
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በጎፋ ዞን ገዜ ወረዳ የደረሰውን የመሬት መንሸራተት አደጋ ተከትሎ ሕይወታቸው ላለፉ ዜጎች የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከነገ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚቆይ ብሔራዊ ሐዘን አውጇል።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ጎፋ ዞን፣ ገዜ ጎፋ ወረዳ ባለፈው ሰኞ በተከሰተው የመሬት ናዳ የሞቱ ሰዎች ቁጥር 500 ሊደርስ እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት (ተመድ) ያስታወቀ ሲሆን እስከ ረቡዕ ሐምሌ 17፤ 2016 ድረስ የሟቾቹ ቁጥር ወደ 257 ማሻቀቡን ድርጅቱ መግለፁ ይታወሳል።
የተመድ የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (OCHA) ዛሬ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርት፤ በመሬት ናዳው ከሞቱት በተጨማሪ ጉዳት የደረሰባቸው 12 ሰዎች በሳውላ ሆስፒታል ህክምና በማግኘት ላይ ሲሆኑ በአደጋው ቢያንስ 125 ሰዎች መፈናቀላቸውን ያመለከተው ሪፖርቱ፤ ነዋሪዎቹ በአሁኑ ወቅት በአካባቢው ማህበረሰብ ተጠልለው እንደሚገኙ ጠቁሟል።
OCHA በዛሬው ሪፖርቱ፤ ለተጨማሪ የመሬት መንሸራተት አደጋ በከፍተኛ ሁኔታ ሊጋለጡ የሚችሉ 15,515 ነዋሪዎች በአፋጣኝ ከአካባቢው እንዲለቅቁ ሊደረግ እንደሚገባ በማሳሰብ የፌደራል መንግስት፣ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እና ከጎፋ ዞን አስተዳደር ጋር በመተባበር፤ ነዋሪዎቹን ወደሌሎች ቦታዎች ለማዘዋወር የሚያስችለውን እቅድ በማጠናቀቅ ላይ መሆናችውን ጽህፈት ቤቱ ጨምሮ ገልጿል።
በሌላ በኩል ለተጎዱ ወገኖች መፅናኛ እና ድጋፍ ለማድረግ የተለያዩ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችና የህብረተሰብ ክፍሎች ወደ ስፍራው በማቅናት እንዲሁም በተጠቀሰው ድጋፍ አካውንት ገንዘብ በማስገባት አጋርነታቸውን በማሳየት ላይ ይገኛሉ። Wolaita Times