1000014060

በዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርስቲ ልዩ የአቅም ግንባታ ስልጠና የተመደቡ መምህራን እና የትምህርት ቤት አመራሮች ሥልጠናውን በከፍተኛ ደረጃ ተቃውመዋል።

እነዚህ አካላት ወደ ዎላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የተመደቡት በዋናነት ከዎላይታ ዞን ከሁሉም ወረዳዎች፥ ከጎፋ ዞን እና ከጋሞ ዞን ከተወሰኑ ወረዳዎች የመጡ እንደሆነ ተገልጿል።

ከስፍራው የደረሰን መረጃ እንደሚያመለክተው በስልጠናው እንዲሳተፉ የተላኩት የ2ኛ ደረጃ የሳይንስ ትምህርቶች መምህራን፥ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህራን እና የት/ቤት አመራሮች ሲሆኑ ሰልጣኞች ተቃውሟቸውን እያሰሙ የቆዩት ከማክሰኞ 23 – እለተ አርብ ቀን 26/11/2016 ዓ.ም ድረስ መሆኑም ተነግሯል።

የዩኒቨርስቲው ፕሬዝዳንት ዶ/ር ጉቼ ጉሌ እና የስልጠናው አስተባባሪዎች መምህራንን “ለማግባባት” በሚል ሁለት ዙር ስብሰባ ቢያካሂዱም “ሠልጣኞቹ በሁለቱም ስልጠና መግባባት ባለመቻላቸው ስልጠናውን ረግጦ ወጥተዋል” ሲል አንድ ሰልጣኝ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተዋል።

በተጨማሪም ሐሙስ ዕለት በቀን 27-11-2016 ዓ.ም ደግሞ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር አበባየሁ፥ የዎላይታ ዞን ትምህርት መመሪያ ኃላፊ እና የዞኑ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ጎበዜ ጎዳ እና የዩኒቨርስቲው ፕሬዚዳንቶች በጋራ ሆኖው ሦስተኛ ዙር አወያይተው የሰጡት ምላሽ አጥጋቢ ባለመሆኑ ሠልጣኞች ስብሰባውን አቋርጠው መውጣታቸውንም አክለው አብራርተዋል።

መምህራኑና የት/ቤቶች አመራሮች ስልጠናውን እንዲቃወሙ ካደረጉ ምክንያቶችን ሰልጣኞች ሲገልፁ “ስልጠናው ለስሙ ስልጠና ተብሎ ነገር ግን ውሎ አበል የሌለው በመሆኑ፥ አብዛኞቹ መምህራን እና የት/ቤቶች አመራሮች ከሚሠሩበት ወረዳ የግንቦት ወር ደመወዝ ጭምር ያልተከፈላቸው መሆኑ፥ የተከፈላቸውም ከ30% -50% ብቻ ሆኖ ራሳቸውን እና ቤተሰቦቻቸውን አደጋ ጥሎ መምጣታቸው ነው”

ከዚያ ባሻገር “ሥልጠናው የተዘጋጀበት ዋና ዓላማ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በዩኒቨርስቲ በተሠጠው የ12ኛ ክፍል ፈተና ተማሪዎች እጅግ በጣም ዝቅተኛ ውጤት በማምጣታቸው ለዛውም ምክንያቱ በዋናነት ለሁሉም የ2ኛ ደረጃ ት/ቤት መ/ራን ዕውቀትና ክህሎት ስለሌለ ነው ተብሎ በመታሰቡም አለመግባባት ተፈጥሯል።

ከ20 ቀን ስልጠና በኋላ በኦን ላይን በሚሰጥ ፈተና 70% እና ከዛ በላይ ያላመጣ የደረጃ ዕድገት እና ልዩ ልዩ ጥቅማጥቅሞችን አያገኝም መባሉ፥ ፈተናው በተጨባጭ መምህሩ በት/ቤት ከሚያስተምረው ትምህርት ይዘት ይልቅ በትዮሪ /በንድፈ ሀሳብ ላይ ብቻ ያተኮረ መሆን፣ ከኬጂ እስከ ማስተርስ ድግሪ ድረስ ተምረው አብዛኛው ከ25 ዓመት በላይ የሥራ ልምድ ኖሮት በርካታ ምሁርን ልፋቱንና አገልግሎቱን ውድቅ ለማድረግ መታሰቡ ተቋውሞ አስነስቷል።

ከሞላ ጎደል በዚህ ዕድሜ በቤቱ በተሻለ መኝታ የሚያድረውን መምህር ጥሩ ሽታ በሌለው፥ ሎኬር፥ ጠረጴዛ እና ወንበር በሌለበት ማጎር፥ በዩኒቨርስቲው የሚሰጠው የካፌ አገልግሎት ምቹ አለመሆን እና ነጋ ጠባ ሽሮ ማቅረብ፣ የተዘጋጁት ሁለት የስልጠና ሞጁሎች በውስጣቸው የያዟቸው የትምህርት ይዘቶች መምህሩ ከዚህ በፊት በተለያዩ ስልጠናዎች የሚያውቋቸው መሆኑ፥ በሞጁል ጥራት ላይም ችግር መኖሩ እንዲሁም ስልጠናው ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ሁኔታ ያልፈጠረ መሆኑ ተጠቅሷል።

ሌላው በኦን ላይን የተሰጠው ቅደመ ፈተና የተባለው እና በስልጠና ሞጁል ላይ የስልጠና ይዘቶች በብዛት የማይገናኙ መሆናቸው፣ መንግሥት ደመወዝ በጊዜ ባለመክፈል እና አስፈላጊ የትምህርት ቁሳቁሶችን ሳያቀርብ የትምህርት ሥራ እንዲወድቅ እያደረገ በተቃራኒው ችግሮችን ሁሉ በመምህራን በመዘፍዘፉ፣ የክልሉ መንግሥት ይህን ሁሉ ችግር እንደ ቀላል በማየት “ክልሉን እየመራሁ ነው” መባሉ ሠልጣኞችን ለተቃውሞ ያነሱት እነዚህ ከፍ ሲል የተጠቀሱ እና የመሳሰሉ ችግሮች እንደሆነም አስረድተዋል። #WolaitaTimes

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው