
“ለተጎዱ ዜጎች የሚመለከተዉ አካል ተገቢና በቂ የአስቸኳይ ጊዜ የመልሶ ማቋቋሚያ ተግባራትን እንዲያከናውን የሚጠይቅ የዎላይታ ፖለቲከኛ/አክቲቪስት አለመኖሩ የበለጠ የሚያሳዝን ነው” ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ዎዳጆ
“እነኚህ አክቲቪስቶችና በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ዎላይታ- የዞን/ክልል ባለስልጣናት አደጋዉ በደረሰበት አከባቢ ተገኝተዉ ተጎጂዎችን ማጽናናታቸዉን ሲያሞጋግሱ ሲያደናንቁ መመልከት የዎላይታ ልህቃን የፖለቲካ ግንዛቤ ገና እንጭጭ መሆኑን ያመላክታል” ሲሉም የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ተችተዋል።
በኢትዮጵያ የአደጋ መቆጣጠርና መከላከል ፖሊሲ ብሎም በ5ኛዉ ዙር የልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም አፈጻጸም መመሪያ (አሁን እየተተገበረ በሚገኘዉ) በተለያዩ የተፈጥሮ አደጋዎች (የመሬት መንሸራተት አደጋ ጭምር) አልፎም ተርፎ በሴፍትኔት ፕሮግራም ተጠቃሚ በሆኑና ባልሆኑ ቤተሰቦች (በቤተሰብ ደረጃ በሚከሰቱ አደጋዎች) ጉዳት ለደረሰባቸዉ ሁሉ የአስቸኳይ ጊዜ ዕርዳታዎች እና ለመልሶ ማቋቋም ተግባራት በቂና ተገቢ ድጋፍ የሚሰጥ መሆኑ መደንገጉን ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ዎዳጆ አስረድተዋል።
በተለይም በሴፍትኔት ተጠቃሚ ወረዳዎች (ሁሉም የዎላይታ ዞን ወረዳዎች በሴፍትኔት ፕሮግራም የታቀፉ መሆናቸዉን ልብ ይሏል) ለሚከሰቱ አከባቢ አቀፍ እና ቤተሰብ አቀፍ አደጋዎች) ለአስቸኳይ ዕርዳታ እና ለመልሶ ማቋቋሚያ የሚዉል በፌዴራል፣ ክልል፣ ዞንና ወረዳ ደረጃ ተጠባባቂ በጀት የሚያዝ መሆኑንም ጠቁመዋል።
ከዚህም በላይ ከፌዴራል እስከ ወረዳ ደረጃ የተቋቋሙ የአደጋ ስጋት ስራዎች ኮሚሽኖች፣ መምሪያዎችና ጽ/ቤቶች በጥናት ላይ የተመሠረቱ የአደጋ ቅድመ መከላከል ስራዎችን ትኩረት ሰጥተዉ የመሥራት ኃላፊነትና ግዴታ የተጣለባቸው ቢሆንም 5ኛዉ ዙር ልማታዊ ሴፍትኔት ፕሮግራም በታቀፉ በርካታ የዎላይታ ዞን ወረዳዎችና ቀበሌዎች ባለፉት 3/4 ዓመታት የተከሰቱ ተፈጥሯዊ አደጋዎች-ድርቅ፣ ንፋስንና በረዶን የቀላቀሉ ከባድ ዝናቦች፣ (ከ2/3 ሳምንት በፊት በቦሎሶ ሶሬና ዳሞት ሶሬ ወረዳዎች በ3/4 ቀበሌዎች ከባድ ጉዳት ያደረሰዉ በረዶና ከባድ ዝናብ ጨምሮ) መከሰቱን ረዳት ፕሮፈሰሩ ገልጸዋል።
“ይሁን እንጂ በተፈጥሮ አደጋ ከባድ ጉዳት ለደረሰባቸዉ ወገኖች ተገቢና በቂ የአስቸኳይ ጊዜ እና የመልሶ ማቋቋሚያ ዕርዳታና ድጋፍ በመንግስትና መያድ የተሰጠ አይመስለኝም።
በዎላይታ ዞን በርካታ ወረዳዎች በተለይም በተራሮችና ኮረብታዎች ብዙ ሕዝብ የሰፈረባቸዉ በርካታ ቀበሌያት ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ መሆናቸዉ ይታወቃል” ሲሉ አክለዋል።
“የመሬት መንሸራተት አደጋ ቅድመ መከላከልና መቆጣጠር ስራ ያልተከናወነ በመሆኑ ሰሞኑን በካዎ ኮይሻ ወረዳ በ2/3 ቀበሌዎች የተከሰተው የመሬት መንሸራተት አሰቃቂ ሰብዓዊ፣ ስነልቦናዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀዉስ አስከትሏል፤ እጅግ የሚያሳዝነዉ የክልሉ፣ ዞኑና ወረዳ መንግስታት የተያዘዉን ተጠባባቂ በጀት (መያዝ ያለበትን) ለአስቸኳይ ጊዜ እና ለመልሶ ማቋቋሚያ እያዋሉ አይደለም” ሲሉም ተችተዋል።
“የሚመለከተዉ መንግስታዊ አካል ተገቢና በቂ የአስቸኳይ ጊዜ እና የመልሶ ማቋቋሚያ ተግባራትን እንዲያከናውን የሚጠይቅ የዎላይታ ፖለቲከኛ/አክቲቪስት የለም። ከዞኑ መንግስት ፈቃድ አግኝተዉ በሶሻል ሚዲያዎች እርዳታ በመለመን/በማስተባበር ስራ የተጠመዱ ጥቂት የዎላይታ አክቲቪስቶችን እንመለከታለን። እነኚህ አክቲቪስቶችና በርካታ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚ ዎላይታ- የዞን/ክልል ባለስልጣናት አደጋዉ በደረሰበት አከባቢ ተገኝተዉ ተጎጂዎችን ማጽናናታቸዉን ሲያሞጋግሱ ሲያደናንቁ መመልከት የዎላይታ ልህቃን የፖለቲካ ግንዛቤ ገና እንጭጭ መሆኑን ያመላክታል” ሲሉም የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኙ ተችተዋል።
አክለውም “ለተጎጂዎች በቂና ተገቢ የአስቸኳይ ጊዜ እና የመልሶ ማቋቋሚያ ዕርዳታ የማቅረብ ዋነኛና ቀዳሚ ኃላፊነት የመንግስት መሆኑ ተዘንግቷል። መንግስት የሚጠበቅበትን ኃላፊነትና ግዴታ እየተወጣ ሌላዉ ሕዝብ የበኩሉን ድጋፍ /አስተዋጽኦ ማበርከት ይኖርበታል” ብለዋል።
በማጠቃለያው “በዎላይታ ዉስጥ አሉ የሚባሉ ፖለቲካ ፓርቲዎች እና አክቲቪስቶቻችን የሕጻን ፖለቲካ ትተዉ የክልል፣ የዞን እና ወረዳ መንግስታት በመሬት መንሸራተት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸዉና ከቀዬአቸዉ ለተፈናቀሉ ወገኖች ተገቢና በቂ የአስቸኳይ ጊዜና የመልሶ ማቋቋሚያ ዕርዳታ በአስቸኳይ እንዲያቀርቡ ማፋጠጥ ይኖርባቸዋል። ከዚህ ጎን ለጎን ለመሬት መንሸራተት አደጋ ተጋላጭ በሆኑ አከባቢዎች ሁሉ የቅድመ ጥንቃቄና ዝግጁነት ብሎም በሳይንሳዊ ጥናት የአደጋ ቅድመ መከላከል እና የመሬት መንሸራተት አደጋ ቅድመ መከላከል ሥራዎችን እንዲያከናዉን የተቀናጀ ጫና መፍጠር ይኖርባቸዋል” በሚል ረዳት ፕሮፌሰር አሰፋ ሀሳብ ሰጥተዋል።