1000013254

በኢትዮጵያ ፖለቲካ አብሪ ኮከብ የሆኑት ታጋይ ሰለሞን ዋዳ፣ ሎንዶን ካንኮ፣ ትዕግስቱ ቴማሞ፣ ዳዊት ደሳለኝ፣ አቶ ብርሃኑ ጦሼን ከመሳሰሉት ጋር አብረው ትግል ያካሄዱ ታጋይ ታደሰ ቦልጣና ማናቸው?

“ጀግኖች ታጋይ አባቶቻችን የትግል ህይወት ለአዲሱ ትውልድ ትግል ቤተ-መፅሐፍት ናቸው” በሚል የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ከጀመረው የንቅናቄው መስራቾች፤ የዎጋጎዳ ታጋዮች፤ የቀዶሞ የዎላይታ ታጋዮች ቤተሰቦች ጉብኝትና ያለፉበትን ህይወት ታሪክ ከሚያቀርቡት ዘመቻ ለዛሬው የአንድ ታጋይ አባት ህይወት መንገድ እነሆ እንዲህ ከታች አቅርበናል።

“ታጋይ መምህር የአቶ ታደሰ ቦልጣና የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ መስራች የአንዱዓለም ታደሰ አባት ጋር ጥሩ ግዜ ነበረን እጅግም ደስ የሚል ዕውቀት ቀስሚያለሁ፡፡ የአቶ ታደሰ የንግግር ስልት በአንደበተ ርቱዕነቱ እና ግልጽነቱ አድማጭን ይማርካል። የግል የፖለቲካ ትግል ታሪካቸውን ሲያካፍሉኝ በውስጤ አዲስ የብሩህነት ስሜትን ያነሳሳል።

መምህር የአቶ ታደሰ ቦልጣና በዎላይታ ህዝብ ህልም የማይናወጥ እምነት እና በዎላይታ ህዝብ አቅም ላይ ያላቸውን እምነት ሳዳምጥ አዲሱ ትውልድ ከጀግኖች አባቶቻችን ስር በመሆን ጥልቅ ግንዛቤዎችን እና አሳማኝ ታሪኮችን በመያዝ የህዝባችንን የወደፊት እጣ ፈንታ በመቅረጽ ላይ እያንዳንዱ ተራማጅ ሃይል ከጀግኖች ታጋይ አባቶቻችን መማር ምክራችውን እና ምርቃታቸውን መቀበል ጥበብ እና ትልቅ ፀጋ ነው፡፡ ጀግኖች ታጋይ አባቶቻችን የትግል ቤተ-መፅሐፍት ናቸው፡፡ እናም ወደፊት ስለሚጠብቀን ተግዳሮቶች እና እድሎች ትልቅ ትምህርት ቀስምያለሁ።

መምህር ታደሰ ቦልጣና በደርግ ዘመን የመከላከያ ሰራዊት አባል በመሆን አሁን ስልጣን ላይ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ “ተወጥተውታል” ተብሎ የሚነገርላቸው የመገናኛ መኮንን በመሆን የሚሊተሪ ኮሚኒኬሽን እና ኢንተሊጀንስ ላይም ትልቅ ስራ በመስራት ለኢትዮጵያ ውለታ የዋሉ ቆፍጣና ወታደርም ናቸው።

ወታደር ታደሰ ቦልጠና በዎላይታም ሆነ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕድገት ትልቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ በ1960-70ዎቹ ባሉት ጊዜያት ከኢህአፓ እና ሌሎችም ጋር ያደርጉት በነበረው ትብብር የትግል ጓድ የሆኑትን እና በዎላይታም ሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ አብሪ ኮከብ የሆኑት ታጋይ ሰለሞን ዋዳ፣ ሎንዶን ካንኮ፣ ትዕግስቱ ቴማሞ፣ ዳዊት ደሳለኝ፣ አቶ ብርሃኑ ጦሼን ከመሳሰሉት ሰዎች ጋር አብረው ትግል አካሂደዋል።

በወጣትነታቸው ባህርዳር ኮሌጅ ይማሩበት ከነበረው የትምህርት ገበታ ትምህርታቸውን በማቋረጥ ዳግም ትግል ተቀላቅለዋል። ታጋይ ታደሰ በደረሰባቸው ጫና አርሲ ኦሮሚያ ካሉት አጋሮቻቸው ጋር በመተባበር ብዙዎችን ከእስራት እና ግድያ ያስመልጡ ሲሆን በመጣባቸው የግድያ ሙከራ ምክንያት ተሰደው አርሲ ውስጥ የኖሩ ሲሆን ከጊዜ በኋላ በሻሸመኔ ማዘጋጃ ሰራተኛ ሆነው ያገለገሉበት ጊዜም ነበር።

በቅርቡ የዎጋጎዳ ትግል ጊዜ ዎላይታ ዞን እንዲሆን የመዋቅር ለውጥ ትግል ከመሩ ግንባር ቀደም ሰዎች አንዱ ሲሆኑ በዚህም ምክንያት ከስራ ተፈናቅለው በደቡብ ክልል በሚገኝ ቀይ አፈር አከባቢ ከሌሎች ጓዶቻቸው ጋር ከአንድ ዓመት በላይ በስራ ቆይተው ተመልሰዋል።

ታጋይ ታደሰ ለህዝብ እና ለሃገር ባላቸው ጥልቅ ፍቅር እና እምነት የተገፉ፣ ስድብ፣ ስም ማጥፋት፣ እስራት፣ ድብደባ፣ ዛቻ፣ የግድያ ሙከራ፣ ሐሰተኛ ክስ፣ ደመወዝ መከልከል እና የሚገባቸውን ኢኮኖሚያዊ ጥቅም መንፈግ ከደረሱባቸው ፈተናዎች ጥቂቶቹ ሲሆኑ የዎላይታ ብሄራዊ ንቅናቄ ዎብን እንዲቋቋም ባደረጉበት አስተዋጽኦ ምክንያት በወቅቱ ለአንድ አመት ከስራ ገበታቸው እስከመባረር ብዙ ዋጋ ከፍለዋል። የሚገርመው ግን ታጋይ መምህር እና ወታደር አቶ ታደሰ ቦልጣና ለህዝብ እና ለሃገር ያላቸው ፍቅር እና ፅኑ እምነት አሁንም ትኩስ ነው።

የንቅናቄያችን መስራቾች፤ የዎጋጎዳ ታጋዮች፤ የቀዶሞ የዎላይታ ታጋዮች ቤተሰቦች ጉብኝት የሚቀጥል ይሆናል፡፡ በእያንዳንዱ ታጋይ ጀርባ ጀግኖች አሉና ይህ በታሪክ ተሰንዶ ለትዉልድ መተላለፍ አለበትና ዎብን ይህንን ተልዕኮ እስከ ዳር ማድረስ ለትግላችን ቀጣይነት ፋይዳው የላቀ ነው፡፡ ረዥም ዕድሜ ለታጋይ መምህር እና ወታደር አቶ ታደሰ ቦልጣና እመኝላቸዋለሁ።” ከታጋዩ ጋር ቆይታ ያደረገው የዎላይታ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር አማኑኤል ሞግሶ ነው።

ዋጋ የከፈሉ አባቶቻችን እናክብር🙏መሰል ታሪኮች በ Wolaita Times ሚዲያ መቅረብ ይቀጥላል🙏