ከያለንበት ያለምንም ፓለቲካ አመለካከት ልዩነትና ሁኔታ ጋር አገናኝተን ሳንወስድ በአስቸኳይ ለአላማው መሳካት መሰብሰብ የሞራል ግዴታም ጭምር ነው” ብለው ለሚመለከታቸው በሙሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ሌላኛው አንድ የማህበሩ አመራር በመሆን ተመርጠው የነበረው ምሁር በጉዳዩ ዙሪያ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሲጠይቅ “የማህበሩ መመስረት በአሁኑ ወቅት በአከበቢዉና በአገርቱ እየመጣ ያለዉን ለዉጥ በአገባቡ ለመጠቀምና በየጊዜዉ ለሚከሰቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፊትሄ ለማበጀት ወሳኝ እርምጃ መሆኑን በማስረዳት ምሁራኑ ከምን አገባኝ ዳር ቆመው ከመመልከት ያስተማራቸውን ማህበረሰብ መልሶ ለማገልገል ቁርጠኝነት ማሳየት ይገባናል” ብለዋል

የዎላይታ ሕዝብ ለረጅም ዘመናት በትርፍ አምራችነት የሚታወቅ ቢሆንም አብላጫዉ የዎላይታ ሕዝብ በተለይም በገጠር የሚኖረዉ ህዝብ በተለይም ከ1977 ዓ/ም ጀምሮ ለዘርፈ፣ ብዙ ድህነት ተዳርጎ ስር የሰደደዉ ድህነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ከመጣዉ የህዝብ ዕድገት፤ ከፍተኛ የህዝብ ጥግግት፣ የመልካም አስተዳደር እና ተገቢና አሳታፊ የልማት ፖሊሲ ዕጥረት ጋር ተደማምሮ ህዝቡን ለዘርፈ ብዙ ተጋላጭ ባደረገበት ወቅት የምሁራን አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደሆነም ምሁሩ ጠቁመዋል።

ህዝብ ከገጠመው ችግር ለማምለጥ እንደ አዉሮፓ አቆጣጠር ከ1960ዎቹ ጀምሮ በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ወጣቶች ሴቶችና አዋቂዎች አከባቢዉን ጥለዉ እንደሚሰደዱና ከእነዚህ ስደተኞች መካከልም አብዛኛዎቹ በዕድሜ ያልበሰሉ ወጣቶችና ሴቶች ከመሆናቸዉ የተነሳ በሄዱበት አከባቢዎች ተገቢ ክፍያ አሊያም አደጋ ባለው ስራ በመሰማራት ከእጅ ወደ አፍ የሆነ ኑሮ እየገፉ እንደሆነ መታዘባቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም ካለፉት ሁለት አስርተ ዓመታት ጀምሮ በርካታ ህጻናት ትምህርት መጀመሪያ ዕድሜያቸው አከባቢዉን ለቀዉ ወደ ተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች እየፈለሱ በሄዱበት አከባቢ የትምህርት ዕድል የማያገኙ ከመሆናቸዉም በላይ ለከፍተኛ የጉልበት ብዝበዛና ሰብአዊ መብት ጥሰት እየተዳረጉ ይገኛሉና “ሁላችንም ከያለንበት ተሰባስበን ለመፍትሄው መረባረብ በአንድነት መመካከር ይገባልም” ብለዋል።

ምሁሩ በማጠቃለያ ሀሳባቸው “በአሁኑ ወቅት የእኛን ጉዳይ ለመፍታት መጀመሪያ ራሳችን ተነስተን የበኩላችንን ሳናደርግ ሌላውን የመተቸት ሞራል የሌለን መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፤ የአንድነት፣ የመቻቻልና በህዝብ ጉዳይ ያለልዩነት በጋራ የመተጋገዝ ጉዞ ለዎላይታ አማራጭ የለለው መፍትሔ፣ ለሀገሪቱም ቁልፍ ምሶሶ በመሆኑ የማህበሩን ዓላማ እና ተልዕኮ በሚገባ የማስፈፀም ብቃትና እውቀት ያለን በሃገር ውስጥና በአለምአቀፍ ደረጃ በተለያዩ ሙያ የሰለጠንን ህዘቡ የእኛ እርዳታ እየጠበቀ ነውና የበኩላችንን ለመወጣት ከልብ መዘጋጀት አለብን” በሚል ተማፅነዋል።

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *