
በጎፋ ዞን በደረሰው የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል የመንግስታቱ ድርጅት አስታወቀ።
በሌላ በኩል ለተጎዱ ወገኖች መፅናኛ እና ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ስፍራው በማቅናት እንዲሁም በተጠቀሰው ድጋፍ አካውንት ገንዘብ በማስገባት አጋርነታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ በተከሰተው የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያስታወቀ ሲሆን እስከ ትላንት ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 ድረስ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 257 ማሻቀቡን ድርጅቱ ገልጿል።

የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ዛሬ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርት፤ በመሬት ናዳው ከሞቱት በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው 12 ሰዎች በሳውላ ሆስፒታል ህክምና በማግኘት ላይ ይገኛሉ። በአደጋው ቢያንስ 125 ሰዎች መፈናቀላቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ማህበረሰብ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁሟል።
OCHA በዛሬው ሪፖርቱ፤ ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጡ የሚችሉ 15,515 ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከአካባቢው እንዲለቅቁ ሊደረግ እንደሚገባ በማሳሰብ የፌደራል መንግስት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከጎፋ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር፤ ነዋሪዎቹን ወደሌሎች ቦታዎች ለማዘዋወር የሚያስችለውን እቅድ በማጠናቀቅ ላይ መሆናችውን ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
በሌላ በኩል የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶክተር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ እና ልኡካኑ ለተጎጂዎች የተለያዩ ሰብዓዊ እርዳታ ያደረጉ ሲሆን በአደጋው ህይወታቸውን ላጡ ወገኖችና ለተጎጂዎች በመጀመሪያ ዙር በጥሬ ገንዘብ 5 ሚሊዮን ብር እና በዓይነት 1.5 ሚሊዮን በላይ በዓይነት በቦታው ተገኝተው ድጋፍ አድርገዋል።

በተጨማሪም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን በገዜ ጎፋ ወረዳ ኬቾ ቀበሌ ባጋጠመ የመሬት መንሸራተት አደጋ ለተጎዱ ወገኖች የሚሆን የመጀመሪያ ዙር ከ45 ሚሊዮን ብር በላይ የገንዘብ እና ቁሳቁስ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ቦታው መላኩን አስታውቀዋል። Wolaita Times