
በኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ግጭትና ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እልባት እንዲያገኝ የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ ጥሪ አቅርቧል።
ኦፌኮ በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ባስተላለፈው ጥሪ “አገራዊ ችግሮች በአንድ ገዢ ፓርቲ ብቻ የሚፈታ ባለመሆኑ ሁሉም ተፋላሚ አካላትን ጭምር የሚያካትት አገራዊ ምክክር እንዲደረግ” ሲል ጠይቋል፡፡
ፓርቲው በአሁኑ ወቅት የአገሪቱ ጊዜያዊ ሁኔታን ገመገምኩ ብሎ ባወጣው መግለጫ ህገመንግስቱን የሚጻረሩ ያሏቸው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች፣ በሚካሄደው ጦርነትም የጅምላ ግድያዎች እና እስር ብሎም የቤቶች ቃጠሎ ድርጊቶች፣ ስርዓታዊ ሙስና መንሰራፋቱንና ከጦርነቱ የተነሳ በተዛባው የጤና ስርዓት ተላላፊ በሽታዎች መስፋፋታቸውን፤ ብሎም የስራ አጥነትና የኑሮ ውድነት አሳሳቢ ደረጃ መድረሱን ገልጿል።
የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግሬስ በመግለጫው ጨምረውም በኢትዮጵያ ውስጥ የተስፋፋው ግጭትና ጦርነት በሰላማዊ መንገድ ብቻ እልባት እንዲያገኝ ገዢው ፓርቲ ብቻ ሳይሆን ሁሉም ተፋላሚ አካላትን ጭምር የሚያካትት ሀገራዊ ምክክር መደረግ እንዳለበትም ጥሪ አቅርቧል። Wolaita Times