1000014561

በደቡብ በተለይም ዎላይታ አከባቢ ፓለቲካ አካሄድ ከሀገራዊ ሁኔታው አንፃር እንዴት ነበር❓ በሀገሪቱ ባለፉት አምስት አመታት በተካሄደው ወሳኝ ልማት/ጦርነት የዎላይታ ተሳትፎ እና ያገኘው ውጤት እንዴት ይመዘናል❓ የዎላይታ ምሁራንና ፓለቲካኞች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የጎረቤት ህዝብ አንድነትና የጋራ ልማት በተመለከተ ያደረጉት በጎ ሆነ መጥፎ ተፅዕኖ ምንድነው❓ እንዴትስ መቃኘት አለበት❓

አብዛኛው የዎላይታ አከባቢ ፓለቲካ አቀንቃኞች መንግሰት ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሰጥ የህዝብ ተጠቃሚነት የመጨረሻ አድረገው ይደሰታሉ፣ አቋማቸውንና ሙግታቸውን አቁሞው ዝም ይላሉ (ሹመት፣ ከእስር የሚወዱትን ስፈታ፣ በንግግር …ወዘተ) ይሄ ከምን የሚመነጭ ነው? መፍትሔውስ❓

በአካባቢያችን በፓለቲካ የቆዩ ባለልምድ በቀላሉ መንግሥትን በህዝብ ጉዳይ ላይ ማሳመን የሚችሉትን በማግለል ማሳተፍና እውቅና መስጠት ብዙም አልተለመደምና ለዚሁ ነገር ከአከባቢው አመራሮች ጀምሮ ምን ይጠበቃል❓

በአካባቢያችን በየወቅቱ የተከሰቱ የአመራሮች እንዲሁም ሌሎች በህዝብ ጉዳይ ላይ በቅርበት የሚሰሩ ግለሰቦች ልዩነታቸውን ትተው በአንድ መድረክ ሲነጋገሩ አይታዩም፣ ይሄ አካሄድ በህዝብ ጉዳይ ላይ ሶስተኛ ወገን ጠላት እጁን እንዲከት አላደረገም ወይ❓ እንዴት ቢናደርግ ነው የሚሻለው❓

ከላይ የተጠቀሱ ችግሮች እየተስተዋለ ከፌደራል፣ ከክልል ጋር ያለውን ጤናማ ግንኙነት አጠንክረን ህዝባችን የሚገባውን እንዲያገኝና ተደማጭነት ከፍ እንድል እንዴት ማድረግ ይበጃል❓ለዚሁ ሁሉ ችግር ኃላፊነት የሚወስደው ማነው❓ ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቅብናል❓ በሚሉ ጉዳዮች ላይ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት አንድ በተነሱ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው አቅርቧል። ዝግጅቱ በሁለት ክፍል የሚቀርብ ሲሆን ለዛሬው ክፍል አንድ እንደሚከተለው ቀርቧል።

⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦ ሰላም። እንኳን ወደሚዲያችን በደህና መጣህ።

✅ ማሪንዶስ ጦና ፦ እንኳን ደህና ቆያችሁኝ። እድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦ ከለዉጡ ጀምሮ በደቡብ በተለይም ዎላይታ አከባቢ ፓለቲካ አካሄድ ከሀገራዊ ሁኔታው አንፃር እንዴት ነበር ❓

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ይህ በጣም ሰፊ ጥያቄ ነው፣ እንግዲህ ለዉጡ ለምንና እንዴት መጣ የሚለዉን ትተን፣ ከነበረዉ ሁኔታ አንጻር፣ የዎላይታ ተወላጅ የሆኑት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የመፍትሔው አካል ለመሆን ብለዉ ስልጣን እስከመልቀቅ ደርሰዉ ለአፍሪካም ትልቅ አርአያነት ያሳዩበት ነው። ከለዉጡ በፊትም በአንዳንድ አካባቢዎች፣ ማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች በተለያዩ ሕዝቦች ላይ ሲደርሱ የዎላይታም ልጆች በተለያዩ ቦታዎች ጥቃቶች አስተናግደዉ ነበረ። የለዉጡም አስፈላጊነት የታመነዉ አንዱ መሰል ችግሮችን ለመቅረፍ የነበረ ቢሆንም፣ በተለይ ከመርህ ዉጪ ኦሮ_ማራ ከሚለዉ እንቅስቃሴ ጀምሮ ስልጣኑን የተረከቡ አካላትና ከዉጪ የሚገቡ የፖለቲካ ኃይሎች ስለ ኢትዮጵያ ያላቸው አተያይ ና አላማ የተለያዬ በመሆኑ፣ ሐገሪቷን ከነበረችበት ወደ ባሰ ዘርፈ ብዙ ቀዉስ ዉስጥ ከተዋታል።

ባልተጠበቀ ሁኔታ፣ በኢትዮጵያ ታሪክ አሰቃቂ የሚባለዉ ጦርነት በትግራይ ተነስቶ አማራና አፋር ክልልን አካልሎ ተካሂዷል። በአገዛዙ ና በዙሪያዉ በተሰባሰቡ ኃይሎች ሕገመንግሥቱንና የሐገሪቷን ወቅታዊ ሁኔታ ያላገናዘቡ እርምጃዎች በብዛት ተወስደዋል፣ አላስፈላጊ መንገዶችም ተሂዶባቿል። በዎላይታም በኩል ካየን ሕዝቡ ከለዉጡ ከጠበቀዉ በተቃራኒዉ በከፍተኛ አመራር ደረጃ የነበሩ ተወካዮችን በሴራና በግፍ የመግፋት፣ ሕዝቡ አሰቃቂ ጥቃቶች ሲደርሱበት አለማዳን፣ ከመከላከያ በግፍ 40 ሺ ዎላይታዎችን መቀነስ፣ የሐሰት ክሶችን በተከታታይ መለጠፍ፣ የክልል ምክርቤት የዎላይታን ሕዝብ ጥያቄ ላለመመለስ አንድ ዓመት ሙሉ እንዳይሰባሰብ ማድረግ፣ በዞኑ መፈንቅለ መንግስት እስከማድረግ ተደርሷል። አሁን እንግዲህ በጉልበት፣ ያለበቂ ድርድርና የሕዝብ ይሁንታ ስድስት መቀመጫ ከተማ ባለዉ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዉስጥ ዞኑ እንዲገባ ተደርጓል።

ቀድሞ የነበረዉና ከዎጋጎዳ ትግል በሁዋላ በኃይለማርያም አመራር ተረጋግቶ፣ ሕገመንግሥቱ ተሻሽሎ፣ 17 ፓርቲዎች የተጣመሩበት አንድ ደኢህዴን የተፈጠረበት፣ በኢትዮጵያ ሁለተኛ ከተማ ለመሆን የበቃችዉ አዋሳ የተገነባችበት፣ የተለያዩ ምሁራንን ወደ ፓርቲዉ በመጋበዝ በኢትዮጵያ ታሪክ ከፍተኛ ስልጣንን የደቡብ ሰዎች የተቆናጠጡበት ሁኔታ የተፈጠረበት የደ/ብ/ብ/ሕ/ክ አሁን የለም። የደቡብ አመራሮች በጋራ፣ ለጋራ ጥቅም ና አላማ የመቆም ያዳበሩት ባህል በለዉጡ ዘመናት በጠቅላላዉ ጠፍቷል።

የክልሉ ፈረሳም እራሱ በሰላማዊና በሕገመንግስታዊ መንገድ ሳይሆን የዉስጥና ከክልሉ ዉጪ የነበሩ ኃይሎች ተቀናጅተዉ፣ ንጹሐንን አስጨፍጭፈዉ ያፈራረሱበት ሁኔታ ነው ያለዉ። ወንድማማች ሕዝቦች መሐል ቅሬታ ተፈጥሯል፣ ተጠያቂነት የሚባል ነገር ጠፍቷል።

ችግሩ ግን የብዙ ኃይሎች ድምር ዉጤት መሆኑን መዘንጋት አያስፈልግም። እንግዲህ በሐገሪቷ አሁን የሚታዩት ችግሮች መጀመሪያ የዎላይታ ሕዝብ እየቀመሳቸዉ ችላ ስለተባሉ፣ የሁሉንም በር አንኳክተዋል። የፖለቲከኞች ስደት ከነ አቶ በቀለ ገርባ ና ልደቱ አያሌዉ በፊት፣ በዎብን መሥራቹ አንዷለም ቦልጠና በኩል ዎላይታ ነው የተጀመረዉ፣ የጋዜጠኞች እስርና ስደት ብንል ያንተን የዚህ ሚዲያ ባለቤት የናትናኤል ጌቾ ቤታሎንና ታጁራ ላምቤቦ ጎታን ጉዳይ ማንሳት ይቻላል።

በትግራይ ጦርነት ወቅትም ከቀድሞ የዞናችን አመራሮች እስከነ አሰፋ ዎዳጆ ድረስ በማጎሪያ የታሰሩበት ነው። ዞኑ አስተዳዳሪዎቹ ከ5 ጊዜ በላይ የተቀያየሩበት ነው። ከአምስቱ ዶክተር ጌታሁን ጋረዶ የመንግስት አመራርነት በቃኝ ብሎ ወደ አለም አቀፍ ተቋም ሄዷል፣ አቶ ዳጋቶ ኩምቤ ከእስር በሁዋላ ወደ አመራር ተመልሷል፣ አቶ አክሊሉ ለማ ስደትን መርጧል። በአጠቃላይ በዞኑ በተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት ወቅት ከተገደሉ ንጹሐን ጉዳይ ጨምሮ ስናይ ከለዉጡ ጀምሮ ያለዉ ጊዜ ጥሩ የሚባል አይደለም። ሐገራችን በአጠቃላይ ጥሩ ሁኔታ ዉስጥ አትገኝም፣ በእዉነቱ የትኛውም ማህበረሰብ በተለዬ ሁኔታ ደልቶታል፣ ተጠቅሟል ማለት የሚቻል አይመስለኝም።

⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦በሀገሪቱ ባለፉት አምስት አመታት በተካሄደው ወሳኝ ልማት/ጦርነት የዎላይታ ተሳትፎ እና ያገኘው ውጤት እንዴት ይመዘናል ❓

✅ ማሪንዶስ ጦና ፦ከጦርነቱ ብጀምርልህ ኢትዮጵያ ተመልሳ ወደ እርስ በርስ ጦርነት መመለሷ፣ ለዎላይታም ሆነ ለተቀረዉ ኢትዮጵያዊ ትልቅ ኪሳራና ዉርደት ነው። ጦርነቱ ሲጀመር እናተርፋለን ብለዉ ያሰቡ ብዙ ኃይሎች ዛሬ ላይ ሆነዉ እየተጸጸቱ ነው። በርግጥ ጦርነቱ በዋናነት በኦሮሚያ ና አማራ ብልጽግናዎች፣ ከህወሓት ጋር የነበራቸዉ አለመግባባት ተካሮ ያፈነዳዉ ቢሆንም፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ ከወረደ በሁዋላ የደቡብ አመራሮች ክልሉን ከነበረበት የፖለቲካ ቁመና በመፈጥፈጣቸዉ፣ ዉሳኔ ሰጪ አካላት ዉስጥ የደቡብ ሰዎች ባይኖሩም እንደ ደርግ ጊዜዉ ሁሉ የደቡብ ሕዝብ ልጆች በማያገባቸዉ ወይንም ከሚያገባቸዉ በላይ በጦርነቱ ተማግደዋል።

እዚህ ጋር ማንሳት የምፈልገዉ፣ የዎላይታ 40 ሺ ልጆች ከመከላከያ አለአግባብ መቀነሳቸዉ ዎላይታን ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያን በጣም ጎድቷል። ከብልጽግና ሕገወጥና መርህ አልባ አግላይ አካሄዶች ባሻገር፣ ህወሓት የነበረባት እብሪት፣ በግልጽ እንዳመኑት ተኩሰዉ ጦርነት ከመጀመራቸዉ ባሻገር ጦርነት ከለኮሰባቸዉ ና ከብልጽግና ሰዎች ጋር ሲነታረክ ከነበረባቸዉ ምክንያቶችም አንዱ ተቋማት በሕብረብሔራዊነት ሳይሆን በኦሮ_ማራዊነት እየተገነቡ ነው የሚልና እንደዎላይታዉ ሁሉ አለአግባብ ተቀንሰናል የሚልም ነው።

እንግዲህ ያ 40 ሺ የዎላይታ ልጆች ባይቀነሱ፣ ብዬ ምልከታዬን እንዳላስቀምጥ፣ ትግራይ የተገፋችበት ሁኔታ ዎላይታንም ያካተተ ነበረ። ግን በዎላይታ በኩል ያ ከፍተኛ ልምድና ዉጊያን የመቋቋም አቅም ያለዉ፣ ሐቀኛ ሪፎርም ከተካሄደ ጥሩ ቦታዎችን የሚይዘዉ ጦር ተቀንሶ፣ በሚያሳዝን ሁኔታ አሁንም አዲስ ወጣቶች በ10ሺዎች ተመልምሎ፣ በጦርነቱ ተማግዷል።

ያዉ ጦርነቱ ብዙ የዉጪ ኃይሎችንና ና ኢ_መደበኛ ኃይሎችን ያሳተፈ፣ ሕዝባዊ የርስ በርስ ጦርነት ስለነበረ ሁሉም ኢትዮጵያዊ በጣም ተጎድቷል፣ በየቤቱ ፣በየሰፈሩና መንደሩ ሁሉ ሐዘን ገብቷል። ከዛ በተረፈ በ state building መከላከያ ትልቅ ቦታ የሚሰጠዉ ነውና 40 ሺ ዎላይታ ከሠራዊቱ መቀነሱ አንድምታዉ ከባድ ነው፣ ኃይለማርያም ደሳለኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሲሆን አንድ እንኳን የዎላይታ ጀነራል አልነበረም፣ ያ የሚፈጥረዉ ክፍተት ቀላል አይደለም። ብልጽግና መፍጠር የሚፈልገዉ ሐገር ምን አይነት ነው የሚለዉንም ጥያቄ ዉስጥ የሚከት ነው።

በልማት አኳያ ካየነዉ ደግሞ በዎላይታ የመዋቅር ጥያቄ ካለመመለሱ በተጨማሪ፣ ለምሳሌ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የእንዱስትሪ ዞን ሕዝቡ ሲጠይቅ፣ የእንዱስትሪ ዞን አያዋጣም በዎላይታ አንሠራም፣ ባለ ማግስት በኦሮሚያ ና በአማራ ክልሎች ሲያስመርቅ አይተናል። በዚህ ረገድ ከየትኛዉም አካባቢ የበለጠ በሕዝብ ቁጥር አንጻር ካየን በ100ሺ ዎች የተማረ ሥራ አጥ ያለበት ዎላይታ አሁንም የተለወጠ ነገር የለም። በሐገሪቷ ሰላም ካለመኖሩ ጋር ተያይዞ እንደድሮዉ በሌሎች አካባቢዎችም ሥራ የለም።

ሌላዉ አጼ ኃይለሥላሴ ጊዜ ተፈቅዶ በዎላይታ ሕዝብ ጉልበት የተገነባዉ አየር ማረፊያ ለጥቂት አመታት አገልግሎ መዘጋቱ ሲቆጨዉ የኖረዉ ሕዝብ፣ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የዎላይታ ሶዶ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ እዲገነባ ሲጠየቅ፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አርባ ምንጭ ሄዳቹ ኑ ብሎ፣ ሕዝቡን ቢያስከፋም፤ መልሶ ደግሞ ግምባታ ተጀምሮ በርሳቸዉ የተጎበኘዉ ቀርቶ ሌላ፣ በአረካ ሱማሜ ሜዳ ይገነባል ተብሏል። አሁን የሕዝቡ ጥያቄ ቶሎ ይገንባልን የሚል ነው። በሐገሪቷ ሠላም አለመኖሩ ከልማት አኳያ ማነቆ ቢሆንም፣ የሚሰሩ የተወሰኑ ልማቶችም ከሚወጣባቸዉ ወጪ አንጻር ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ ይገባል ወይ የሚለዉ አጠያያቂ ነው፣ በግሌ ቤተመንግስት፣ ፓርኮችና የኮሪደር ልማቱ ቅድሚያ ሊሰጣቸዉ ይገባል ብዬ ባላምንም፣ እነሱም ቢሆኑ በዎላይታ የተሠሩበት ሁኔታ የለም።

በመሠረተ ልማት አኳያ ካየን ከለዉጡ ወዲህ በዎላይታ መሠረተ ድንጋይ ከመጣል በዘለለ ያለቀ ትልቅ ፕሮጀክት የለም። በዎላይታ ሶዶ ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅ ይገነባል የተባለዉ አስፋልት፣ ሕዝቡ እስከ ሁምቦ መዉጫ መቀጠል አለበት የሚል ጥያቄ እያነሳ ቢሆንም፤ ያንን መሥማት ቀርቶ፣ መጀመሪያ ቃል የተገነባዉንም መገንባት አልጀመሩም። በትምህርት አኳያም በአዲሱ አሰራር በገፍ እየወደቀ ያለዉ ተማሪ ጉዳይ፣ ከመምህራን ደሞዝ አለማግኘት ጋር ተያይዞ አሳሳቢ ነው የሚለዉንም መጥቀስ እፈልጋለሁ ባጭሩ።

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ የዎላይታ ምሁራንና ፓለቲካኞች እንዲሁም የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች የጎረቤት ህዝብ አንድነትና የጋራ ልማት በተመለከተ ያደረጉት በጎ ሆነ መጥፎ ተፅዕኖ ምንድነው ? እንዴትስ መቃኘት አለበት ?

✅ ማሪንዶስ ጦና ፦ ከፖለቲከኞች ከተነሳን በእዉነቱ ከዎላይታ የተነሱት ሌላዉን የደቡብ ሕዝብ አስተባብረዉ እንደሰሩት ያንን ማስቀጠል የሚቻልበት አመቺ ሁኔታ ነበረ ብዬ አላምንም፣ በዎላይታ ላይ ከሚደርሰዉ የተለዬ ጫና የተነሳ ፖለቲካዉ reactive ነበር፣ የምሁራኑም ጉዳይ ተመሳሳይ ነው ሕዝቡ በመጠቃቱ፣ ያንን በመከላከል ላይ ያተኮረ መሰባሰብ ነው የነበረዉ። ፖለቲከኞቻችንም ሆነ ምሁራን በከፍተኛ ጫና ፣ እስርና ማሳደድ ሲደረግባቸዉ ስለቆዬ ካሳለፉት ችግር ባሻገር፣ አገዛዙ በዎላይታ ሕዝብ ላይ የሚያደርሰዉን ኢ_ሕገመንግሥታዊ ጫና በማየት አድባቴጅ የወሰዱና መዉሰድ የሚፈልጉ የአጎራባች ሊህቃን አሉ፣ እነዚህ ከሚያደርሱት ጉዳት አንጻር፣ በዎላይታ በኩል ያለዉ ነገር ከመሥመር የወጣ አይደለም።

አገዛዙ ዉስጥ የሚገኙ ረዣዥም የሶስተኛ ወገኖች እጆች ዎላይታን ለመጉዳት በአጎራባች ሊህቃን በኩል በተደጋጋሚ ይመጣሉ፣ እኔ በደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድማማችነት ባምንም፣ መንግስት ሁሉንም ሕዝቦች እኩል በማያይበት ሁኔታ ለጋራ ልማት መሥራት አስቸጋር ነው። በፈደራል ሥርዓቱ መሠረት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር የያዘዉ የዎላይታ ሕዝብ በፈደራልም፣ በክልልም ሚዛናዊ ዉክልና ማግኘት ሲገባዉ ያንን ተነፍጓል። ይህ ትልቅ ክፍተት እየፈጠረ ቀጥሏል፣ ክልሉም ቢሆን በዎላይታ ሕዝብ ላይ ያለበቂ ድርድር መጫኑ ይታወቃል።

ዳዉሮና ኮንታም ከሚቀራረቧቸዉ ሕዝቦች ተነጥለዉ መሄዳቸዉ፣ የደቡብ አመራሮችን ድክመት ያሳያል፣ ተንኮልም ያለ ይመስላል፣ የዳዉሮንና የኮንታን መሄድ በስልታዊ መንገድ የሚደግፉ ኃይሎች የነበሩ ይመስለኛል፣ ብርቱ ጥርጣሬ አለኝ፣ ደግሞ ከለዉጡ በሁዋላ ዎላይታ በደቡብ ጉዳይ ላይ የሚወስንበት ስልጣን አልነበረዉም፣ እነኝህ አካባቢዎች ዞንነት ያገኙትም በዎላይታ ሕዝብና አመራር ትግል መሆኑ ይታወቃል። አሳዛኝ ቢሆንም ወንድማማችነቱ ከክልል መዋቅሩ ዉጪም ይቀጥላል።

ደቡብ ኢትዮጵያን እዉነተኛ ሶስተኛ ክልል ማድረግ ካስፈለገ እነኝህን ወንድም ሕዝቦች መመለስ ከፈለጉ ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እድል ሊሰጣቸዉ ይገባል ባይ ነኝ። በዎላይታ በኩል ከሕዝብ ቁጥር፣ ከደረሱ ጥቃቶች አንጻር፣ ከታሪካዊ ናፖለቲካዊ እዉነታ አንጻር የሚነሱ ጥያቄዎችን በድርድር መመለስ፣ በክልሉ የሚነሱ የማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄዎች ያለ ተጨማሪ ቀጠሮ በአሳታፊ ሕገመንግሥታዊ ና ዴሞክራሲያዊ ሕዝባዊ መድረኮች፣ ያለ ጣልቃ ገብነት መቋጫ የሚያገኙበትና ሕዝቡ ወደ ልማት የሚመለስበት መንገድ መፍጠር ያስፈልጋል።

በእኔ እይታ መንግስት በዎላይታ ላይ የሚያደርሰዉ የተለዬ ጫና ለነዚህ ሁሉ ችግሮች ዋነኛ ምክንያት ነው። ሶስተኛ ወገን ጣልቃ የማይገባበት፣ አዉድ ከተፈጠረ ክልሉ ትልቅ ተስፋ አለዉ። በማህበራዊ ሚዲያ አንቂዮች ጉዳይ አንድ የማልደብቅህ ነገር ቢኖር፣ ሥነምግባር፣ ስክነትና አርቆ አሳቢነት ይጎድላል ባይ ነኝ። ይህ በመላዉ ኢትዮጵያ የሚታይ ችግር ነው።

⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦ አብዛኛው የዎላይታ አከባቢ ፓለቲካ አቀንቃኞች መንግሰት ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሰጥ የህዝብ ተጠቃሚነት የመጨረሻ አድረገው ይደሰታሉ፣ አቋማቸውንና ሙግት አቁሞው ዝም ይላሉ (ሹመት፣ ከእስር የሚወዱትን ስፈታ፣ በንግግር …ወዘተ) ይሄ ከምን የሚመነጭ ነው? መፍትሔውስ❓

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ ያልከዉ ነገር ይስተዋላል። ለሕዝብ ታግሎ የታሰረና የተንከራተተ አመራር ከእስር ተፈቶ ወደ ሥራ ሲመለስ…. .. ክፍል ሁለት ይቀጥላል።

ውድ ተከታዮቻችን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው የቀረበው ዝግጅቱ በሁለት ክፍል የሚቀርብ ሲሆን ለዛሬው ክፍል አንድ አቀረብንላቸው ክፍል ሁለት ደግሞ በቀጣይ ይቀርባል። Wolaita Times ,Voice of People 🙏