
ከዎላይታ የተወሰዱት አርቲስት ተመስገን ሎሪሶ (ሻንቶ) እና የሙዚቃ አቀናባሪ ፈቃዱ ማንዛ “ሰብዓዊ ክብራቸውን በማይመጥን” ሁኔታ በአርባምንጭ እስርቤት እንደሚገኙ የስራ ባልደረባቸው ገለፀ።
በህዝብ ዘንድ የተለያዩ የጥበብ ስራ በመስራት የሚታወቁ እነኚህ አርቲስቶች የታሰሩት በጋሞ ዞን “የዘይሴ ብሄረሰብ ሙዚቃ በመስራት ህዝብን አነሳስታችኋል” በሚል እንደሆነም ተነግሯል።
መኖሪያቸውን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ሶዶ ከተማ ያደረጉ የሙዚቃ አቀናባሪ ፈቃዱ ማንዛ በወቅቱ በክልሉ ፖሊስ ፓትሮል መኪና የመጡ አካላት ከስቱዲዮ ውስጥ ያለውን ንብረት ጋር እንዲሁም አርቲስት ተመስገን ሎሪሶ (ሻንቶ) በሌላ ቀን ከስራ ቦታ ይዘው መሄዳቸውን አንድ የአይን እማኝ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልጿል።


አርቲስቶቹን በመጀመሪያ ቀናት በዎላይታ ሶዶ ከተማ ፓሊስ ጣቢያ ቢያስገቡም ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ወደ አርባምንጭ ከተማ ዙሪያ ወረዳ እስርቤት በመውሰድ ማሰራቸው ተረጋግጧል።
የድምፃዊና ሙዚቃ አቀናባሪ መታሰር በተመለከተ ወደታሰሩበት ፓሊስ ጣቢያ በመሄድ የጠየቀው አንድ የስራ ባልደረባ ያሉበት ሁኔታ ስገልጽ “እጅግ በሚያሳዝን ሰብዓዊ ክብራቸውን በማይመጥን” ሁኔታ ውስጥ እንዳሉ በመግለፅ ሌሎች ስንቅ ይዘው ለመጠየቅ የሚሄዱትን የማሻማቀቅና የማስፈራራት ሁኔታ መኖሩን መታዘቡን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድቷል።
የታሳሪዎቹ ባልደረባ ስለእስራቸው ሁኔታ ተጠይቆ እንደገለፀው በቅርቡ የዛይሴ ብሄረሰብ የብሄሩን አዲስ አመት ለማክበር ቅድመ ዝግጅት ካደረጉ በኃላ በአከባቢው የፓለቲካ ጫና እና ማንነት ጥቃት መኖሩን ተከትሎ ከአንድ ወር በፊት እንዳይከበር ስለተከለከለው “ዮዌ ሱሩቄ” በመባል ለሚታወቅ በዓል ሙዚቃ ከማቀናበር ጋር በተያያዘ እንደሆነና በአርባምንጭ ዙሪያ ፍርድቤት ቀርበው የዋስትና መብታቸውም ጭምር ተከልክለው በጊዜ ቀጠሮው እስርቤት እንዲቆዩ መደረጉንም አክለው አረጋግጧል።
የሙዚቃ አቀናባሪውና አርቲስቱ በተለይም በአከባቢው እንዲሁም በአጎራባች ህዝቦች ታርክ ባህልና ቋንቋን የሚያሳድጉ ስራዎችን በመስራት ከመታወቅ ባሻገር ምንም አይነት የፓለቲካ ተሳትፎ የለላቸው ስለመሆኑም የስራ ባልደረባቸው መስክሯል።


በተጨማሪ በጉዳዩ ዙሪያ አንድ የዘይሴ ብሄረሰብ አባልን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ስጠይቅ “የአርቲስቶቹ መታሰር እኛ ለዘመናት በማንነታችን ምክንያት እያየን ያለነው መከራን በጥቂቱ በግልጽ በአደባባይ የገለጠ ነውርና ሁሉም ሰው ሊያወግዘው የሚገባ ህገወጥና የአምባገነኖች ተግባር ነው” በሚል ሁኔታውን በአጭሩ ገልፀዋል።

“በሰላማዊ መንገድ በዚህ ዘመን ሰው የራሱ ማንነት ይከበር ስላለ ብቻ እንዴት ስቃይና መከራ ይደርሳል?!” በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም “በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታችን ባልተወከለበት መብታችን በማፈን እንዲሁም ይባስ ብለው የዘይሴ ብሄረሰብ ሙዚቃ የሰሩ በማለት የሌላ ብሄር አርቲስቶችን ጭምር አፍነው ማሰር ተስፋችንን አጨልሞታል፤ መንግስት ካለ ሊሰማን ይገባል” ስልም ሁኔታውን በምሬት አስረድተዋል።
የብሄረሰቡ አባሉ በማጠቃለያ ሀሳብ ላይ “በተለይም በጋሞ ዞን ለዘመናት ማንነታቸው ታፍነው የሚገኙ የራሳቸው ማንነት ያላቸው ብሄረሰቦች መዋቅር ጥያቄ በክልሉ ብሄረሰቦች ምክርቤት ስብሰባ ላይ ይመለሳል ብለን ተስፋ ቢናደርግም በተቃራኒው አሁንም የህዝብ ጥያቄዎችን በህጋዊ መንገድ ያነሱ አመራሮችንና የመብት ተሟጋቾች ከኃላፊነት በሴራ ማንሳት፣ የተለያዩ ስም በመስጠት ማሳሰር፣ ከስራ ማፈናቀል እንደቀጠለ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም በተለያዩ መንገዶች የህዝብ ጥያቄ እንዲኮላሽ በማድረግ ከህዝብ ማንነት ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም ውግንና ያደረጉ ቡድኖች እንደወትሮው ተመሳሳይ በደል እንዲቀጥሉ መፍቀድ ባሻገር በአከባቢው አለመረጋጋት እንዳይኖር በማድረግ የማንነት ጥያቄ ለዘመናት ሲያነሱ የነበሩ ብሄረሰቦች ራስን በራስ የማስተዳደር መብት አለማክበሩ ሀገራችን የምትከተለውን ህግ ያላከበረ ፀረ ፌደራሊዝም በሆኑ ሰዎች አስተሳሰብና ሴራ ተላልፎ መሰጠቱ ተገቢ ባለመሆኑ የፈደራል መንግስት ጠልቃ እንዲገባ በፈጣሪና በተጨቆኑ ህዝብ ስም እጠይቃለሁ” በሚል ጥሪ አቅርበዋል።