1000013132

አቶ ታገሰ ጫፎ፣ ዶክተር ተስፋዬ በልጅጌ ጨምረው ሌሎች ከፍተኛ የፌዴራል መንግስት የስራ ኃላፊዎች በገዜ ጎፋ ወረዳ በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናኑ

የፌደራል፣ የክልሉ መንግስትና የአካባቢው ነዋሪዎች በአሁኑ ሰዓት የነፍስ አድንና ተጨማሪ አደጋ እንዳይከሰት ማድረግ የሚያስችሉ ተግባራትን በርብርብ እያከናወኑ እንደሚገኝ ተገልጿል።

በትላንትናው አደጋ የሟቾች ቁጥር አሃዛዊ መረጃው እኛ ከተገለፀው በላይ እየጨመረ ሲሆን እስከ ዛሬ ጠዋት ድረስ የ267 ሰዎች አስከሬን ተገኝቷል አሁንም የጠፉ ሰዎች ስላሉ የአስከሬን ማውጣቱ ስራ እንደቀጠለ ነው ሲሉ ገልጸዋል::

ትላንት ከፌደራል የመጡ ሶስት የቀይ መስቀል መኪኖች እህል እና አልባሳት ወደ ስፍራው አጓጉዘው ነበር ያሉት ባለሙያው አክለውም አጎራቦች ከሆኑ አከባቢዎች እርዳታዎች እየተደረጉ እንደሆነ ገልጸዋል::

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን በደረሰው አደጋ 400 የሚሆኑ ዜጎች መፈናቀላቸውን የአደጋ ስጋት አመራር ኮሚሽነር አምባሳደር ሽፈራው ተክለማርያም (ዶ/ር) በዛሬው ዕለት ለመገናኛ ብዙሀን በሰጡት መግለጫ ጉዳት ለደረሰባቸውና ለተፈናቀሉ ዜጎች የሚያስፈልጋቸውን ምግብ እና ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶች ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑን ገልጸዋል::

በተከሰተው አደጋ በርካታ አካላት ሃዘናቸውን እየገለጹ የሚገኝ ሲሆን የኢፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ “በደረሰው አስከፊ ጉዳት የተሰማኝን ጥልቅ ሀዘን እገልጻለሁ። አደጋውን ተከትሎ የፌዴራል የአደጋ መከላከል ግብረ-ሀይል በአካባቢው ተሰማርቶ የአደጋውን ጉዳት ለመቀነስ ርብርብ እያደረገ ነው” ሲሉ ገልፀዋል::

በኢትዮጵያ የአሜሪካ ኤምባሲ በበኩሉ “ከ200 በላይ ሰዎችን ህይወት በቀጠፈው የመሬት መደርመስ አደጋ እጅግ አዝነናል።” ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ላይ ባሰፈረው መልዕክት ያስታወቀ ሲሆን ኤምባሲው አክሎም የአሜሪካ መንግስት በዩኤስ ኤአይዲ በኩል ካሉ የሰብአዊ እርዳታ አጋሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ ሁኔታውን በቅርበት እየተከታተለ መሆኑን አስታውቋል::

በተጨማሪም ኢትዮ ቴሌኮም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጎፋ ዞን አደጋ መከላከልና ዝግጁነት ጋር በመተባበር በጎፋ ዞን በደረሰዉ ድንገተኛ የመሬት ናዳ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖች ድጋፍ ማሰባሰቢያ አጭር የመልዕክት ቁጥር ይፋ አድርጎ ዜጎች ወደ 8091 የፈለጉትን የብር መጠን በመላክ ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መደገፍ እንደሚችሉ አስታውቋል።

የተለያዩ የፌዴራል እና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች በስፍራው በመገኘት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች አጽናኑ ሲሆን በአደጋው የተጎዱ ዜጎችን ለማገዝ በማህበራዊ ሚዲያ ገንዘብ ማሰባሰብ እንቅስቃሴ በስፋት እየተከናወነ የሚገኝ ሲሆን በርካታ ወገኖችም ለችግሩ ልዩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ላይ መሆናቸው ተገልጿል። Wolaita Times