1000014643

ወደ ፖለቲካው ዓለም የተቀላቀሉት ገና በወጣትነት የኮሌጅ ተማሪ እያሉ እንደ ሆነ ይነገራል። ወደ ፖለቲካው ዓለም ከገቡ በኋላ በአጭር ጊዜ ወደ አመራርነት መጥተዋል። የቀድሞ ደቡብ ኢትዮጵያ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ፣ ግብይት እና ህብረት ስራ ቢሮ በቢሮ ሀላፊነት ግብርና ቢሮን በምክትል ቢሮ ሀላፊነት ሰርተዋል።

በዚህ ወቅት የደቡብ ክልል ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት ሆነውም ያገለገሉ ሲሆን በሀገር ደረጃ ተመርጠው የኢትዮጵያ የኢህአዴግ ወጣቶች ሊግ ፕሬዝዳንት በመሆን ለሦስት ዓመታት አገልግለዋል።

እንዲሁም የዎላይታ ዞን አስተዳዳሪ ሆነው ለ3 ዓመታ የሚጠጋ ጊዜ ያገለገሉ ሲሆን በጊዜው የዎላይታ ዞን የተጀመሩ የልማት ሥራዎች እንዲጠናቀቁ፣ አዳዳስ የልማት ሥራዎችንም በመሥራት ውጤት አስገኝተዋል። በወቅቱ የዎላይታ ዞን በሁሉም ዘርፎች በክልሉ በላቀ አፈፃፀም ለ3 ተከታታይ ዓመታት ተሸላሚ እንዲሆን አብቅተዋል።

ከዎላይታ ዞን አስተዳዳሪነት ከተነሱ በኋላ የደቡብ ክልል ሕብረት ሥራ ቢሮ ኃላፊነት፣ እንዲሁም በውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊነት አገልግለዋል።

ከክልል ኃላፊነት ወደ ፌዴራል ተስበው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ም/ዋና ዳይሬክተር፣ ቀጥሎም የወጣቶችና ስፖርት ሚኒስትር ሚኒስቴር ደኤታ ሆነው አገልግለዋል።

በዚህ ወቅት የፌዴራል ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እንዲሁም የዴኢህዴን ሥራ አስፈፃሚ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ነበሩ።

የተጀመረው ሀገራዊ ለውጥ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ ወሳኝ ሚና የተጫወቱ ሰው ናቸው። በወቅቱ የሕ/ተ/ምክር ቤት አባል በነበሩ ጊዜ በጊዜው በድፍረት በሀገሪቱ የነበረውን ሙሰና በመተቸት በወቅቱ አይነከ የተባሉ አካላትንም በድፍረት ይገመግሙ ነበር።

አቶ ተስፋዬ ያመኑትን ነገር ፊት ለፊት የሚናገሩ፣ ገንዘብና ሥልጣን የማያንሰፈስፋቸው ግን ደግሞ ከውስጥ የጠለቀ የሕዝብ ለውጥ ፍላጎት ያላቸው፣ ለዚያም ሁሌም ያለመታከት የሚተጉ ሰው ናቸው። በዚህ ምክንያት በጊዜው የነበሩ አንዳንድ የደቡብ ባለሥልጣናት ሴራ በመጠንሰስ ሥራቸውን እንዳይከውኑ ብዙ ቢጋፈጧቸውም ተግባር ጥለው ተገምግመው አያውቁም።

የለውጡ መንግሰት ከተመሰረተ በኋላም በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት መልሶ ማቋቋሚያ ፕሮጀክት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስፈፃሚ በመሆን ያገለግላሉ ሲሆን በኋላም የደቡብ ብ/ብ/ሕ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንትና የከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆነው አገልግለዋል።

የደቡብ ኢትዮጰሰያ ክልል ምክር ቤት አባልና የብልፅግና ፓርቲም ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ተስፋዬ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተደራጀ በኋላ የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተው አሁን ወደ ፌዴራል በመሳብ የመስኖና ቆላማ ሚኒስቴር ሚንስትር ዴኤታ ሆነው ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴር በዶ/ር አቢይ አህመድ ተሹመዋል።

አቶ ተስፋዬ በሰራባቸው ጊዜያት በርካታ ስኬቶች የተጎናፀፉ ሲሆን እንደ ሰው የራሱ የሆኑ ደካማ ነገሮችም ሊኖሩ ይችላሉና እሳቸውን በዚያ መንገድ ማየት ተገቢ የሚሉ ወገኖች አሉ።

የዎላይታ ክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ “የክልል ጥያቄን ያጨናገፈው እሱ” በሚል ስሙን አንስተው የሚከሱ ብዙዎች አሉ። በሌላ በኩል “የክልል ጥያቄ እንዲጨናገፍ ሳይሆን ሕግንና መርህን ተከትሎ እንዲሄድ ከጅምር ጀምሮ አብሮ የነበረ እንጅ የክልል ጥያቄ እንዲጨናገፍ ለአንድም ቀን ሲሰራ አላየንም እንዲያውም እሱ ባይሳተፍበት ኖሮ ክልል ጥያቄ ጋር በተያያዘ ብዙ ቀውስ ሊከሰት ይችል ነበር” የሚሉ አብረውት የሰሩ የሚመሰክሩ ብዙ ናቸው።

በዎላይታ ተፈጥሮ በነበረው አለመረጋጋት ተያይዞ ሰዎች መታሰራቸው ከሥልጣን መነሳታቸው ጋር አያይዘውም ስሙን የሚያነሱ አሉ። ሌሎቹ በትግራይ ጦርነት ወቅት ሰዎች መታሰራቸው አሳዛኝ ክስተት ቢሆንም እንደ መንግስት በሀገርና በክልል ደረጃ ለተፈጠረው ጉዳይ ስህተት ካለም በወቅቱ የደቡብ ክልል የሚመሩ አካላት በጋራ ወስነውበት ለተፈጠረው “ኃላፊነቱና ተጠያቂነቱ ተቋማዊ እንጅ ግለሰባዊ ሊሆን አይገባም” የሚሉ አሉ።

አቶ ተስፋዬ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የክልሉ አስተባባሪ ኮሚቴ ሆነው ቆይተው አሁን ወደ ፌዴራል በመሳባቸው ሁለት ሀሳቦች ይነሳሉ። ከአቶ ተስፋዬ ጋር ልዩነት ያላቸው አካላት እሱ ከክልል አከባቢ ፖለቲካ መነሳቱ ተገቢ ነው ይላሉ።

ሌሎቹ ደግሞ በክልሉ በአሁን ሰዓት ያለው የአመራር ሥርዓት የተበላሸ፣ ግለሰብአዊ አምባገነንነት የተጠናወተውና በተለይም የዎላይታን ሕዝብ ፍትሐዊና ሕጋዊ ጥቅሞቹን ለማስከበር እንደ ተስፋዬ ያለ በሳል ፖለቲከኛና ቁርጠኛ ሰው በጣም በሚያስፈልግበት ጊዜ ተስፋዬ ወደ ፌዴራል መሳቡ ትልቅ የፖለቲካ ክፍተት ብለው የሚሰጉ አሉ።

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የዎላይታ ሕዝብ ድምፅ እንደመሆኑ መጠን የዎላይታ ሕዝብ ከምንም ጊዜ በላይ አንድነቱን ሊያጠናክር እንደሚገባ ያሳስባል። እርስ በርስ በመገፋፋት ምክንያት ብዙ ተጎድተናል። በአንድም ይሁን በሌላ መንገድ የሚታየውን ልዩነት ወደ ጎን በመተው ለዘላቂ ሕዝብ ጥቅም ሲባል እጅ ለእጅ መያያዝ የግድ ይላል።

ሰዎች እንዲታረሙ ሊተቹ ይገባል። ነገር በአሉባልታ እና በግል ሁኔታ ላይ የተመሠረተ ፖለቲካ ዞሮ ዞሮ የሚመራው ወደ ውድቀት ነውና በወንድማማችነት መንፈስ መተራረምና መደጋገፍ ሊለመድ ይገባል። ከምንም በላይ ሕዝባችን ካለበት አዝቅት እንዲወጣ አንድ መሆን የግድ ነው። አንዱ ሌላውን በመግፋትና በማጠልሸት እንደ ግለሰብም እንደ ሕዝብም አንከብርም አንከበርም።

ዋናው የህዝብ ጉዳይ መፍትሔ እንዲያገኝ በውስጣችን አንድነት ተፈጥሮ ሁሉንም በየአቅጣጫው የየራሳቸው ሀሳብ ልዩነት ያላቸውን በፍቅር በጋራ እንዲሰለፍ በአክብሮትና በዲፕሎማቲክ አካሄድ ከማቅረብ ይልቅ እንደ ጠላት በመቁጠር የማሳደድ፣ ስም በማጥፋት የበለጠ እንዲርቅና በተቃራኒው እንዲቆም የማድረግ፣ በውስጣችን የእነሱና የእኛ አይነት ክፍፍል ቡድን የመፍጠር፣ የሀሳብ ልዩነት ያለው ግለሰብ እስኪጠፋ ብቻ ከታገልን በኃላ ዋናው ውጤት የሆነውን የህዝብ ጥቅም መርሳት፣ ግለሰቦች በስልጣን እያሉና ከስልጣን ሲወርዱም የህብረተሰባችን አካል መሆናቸውን በደምብ አለመገንዘብ የተፈለገው ውጤት እንዳይመጣ ካደረጉ ነጥቦች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው።

በተለይም እውነተኛና ሀቀኛ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ውሸትና ጠልፎ የመጣል እንቅስቃሴ ማካተት፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስ ጥቅም ብቻ አብዝቶ መጮህና የተፈለገው ሲገኝ ዝምታ መምረጥ፣ በየደረጃው የሚገኙ ህዝብን በመንግሥት ደረጃ ስልጣን ያላቸውን ወደ ህዝባቸው እንዲቀርቡ በሚያስችል መንገድ ከመስራት ይልቅ የበለጠ እንዲርቁ ዘመቻ በመክፈት በእርስበርስ ጥላቻ በሚፈጠረው አንድነት ማጣት ምክንያት ለሶስተኛ ወገኖች ጥቅም አሳልፎ እንዲሰጥ ማድረግ፣ ትኩረታችንን በዋናው ህዝብ ጉዳይ ማድረግን ትተን በትግል ሂደቱ ላይና በሚከሰቱ ጥቃቅን ጉዳዮች ምክንያት እርስበርስ መናናቅና የትግሉን አቅጣጫ ወደ ግለሰቦች በማድረግም አላማችንን መሳት ይጠቀሳሉ።

ሌላው እርስበርስ አለመደማመጥና ለታላላቆቹ በተለይም ልምድ ያላቸው በህዝብ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም አበርክተዋቸውን እንዲያወጡ ማድረግን መዘንጋታችን እስራኤላውያን ከግብፅ ለመውጣት 40 ቀን ብቻ የሚፈጀውን ጉዞ በመንገዱ በነበረው በራሳቸው እርስበርስ አለመስማማት ምክንያት በ40 አመት እንዳሳኩ ሁሉ ለእኛም ዛሬ ላይ ከላይ በጥቂቱ የጠቀስኳቸው የቤታችን ጉድለቶች አንድነትን በማጣታችን ምክንያት ገናና የነበረው ህዝብ በከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛልና ቆም ብለን አስተውለን በቁጭት የመጣንበትን መንገድ ገምግመን መፍትሔ ሊናበጀው ይገባል።

በተለይም ሁሉም እያለን በሀሳብ ልዩነት ምክንያት በስልጣን ባሉት እና ከስልጣን በወረዱት ላይ የምናደርገው፣ እርስበርስ ክፍፍል በሚያሰፋ አኳኃን ጠልፎ የመጣል የትግል አካሄድ እነሱን በሚተኩ ግለሰቦች ላይም አሉታዊ ጫና በመፍጠር ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለግላቸውና ለሾመው ፓርቲ ብቻ እንዲያገለግሉ፣ በእርስበርስ ጭቅጭቅና ጥራጥሬ መሀል ሶስተኛ ወገን ጠልፎ እንዲጥል፣ በህዝብ ላይ የተደቀነው ዘርፈብዙ አንገብጋቢ ጉዳዮች በወቅቱ መፍትሔና ትኩረት እንዳያገኙ እንዲሁም ከአካባቢያችን ተተኪና ልምድ ያለው አመራር እንዳይወጣ የሚያደርግ አደገኛ ልምምድ እየፈጠረ ነውና በጊዜ የለንም መንፈስ የትግል አካሄዳችን ከሀገሪቱ ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በተገቢው መመርመርና ማስተካከል ያስፈልጋል።

አቶ ተስፋዬን ጨምሮ ሁላችሁም በመካከላችሁ ያሉ ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው ለሕዝባችን ሁለንተናዊ ለውጥ በአንድነት ከመቆም ውጭ አንዱን በአንዱ ላይ በማነሳሳትና በማጋጨት የግል ጥቅም ለማካበት ታልመው የሚቀርቡ አጀንዳዎች ሊወገዙ ይገባል እያልን ለአቶ ተስፋዬ መልካም የሥራ ጊዜ እንዲሆንላቸው በመመኘት መልዕክቱን ቋጨን🙏 Wolaita Times