
በዎላይታ ዞን ከህብረተሰቡ እውቅና ውጪ ጥቅጥቅ ደን “ለመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ክፊያ” በሚል ሰበብ ወረዳው ለግለሰብ መሸጡ ቅሬታ አስነሳ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በዎላይታ ዞን ሶዶ ዙሪያ ወረዳ ዝጋ ቦርኮሼ ቀበሌ ውስጥ ህብረተሰቡ እስካሁን ጠብቆ ተንከባክበው ያቆየው እንዲሁም የህብረተሰቡ ሀብት የሆነውን ጥቅጥቅ ደን “ለወረዳው መንግስት ሠራተኞች ደመወዝ እንከፍላለን” በማለት የወረዳው አመራሮች ለአንድ ባለሀብት መሸጣቸውን ከስፍራው ነዋሪዎች ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
እንደ ነዋሪዎቹ መረጃ ከሆነ ይሄንን ህብረተሰቡ ለዘመናት ጠብቀው ያቆየውን ደን በህገወጥ መንገድ ለመጨፍጨፍና ለግል ጥቅማቸው ከአሰራር ውጪ ለግለሰብ እንዲሸጥ የተወሰነው የአከባቢው ህብረተሰብ ስለጉዳዩ ምንም ሳያውቅ ጥቂት ከቀበሌው አስተዳደርና የወረደው አመራሮች ጋር በመመሳጠር እንደሆነ አስረድተዋል።

“በዚያ መንገድ በድብቅ የተሸጠው ደን እንደተባለው “ለመንግሥት ሰራተኞች ደመወዝ ክፊያ” አለመዋሉን ከአከባቢው በተመረጡ ተወካዮች አማካይነት መረጋገጡን የጠቀሰው የመረጃ ምንጫችን አቤቱታቸውንም ለሚመለከታቸው አካላት ማቅረባቸውን ጠቁመዋል።
የህብረተሰቡ የጋራ ሀብት የሆነው ይሄው ጥቅጥቅ ደን በህጋዊ መንገድ ይሸጥ ቢባል እንኳን በበርካታ ሚሊዮን ገንዘብ ተሸጦ ለአከባቢው ልማት መዋል የሚችለውን ሆን ብለው የቀበሌውና የወረዳው አመራሮች በምስጢር በመመሳጠር በእጅአዙር ትርፍ ለማግኘት በ2 ሚሊዮን ብቻ በህገወጥ መንገድ ያለምንም ጨረታ ለግለሰብ መሸጣቸውንም አስረድተዋል።
በህገወጥ መንገድ ደኑን የገዛው ባለሀብት ግለሰብ ለመቁረጥ ወደ ቦታው መኪና ይዞ በመጣበት ወቅት በአከባቢው ነዋሪዎች ዘንድ ከፍተኛ ቁጣ ተነስተው ወዲያው እንዲባረር መደረጉንም አክለዋል።
ጉዳዩን በተመለከተ ከአከባቢው ነዋሪዎች የተመረጡ ተወካዮች አቤቱታ በፅሁፍና በአካል ለዎላይታ ዞን አካባቢና ደን ጥበቃ ፅህፈት ቤት ሄደው ቢያመለክቱም ኃላፊው ለማናገር ፈቃደኝነት አለማሳየታቸውን ተከትሎ በአሁኑ ወቅት አቤቱታቸውን እስከ ክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ቢሮ ድረስ በመሄድ በማመልከት ምላሽ እየተጠባበቁ እንደሆነም አረጋግጠዋል።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ ህብረተሰቡ ባነሳው ቅሬታ ዙሪያ ከሚመለከታቸው አካላት ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ለጊዜው ያልተሳካ ቢሆንም መረጃውን ካገኘ ይመለስበታል።
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው