
ለዎላይታ ሕዝብ ነጻነትና መብት ያለስስት ታግለው ዎጋጎዳ እንዲቀለበስ የበኩላቸውን ሚና የተጫወቱ መምህር ተስፋዬ ላንጋና ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
የዎላይታ ህዝብ ማንነት ለማጥፋት የፀደቀውን “ዎጋጎዳ” የተባለ ቀንበር ከትግል ጓደኞቻቸው ጋር በመሆን መላውን ህዝብ በማስተባበር እንዲቀለበስ በማድረግ ከፍተኛ ሚና ተጫውተው የነበሩ አርበኛ፣ ምሁሩ መምህር፣ የፖለቲካ ተንታኝ፣ መምህር ተስፋዬ ላንጋና ባጋጠማቸው ድንገተኛ ሕመም በሕክምና ስረዱ ቆይተው በዛሬው ዕለት ረፋድ አርፈዋል።
መምህር ተስፋዬ በተለይም በሀገራችን ኢትዮጵያ የህዝብ ትግል በወታደራዊ ጁንታ ከተቀማ በኋላ ከተፈጠሩ ፀረ ደርግ ድርጅቶች አንዱ በሆነው በ”ኢህአፓ” ውስጥ ትልቅ ስምና ዝና ከነበረው ጋር በተያያዘ በደረሰበት ድብደባና እንግልት በአካሉ ላይ ጭምር ጉዳት እስኪደርስ ድረስ ለህዝብ መታገሉን በቅርበት የሚያውቃቸው ይመሰክራሉ።
በኋላም በ1980ዎቹ መጀመሪያ በሃገራችን በነበረው የብዙሃን ፓርቲ ሥርዓት ልምምድ ወቅት የዎላይታ ህዝብ ዴሞክራሲዊ ግንበር መስራቾች አንዱ እንደነበር ይነገርላቸዋል።
“የዎላይታ ህዝብ እንደሌሎች በሀገሪቱ ውስጥ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ ተከብሮ እኩል ተደማጭነት እንዲኖረው የታገለ፣ በዎላይታ ህዝብ ዘንድ “የዎጋጎዳ” ትግል በመባል የሚታወቀውን እንቅስቃሴ ከሌሎች የትግል ጓዶቹ ጋር በመሆን ፊት ለፊት የመራ፣ በዚህም ምክንያት ለበርካታ ወራት አለአግባብ የታሠረና የተንገላታ፣ ለህዝብ መብት መከበር ባደረጋቸው እንቅስቃሴዎች በፓለቲካ አመለካከቱ ምክንያት ብቻ አብዛኛውን ጊዜ አለአግባብ በማረሚያ ቤት ያሳለፈ ከውልደቱ እስከ ዕረፍቱ በፓለቲካ ትግል ውስጥ ያለፈ የትግል መሀንዲስ ነገር ግን ብዙ ያልተዘመረለት ጀግና” በሚልም የቅርብ ጓደኞቻቸው ጥልቅ ሀዘናቸውን ገልጸዋል።
ታጋዩ ባለትዳርና ሴት እና ወንድ ልጆቹንም ወልደው ለወግ ማዕረግ ያደረሱ በአከባቢው ማህበረሰብ ዘንድ እጅግ በጣም ተወዳጅ፣ ተግባቢና አስታራቂ በመሆን የሚታወቁ ሲሆን በተጨማሪ በህዝብ ጥቅምና ክብር ጉዳይ ላይ ተቆርቋሪ እንደነበሩም ከቅርብ ወዳጆቹ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በታጋይ ተስፋዬ ሞት የተሰማንን ጥልቅ ሐዘን እየገለጽን ለቤተሰብ፣ ወዳጅ ዘመዶቻቸው እንዲሁም ለመላው ዎላይታ ህዝብ መጽናናትን እንመኛለን🙏