1000013971

በዎላይታ አከባቢ በየወቅቱ “ህጋዊ” በሚመስል አካሄድ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ ነገሮች ተወሳስበው በአከባቢው የተረጋጋ ልማት እንዳይኖር የሚደረግ ሴራ እንደሆነ ተገልጿል።

በክልሉ በየትኛውም አከባቢ ተግባራዊ ያልሆነ በተለየ መንገድ በዎላይታ ሶዶ ከተማ አመራሮች፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለአከባቢው ልማት በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ በከተማዋ ዕድገት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ያመዘኑ እንደሆነ አንድ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህርና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ አስረድተዋል።

“ለአንድ ከተማ ሁለንተናዊ ዕድገት ግብር ወሳኝ ነው፥ አሁን ደግሞ ወቅቱ ግብር የሚሰበሰብበት መሆኑ እየታወቀ ግብር ለመሰብሰብ ያቀዱ ያዘጋጁ በተገቢው እንዳይሰበሰቡ መዋቅር ላይ ያሉትን በሙሉ በትነው በአዲስ መተካት እንዲሁም የንግዱ ማህበረሰበንና ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ እየተወሰደ የሚገኘው እርምጃ በግልጽ የከተማዋን ዕድገት ወደኋላ የመመለስ ዕቅድ አካል ነው” ሲልም የአከባቢውን ፓለቲካ በቅርበት እየተከታተለ የሚገኘው መምህሩ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አብራርተዋል።

“ለአብነትም በክልሉ በአርባምንጭ፣ በዲላ፣ ጅንካ እና ሳውላ ከተሞች ላይ ተመሳሳይ ችግሮች ቢኖርም አሁን ላይ በብቸኘነት በራሷ ገቢ በሚተዳደር በዎላይታ ሶዶ ከተማ እንዲሁም ቦዲቲ እና አረካ የመሳሰሉ መጋቢ ከተሞች ላይ እየተወሰደ ያለው አይነት “ህጋዊ” በሚመስል ሽፋን እርምጃ አለመኖሩን በመጥቀስ ጉዳዩ ህግ የበላይነት አረጋግጠው ለህዝብ ጥቅም ነው ለማለት አያስደፍርም” ብለዋል።

በቅርቡ በዞኑ የአለም ባንክ የከተሞች ተቋማዊና መሠረተ ልማት ፕሮግራም ( UIIDP) ማዕቀፍ ተጠቃሚ የነበሩ ቦዲቲ እና አረካ ከተማ ከድጋፉ መሰረዛቸውን በማስታወስ ከተሞቹም በ2020 ዓ.ም አሁን ላይ አለም ባንክ ያወጣውን መስፈርት በተገቢው በማሟላትና የተሻለ አፈፃፀም በየጊዜው በማሳየት በክልሉ ከፕሮግራሙ ከፍተኛ ተጠቃሚ እየሆነ የሚገኘው ዎላይታ ሶዶ ከተማ የታለመውን አላማ ሲያሳካ ባላቸው አፈፃፀምና በየጊዜው በሚያሳዩት የተግባር መሻሻል መነሻ የሶዶ ከተማ ደረጃ ስለሚደርሱ ቦታውን የሚተኩ ናቸው” ተብለው ታቅደው የነበረ ቢሆንም በከተሞቹ ዕድገት አሉታዊ ተፅዕኖ በሚስጥር ሁኔታ ከድጋፍ ተጠቃሚነት መሠረዙ የዚሁ ሴራ አካል እንደሆነም ምሁሩ አክለው አስረድተዋል።

ባለፈው ወር የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በምርመራ ዘገባው “የአዲሱ ክልል ከህዝብ ፍትሃዊና ዕኩል ተጠቃሚነት አንፃር ምሁራንና የአከባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?” በሚለው አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር “ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንድመራ መግባባት ተፈጥሮ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ እንቅስቃሴ መኖሩን ጠቁሟል።

ህገመንግስት ያጎናፀፈውን ጥቅም ሊጎዱ የሚችሉ ህጎች በህገ-መንግስት ጭምር እንዲካተት በማድረግ አዋጆች፤ ደንቦች እና መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ወደ ተግባር መገባቱን በመግለፅ ለአብነት በክልሉ በብሄረሰቦች ም/ቤት አማካይነት በሀገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ የበጀት ቀመር የማዘጋጀት፤ በሰራተኞች ምደባ እና ዝዉዉር ለሁሉም ዞኖች እኩል በማድረግ በክልሉ ገቢዎች ቢሮ የተጀመረ በሌሎች ቢሮዎችና አሰራሮች የሚቀጥል ከሆነ በአከባቢው ኢፍትሐዊነት ሰፍኖ አደገኛ የመልካም አስተዳደርና የፓለቲካ አለመረጋጋት ምንጭ ሊሆን እንደሚችልም ምሁሩ ስጋቱን ገልፀው ነበር።

የፍትሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎች በሚነሱበት ወቅት አንዱን የህብረሰብ ክፍል አለአግባብ በመጥቀም ሌላውን አለአግባብ የሚጎዳበት አደገኛ ሁኔታ የሚፈጥር በመሆኑ የመንግስትና የሕዝብ ሀብት እንዲሁም የአስተዳደር ፖለቲካ የመምራት ኃላፊነት ተቀብለው እየሰሩ የሚገኙ አካላት የፍሐዊነትና የዕኩልነት መርሆዎችን በተገቢው ተረድተው “ለራስ በልዩነት” ከሚለው አስተሳሰብና ድርጊት ተቆጥበው በክልሉ ለሚገኙ ሁሉም ህብረተሰቡ ክፍሎች የሚገባቸውን ጥቅምና ክብር መስራት እንደሚገባ አክለው መጠቆሙ ይታወሳል።

አመራሩ ነፃ እና ገለልተኛ ሆኖ ሁሉንም ህዝቦች በቅንነትና በታማንኝነት በህጋዊነት የሚገባቸውን እንዲያገኙ በማድረግ ማገልገል የነበረባቸዉ አንዳንድ ተቋማት በተቃራኒው ናቸውና ህዝቡ በፖለቲካ ሥልጣን ድልድልና በሀብት ክፍፍልም በተለይም የክልሉ ምክር ቤት በሚያውጃቸው ሀብቶች አስተዳደር ላይም ኢፍትሐዊ አሰራር ተሰርቶ ለመልካም አስተዳደር ችግር ምንጭ እንዳይሆን ከወዲሁ ጥንቃቄና ክትትል ሊደረግ እንደሚገባም ምሁሩ በማጠቃለያ ሀሳቡ ጥሪ ማቅረቡን መዘገባችን አይዘነጋም።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው