
ከቀበሌ ልቀመንበርነት ወረድኩ ተብሎ በጥላቻ ለተቃውሞ በሚወጣበት ሀገር ጠቅላይ ሚኒስትርነት የመሠለ ስልጣን በክብር አሳልፎ ሰጥቶ ዛሬም የሀገራችን ዕድገት በሚገኝበት ሁሉ ከፊት ናቸው🙏

እንደ ቀና አስተሳሰቦዎ ሁሉም ነገር ተስተካክሎ🇪🇹 ሀገሪቷ በሰላምና በዕድገት ጎዳና ከፍ ብላ ስትታይ ማየት የበረሰካቶች እርሶዎ ምኞት ነው🙏🙏

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ ሲታወሱ 👇
የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር ከመሆናቸው በፊት ከዩኒቨርስቲ መምህርነት እስከ ከፍተኛ አመራርነት ከአንዱ ወደሌላኛው ኃላፊነት ባላቸው በስራ ልምድና ክህሎት እንዲሁም ፍፁም ሌብነትን በመፀየፍ በማገልገል እየተሸጋገሩ አሁንም ያለስስት በተለያዩ አለምአቀፍ ተቋማት የአመራርነት ሚና እየተጫወቱ የሚገኙት አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ድንገት ወይንም በአጋጣሚ ጠቅላይ ሚኒስትር የሆነ የሚመስላቸዉ፣ አንዳንድ በብሄረተኝነት ተውጠው ኢትዮጵያዊነት ሲያሳድግ (ሲቀርጽ) የበደላቸዉ የዋህ ወገኖቻችንና የሐገሪቱን ችግሮች በባዶ አዕምሮአቸዉ ተሸክመዉ እነሆ መፍትሔ እያሉ ችግር ላይ ችግር የሚደርቡ የተወሰነ ጭብጥ እንዲያገኙ ይህቺ በአጭሩ የታሪክ ዳራ የዳሰሰች ፅሁፍ አስፈልጓል።
አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ከማንሳታችን በፊት እርሳቸዉን ያፈራዉን ብሄር ዎላይታን ፖለቲካዊ ታሪክ ከእርሳቸዉ የሁዋላ ታሪክ ጋር በጥቂቱ መዳሰስ ያስፈልጋል። የዎላይታ ሕዝብ የኢትዮጵያ ኢምፓየር አካል የሆነዉ፣ ከአስደናቂ የሰባት ዓመት ትንቅንቅና ተጋድሎ በሁዋላ ሐገሩ ፈርሶበት መሆኑ መሠመር አለበት።
በአፀ ሚኒሊክ መሪነት ከሚመራዉ የኢትዮጵያ ጦርና በንጉስ ጦና በሚመራዉ የዎላይታ ጦር መሐከል ከተካሄዱ ሰባት አሰቃቂ ጦርነቶች ስድስቱ ላይ ጦናና ሕዝባዊ ጦሩ፣ በአሸናፊነት በማጠናቀቅ ሐገርነቱን አስጠብቆ መቆየቱ በታሪክ ይታወቃል። ከሰባተኛዉ ወረራና ጭፍጨፋ ማለፍ ባይችልም።
እንግዲህ በዚህ መንገድ ወደ ኢምፓየሩ የተቀላቀለዉ ሕዝብ ከአዉዳሚ የሰባት ዓመት ጦርነት በሁዋላ፣ የጠበቀዉ ከጦርነቱ ጠባሳ ሊያገግም ይቅርና ጦርነቱ የቀጠለ የሚመስል ሁኔታ ነበርና። ለዛም ይመስላል ከምርኮ መልስ በተሰጠዉ ስልጣን ተጠቅሞ ራሱ ንጉስ ጦና መልሶ ያመጸዉ፣ ብዙ ባይሳካለትም።
በአድዋ ጦርነት ወቅት ከዎላይታ የዘመተዉን ጦር ከመሩት ጦር መሪዎች አንዱ ነው የሚባለዉ ሐጤሮ ሐንቼ ከብዙ ትልልቅ የዎላይታ ሰዎች ጋር በድጋሚ ሌላ አመጽ ካቀነባበረ በሁዋላ፣ አመጹ የታቀደበት ቀን ሳይደርስ በአጋጣሚ ብቻዉን በወሰደዉ እርምጃ ብዙ ዉጤት ሳያመጣ ከሽፎበት በአሰቃቂ ሁኔታ ለመሞት የተገደደዉ። እንደዉም ፊታውራሪ ገነሜ የተባለ በሚኒሊክ ዎላይታን እንዲገዛ የተሾመ ሰው ወደ ሰገሌ ጦርነት መሄዱን ተከትሎ ሕዝቡ አመጽ በመቀስቀሱ ከፍተኛ ቅጣት ደርሶበታል ።
የዎላይታ ሕዝብ ልጅ ኢያሱ ስልጣን ከሚኒሊክ ሲረከብ ጭቆና በዝቶብናልና መጥተህ ጎብኘን ብሎ መልዕክተኛ የላከና መልዕክቱም ተቀባይነት ያገኘለት ሕዝብ ነው፣ ጉብኝቱ ባይሳካም።
እናም ይህን ለመብቱና ለነጻነቱ ካለዉ ቀናኢነት የተነሳ ለበዝባዥ ሥርዓቶች የማይመቸዉን ሕዝብ ከመአከል ርቆ እንዲያስተዳድር የተወሰነበትና በአሜሪካ ሐገር ትምህርት ተከታትሎ የመጣዉ ተራማጁ ገርማሜ ነዋይ በዎላይታም ሆነ በኢትዮጵያ የለኮሰዉን የለዉጥ ችቦ የምንቃኝ ይሆናል።
ገርማሜ ነዋይን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ከኃይለማሪያም ደሳለኝ ጋር ምን ያገናኘዋል❓
ተራማጁ ምሁር ገርማሜ ነዋይ የዎላይታ አዉራጃ አስተዳዳሪ ተደርጎ በአጼ ኃይለስላሴ መመደቡ በግፈኛ አገዛዝ ለሚማቅቀዉ የዎላይታ ሕዝብ መልካም እድል ነበረ። ገርማሜ በዎላይታ አዉራጃ ለዉጥ ለማምጣት ከግፈኛ መልከኞች ጋር የሚያደርገዉ ትንቅንቅ በንጉሱ አልተወደደምና ወደ ሌላኛዉ የባሰ ጠረፍ ኦጋዴን እንዲመደብ የተደረገ ቢሆንም እሱ ከዎላይታ ልጆች ጋር የማይበጠስ ትስስር ፈጥሮ ነበርና ለለዉጥ ሕልሙ ተግባራዊነት እሳት ፊት መቆም ሲኖርበት እርዳታቸዉ አስፈልጎታል።
የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ መሪ የነበሩ ወቅት ለበዓል ከባለቤታቸው ጋር በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተጋብዘዉ በነበራቸዉ ቆይታ እንደሚከተለዉ ይላሉ የአባታቸዉን ታሪክ ሲያወሩ “አባቴ በትምህርት በጣም በጣም ጎቦዝ ነበር። በነሱ ጊዜ በዎላይታ አካባቢ እስከስምንተኛ ክፍል ብቻ ነበር ትምህርት የነበረዉ። እና ተፈሪ መኮንን ነው እስከ አስራ አንደኛ የተማረዉ።
የ53ቱ የነገርማሜ ብጥብጥ ተሳታፊ ስለነበረ ነው ትምህርቱን አቋዋርጦ ገጠር የገባዉ። አባቴ ሸሽቶ ነው ገጠር የገባዉ፣ ትምህርቱን አልጨረሰም። ሸሽቶ ገጠር ገብቶ …ገርማሜ ነዋይ የዎላይታ አዉራጃ አስተዳዳሪ ነበር እና ከእነዚህ ከዎላይታ ከመጡ ሐይስኩል ከሚማሩ ጋር ኔትዎርክ ፈጥሮ ነበር። ይሄ ነገር ሲነቃና የእነ ገርማሜው ሲከሽፍ አባቴና ጓዋደኞቹ መሸሽ ነበረባቸዉ። ሸሽቶ ገበሬ መስሎ ገጠር ገባ።” ኃይለማሪያም ደሳለኝ
በመፈንቅለ መንግሥት ሙከራዉ የተሳተፉና ያመለጡ የዎላይታ ተማሪዎች ጉዳይ አንደኛ ጀግንነት ሲሆን፣ ሁለተኛ በወቅቱ ስዩመ እግዚአብሔር ነኝ የሚለዉን አስከፊ ንጉሳዊ ሥርዓት ለመገርሰስ ከተራማጅ ኃይሎች ጋር ተሰልፎ መንቀሳቀስ ቀድሞ መንቃትን ያመለክታል።
በወቅቱ በቁጥጥር ስር ዉሎ ተገድዶ በረዲዮ ለሕዝብ መልዕክት ያስተላለፈዉ ልዑል አልጋ ወራሸ አስፋወሰን እንደሚከተለዉ ብሎ ነበር ፣ ለተማሩ ወጣቶች ተሳትፎም ጭምር እዉቅና የሚሰጥ ንግግር ያቀረበዉ“ የኢትዮጵያ ህዝብ ከ3000 አመታት በላይ የሚታወቅ ታሪክ አለው።
VOA ኃይለማርያም ደሳለኝ ከ2010 ጀምሮ የዉጪ ጉዳይ ሚኒስትር እንደነበሩ ጠቅሶ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆኑ በወቅቱ ለተወሰኑ ዓመታት አብሯቸዉ የሰራዉን የአቶ ጌታቸው ረዳን ምስክርነት አቅርቦ “ኃይለማርያም የጥሩ ስብዕና ክህሎት ያለዉ መሪ ነው። በጣም ትሁትና፣ ከሰዎች ጋር ወዳጅነት መፍጠር የሚችል ሰዉ ነው። ከየትኛውም ሰዉ፣ ምናልባትም ከሳቸው በታች ካለ ሰዉም ቢሆን ትምህርት ከመቅሰም የማይቦዝን ሰዉ ነው” ሲል መስክሮአል።
ኃይለማርያም ደሳለኝ ከስልጣን ሲወርዱ የኢህአዴግ እና የህውሐት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባሉ የነበሩት ጌታቸው ረዳ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት “ከአቶ መለስ ዜናዊ ሞት በኋላ በነበረው የስልጣን ሽግግር ወቅት የወንበሩ ፈላጊ እና እኔ ነኝ አዋቂው የሚለው ሰው ቁጥር በመብዛቱ አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ ስራቸውን በሚገባ እንዲሰሩ ከመርዳት ይልቅ ሙከራዎቻቸውንና እንቅስቃሴዎቻቸውን የመንቀፍ ነገር በዝቶ ነበር” ብለዋል።
የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ በኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር በነበሩበት ስድስት አመታት ለሀገሪቱ ሰላምና ዕድገት እንዲሁም አለምአቀፍ ተሰሚነት የተሻለ እንቅስቃሴ በሚያደርጉበት ወቅት ውጤታማ ስራ እየሰሩ በነበሩበት ወቅት በተገቢው ኃላፊነታቸውን እንዳይወጡ እንቅፋት በመፈጠሩ በአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ስልጣንን በገዛ ፈቃዳቸው የለቀቁ መሪ መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን በአሁኑ ወቅት ከፓለቲካ በመውጣት በተለያዩ አለምአቀፋዊ ተቋማት ላይ የመሪነት ሚና በመጫወት እንዲሁም በሀገራችን የተለያዩ ልማት ስራዎች እንዲከናወኑ የበኩላቸውን ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ወደ ዋናው ነጥብ እንመልሳችሁና እንደሚታወቀው “ኢትዮጵያ ከተመሰረተች ጀምሮ አብዛኛው መሪዎቿ በሀይማኖት፣ በብሄር ወይንም በቡድን ውስጥ ተደብቀው መምራታቸው እስከ ዛሬ ከባድ ዋጋ እያስከፈለ ይገኛል። ነገር ግን አሁንም ስልጣንን ከብሄር፣ ከሀይማኖትና፣ ከቡድን አስተሳሰብ የፀዳ፥ ያለ ማንም ድጋፍና በራሱ ጥረትና እግዚአብሔር በሰጠው እውቀትና ክህሎት እስከ ቤተመንግሥት ድረስ ጭንቅላት ብቻ ይዘው የመግባት አቅም ያላቸው እንደ የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር እንጂነር ኃይለማርያም ደሳለኝ ካልሆነ በስተቀር ኢትዮጵያ የምትባል ሀገር የሀይማኖት፣ የብሄር፣ የቡድን ኮታ ስልጣን ለመያዝ መስፈርት ማድረጓን ከቀጠለች፦ የእርስበርስ ጦርነት፣ ሁዋላ ቀርነትና ድህነት፣ ችግርና መከራ እየተፈራረቁ ይቀጥላሉ …ለመሆኑ ልዩነቶችን በመቻቻል በማሸነፍ ኢትዮጵያን በጋራ ተባብረን ለማሳደግ የእርስዎ አስተያየት ምንድነው ? የኢትዮጵያ መሠረታዊ ችግር ምን ብለው ያስባሉ ? ከእያንዳንዳችን ምን ይጠበቃል? #WolaitaTimes
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ