1000014129

የዎላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ የተጨዋቾች ደመወዝ መጠን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ ቅሬታ እያስነሳ ይገኛል።

በሌላ በኩል “የዎላይታ እናቶች ከመቀነታቸው የአቅማቸውን እያዋጡ የህዝብ ገንዘብ ሀላፊነት በማይሰማቸው ሲመዘበር ዝም አንልም፥ እየተደረገ ያለው ግልፀነት የሌለው ዘረፋ በአስቸኩይ በገለልተኛ ይጣራ” በሚል ከነገ ጀምሮ ዘመቻ እንደሚካሄድ ተገልጿል።

የኢትዮጵያ እግር ኳስ የተጨዋቾች ደመወዝ ፤ የመንግሥት ሠራተኞች ሁኔታ እና የመጪው ዘመን ተግዳሮቶች በተመለከተ ከዛሬ አራት ወራት በፊት በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ዘርፍ የሚስተዋሉ በህግ ያልተመሩ አሠራሮች ሊያስከትሉ የሚችሏቸውን አደጋዎች ከግምት ውስጥ በማስገባት ጋዜጠኛ ፈቃዱ ዳና አንድ ጽሁፍ በፌስቡክ አካውንቱ ሲገልፅ፦ “መንግሥት ሆይ በአንድ ሀገር፣ ክልል፣ ዞን ሊኖር የሚገባውን የስፖርት ዓይነት፤ የቡድን መጠን እና ሊኖር የማይገባውን ካልወሰንክ እመነኝ መጪው ዘመን የፖለቲካ ፈተና ስፖርቱ በተለይም እግር ኳስ ይሆናል። መብላት መሠረታዊ ፍላጎት ሳይሆን መዝናናት ለሆነባቸው ሀገራት የተሠራውን መዝናኛ በሙሉ ለሀገሬ ይሆናል ብሎ በየቀበሌው የልማት ጊዜ፣ ገንዘብና ጉልበት ለእርግጫ እያዋላችሁ ያላችሁ የሚመለከታችሁ ሰዎች ልብ በሉ” ብሎ ነበር።

አክለውም “በአመት 17 ቢሊዮን ዶላር ለአሳማ፣ ውሻና ድመት ምግብ ከሚያወጡ አውሮፓውያን፤ በአመት 105 ቢሊዮን ለመጠጥ፤ 50 ቢሊዮን ለሲጋራ፤ 35 ቢሊዮን ለንግድ ቦታ መዝናኛ ከሚያውሉት ጋር እኛ ግን አፍሪካውያን በጠቅላላ 12 ሚሊዮን ዶላር የማይደርስ ምግብ ተመግበን፤ ልጆቻችን ከመቼውም ጊዜ በላይ ትምህርት እየጠሉ ኢመደበኛ በሆኑ መንገዶች ብልጽግናን አያማተሩ ባለበት ጊዜ ህዝቡ በየሠፈሩ ያለስነስርዓት እንደ አሸን የፈላውን የሥራ ፈት ስብስብ በጊዜ፣ በገንዘብ፣ በሞራል፣ በዓይነት እንዲደግፍ እያደረግን እየሳትን ነው፥ ጆሮ ያለው ይስማ አንድ እሥራኤላዊ “ዴሞክራሲ የመጪው ዘመን ዲያብሎስ ነው ” ብሏል። እኔ ግን እላችኋለሁ “እግር ኳስም ገደብ ካልተበጀለት ለኢትዮጵያ በተለይም ለዎላይታ የመጪው ዘመን ዲያብሎስ ነው።” በሚል ሁኔታውን ገልፆታል።

እናም አሁን ከሰሞኑ የዎላይታ ዲቻ ስፖርት ክለብ በዝውውር መስኮቱ የተለያዩ ተጫዋቾችን እያስፈረመ ባለበት ወቅት የተስተዋለው የተጨዋቾች የተጋነነ ወርሃዊ ደመውዝ መጠን በተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ዘንድ የአግባብነት ጥያቄ እያስነሳ ይገኛል።

ከጥያቄዎቹ መካከልም “ምንም ዓይነት ፕሮፌሽናልነት በማይታይበትና ከስሜታዊነት ውጭ ይሄ ነው የሚባል አዝናኝ እግር ኳስ በሌለበት ሊግ የአንድ ተጫዋች ደመወዝ ይህን ያህል የተጋነነበት ምክንያት ምን ይሆን፤ ዲቻ ከአርሶ አደር እስከ መንግሥት ሠራተኛ እንዲሁም ባለሀብት ባዋጣው መዋጮ እምብዛም ግልጋሎት ለማይሰጡ ተጫዋቾች መዋጮ ከፋዮችን ተስፋ በሚያስቆርጥ መጠን ከፍ ማድረጉ ህገወጥነትን አያበረታታም ወይ፤ ለአንድ ተጫዋች ይሄ ያህል ሲከፈል እጅግ በጣም ዝቅተኛ ደመወዝ ለዛውም በጊዜ የማያገኝ ድሃው የመንግሥት ሠራተኛ ከአሁን በኋላ መዋጮ ለመክፈል ምን ያክል ፍቃደኛ ይሆናሉ ?” የሚሉና ሌሎችም የቅሬታ ጥያቄዎችን በከፍተኛ ደረጃ እያስነሳ ይገኛል።

በተያያዘም እንደ አንድ የሶሺዮሎጂ ባለሙያ ለብዙ ዘመናት ለፍቶ በርካታ ነዋይ አፍስሶ የተማረው የመንግሥት ሠራተኛው ከሚከፈለው ደመወዝ አንፃር ምንም ሳይ’ለፋ በአቋራጭ ይህንን ያህል ገንዘብ መሥራት ከተቻለ መጪው ትውልድ ለምን ትምህርት ይማራል? የሚያስብሉ ሁኔታዎች መፈጠራቸው እንደማይቀርና በሂደትም በቀላሉ የማይፈታ ማህበራዊ ችግር የሚያስከትሉ አቋሞች በዜጎች ዘንድ እየተያዙ እንዳይመጣ ስጋት አለኝ።” ብሏል።

ይህ ጽሁፍ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ ዲቻ ወደ ስድስት የሚሆኑ ተጫዋቾችን እንዳስፈረመና የሁለቱን ውል እንዳደሰ መረጃዎች የሚያሳዩ ሲሆን እነዚህም :- 1.ሙሉቀን አዲሱን ከሲዳማ ቡና 566,380 ብር፣ 2.ቴዎድሮስ ታፈሠ ከሀዲያ ሆሳዕና 428,448 ብር፣ 3. ያሬድ ዳርዛ ከኢትዮጵያ መድን 342,241 ብር፣ 4. መሳይ ሰለሞን ከኢትዮ ኤሌክትሪክ 83,620 ብር፣ 5. ውብሸት ክፍሌ ከአዲስ አበባ ከተማ 40,517 ብር፣ 6.ምንተስኖት ተስፋዬን ከነገሌ አርሲ 40,517 ብር እንዲሁም ውል ያሳደሱ ተጨዋቾች ደግሞ 1.አዛሪያስ አቤል 152,586 ብር፣ 2.መሳይ ኒኮላ 99,138 ብር እንደሆነ ለማወቅ ችለናል።

“በመጨረሻም በድፍረት ማለት የምፈልገው ከዞን መዋቅር የወረደ የእግር ኳስ ቡድን እንዳይኖር፤ ሌሎችም ስፖርቶች ለጤና እንጂ ለተኝቶ ተቀላቢ ቡጠኛ ጥሮ ግሮ አዳሪ ደሃ ነጋዴ፣ አርሶአደርና የመንግሥት ሠራተኛ ከግብር የተረፈችውን ሀብቱን እያዋጣ ያለአግባብ ወጣቱን እንዲጦር የተዘረጋውን የዘንዶ አሠራር በህዝባችን የበረታ ፀሎት ከዜጎች ጫንቃ አሽቀንጥረን ጥለን ወጣቱ መደበኛ ሥራውን ተግቶ የሚሠራና እንደህዝብ ገና ለመዝናናት ያልደረስንና የመዝናናት ጥሬ ትርጉሙ ለእኛ የማይ’ገባን ህዝቦች መሆናችንን እንዲረዳ እንሠራለን ! ዲቻ የስፖርት ክለብን ብቻ ይኸ ጉዳይ አይመለከትም !” በማለት ጋዘጠኛው ትዝብቱን አካፍለውናል።

ውድ አንባቢያን የዚህ መሉ ጽሁፍ ይዘት የፀሃፊውን አቋም እንጂ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንዳልሆነ እያሳወቅን ሌሎቻችሁም በጉዳዩ ዙሪያ በዚህ ርዕስ ስር በአስተያየት ሳጥን ሀሳባችሁን እንድታጋሩን እንፈልጋለን።

በተጨማሪም ከዚህ ጋር በተያያዘ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተጨባጭ ተደራጅቶ የደረሰው መረጃ እንደሚያመለክተው ክለቡ አሳማኝ ያልሆነ ተጫዋች ዝውውር እርምት እንድደረግ፣ እንዲሁም ከቡና ጋር የተፈጠረው ችግር በተመለከተ ለእግር ኩዋስ ፌዴረሽን አቤቱታ “ሳያስገቡ አስገብተናል” ብለው ህዝቡን ንቀው የዋሹት የክለቡ አመራር፣ አሰልጣኝና ቦርዱ ግልፅ ይቅርታ እንድጠይቁ ካልሆነ አዲሱ ውድድር አመት ሳይቃረብ ቶሎ ቦታቸውን እንዲለቁ በአመራር፣ አሰልጣኝና ቦርድ አባላት ላይ የተቀናጀ ተቃውሞ ድምፅ ከነገ ጀምሮ በተለያዩ መንገዶች ለማሰማት ዝግጅት መጠናቀቁን አስተባባሪዎቹ ገልጸዋል።

እንደ የዘመቻው አስተባባሪዎች ገለፃ “የዎላይታ ህፃናት ጎዳና ላይ ፀሀይና አቡዋራ ሲፈራርቅባቸው ለፍተው ካገኙት የእለት ጉርስ እንዲሁም የዎላይታ እናቶች ከመቀነታቸው ላይ አካፍለው ለዲቻ የአቅማቸውን እያዋጡ የህዝብ ገንዘብ ሀላፊነት በማይሰማቸው ወንበዴ በግለሰቦች ሲመዘበር ዝም አንልም በማለት፣ የዎላይታ ድቻ አሰልጣኝ፣ አመራርና ቦርድ አባላት በአስቸኩይ ሥራቸውን ይልቀቁ፣ ቡድኑ ላይ እየፈፀሙት ያለው ግልፀነት የሌለው ዘረፋ በአስቸኩይ በገለልተኛ ኦዲት ምርመራ ይደረግ” በሚልም ይካሄዳል።

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው