1000014851

የደቡብ ኢትዮጵያ ርዕሰ መስተደድር ፅህፈት ቤት የዎላይታ ሶዶው ቢሮ “ለመግባት መንገድ ተዘግቷል” በሚል በአርባምንጭ ቢሮ መክፈቱ ተገልጿል።

የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጨምሮ የክልሉ የፓለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ማዕከል በመሆን ይፋ ተደርጎ አገልግሎት እየተሰጠበት የሚገኘው ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ የተወሰኑ መዋቅሮች ቢሯቸውን ለመገንባት ከዞኑ መሬት በመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ቀሪዎቹና ዋናዎቹ በክራይና ቀድሞ በዞኑ በጀት በተገነቡ ቤቶች ላይ በመሆን ይሄንን ለማድረግ ፍላጎት እያሳዩ አለመሆኑ ግልጽ የፓለቲካ ሴራ እንደሚያሳይም ያነጋገርናቸው የዘርፉ ባለሙያዎች አስረድቷል።

የክልሉን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተል እኚህ ምንጫችን ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እንደገለፁት “በክልሉ ሕገመንግስት ብዝሃ ማዕከል ከማለት በተጨማሪ ዎላይታ ሶዶ በስም ተጠቅሶ የአስተዳደርና የፖለቲካ ማዕከል ተብሎ የቀመጠበት የክልሉ ሕገመንግስት ሰነድ እስካሁን አለመታተሙ በግልጽ ከህዝብ ጀርባ ተደብቆ እየተሰራ ያለ የፓለቲካ ሴራ መኖሩን ያመለክታል” ብለዋል።

ሰሞኑን የርዕሰ መስተደድር ፅህፈት ቤት በዎላይታ ሶዶ ወደ “ቢሮ ለመግባት መንገድ ተዘግቷል” በሚል ሰበብ ሁኔታውን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም በተከታታይ ቢሯቸውን ትተው የአመራሮቹ የፊትለፊት ስም ጭምር አሰርተው ውይይት በአርባምንጭ ማድረግን በተደጋጋሚ እያለማመዱ ነው” በሚል ሁኔታውን ምንጫችን አስረድቷል።

ይሄው ወደ ቢሮ የሚያስገባው መንገድ ተዘግቷል የተባለው በዎላይታ ሶዶ ከሌዊ እስከ ግብርና ኮሌጅ የአስፓልት መንገድ ስራ ተስተስጓጉሎ የሚገኝ ሲሆን “አመራሮቹ በሚዲያ እርስ በእርስ ሹክቻ ተጠምዷል፥ ዛፍ ነቅሎ አስቆርጦ የመንገድ ስራው ተጧጡፏል እያሉ ቢሆንም የመብራት፣ የስልክ እንጨትና የትራፊክ መብራት አልተነሳም፥ ግንባታው ከተጀመረ 2 ወር ሞልቶም ያኔ ፌስቡክ ላይ ለመልቀቅ በቆፈሩበት ቆሟል፤ ምንም እንቅስቃሴ የለም” ሲል አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አረጋግጧል።

ሌላው ከአራት ወር በፊት ገደማ በዎላይታ አረካ አቅራቢያ ለመገንባት በይፋ የተጀመረው የአውሮፕላን ማረፊያ ጉዳይ ሲሆን ተቋራጮቹ ክልሉን “በአንድ አመት አጠናቀን እናስረክባለን ከይገባኛል ነፃ አድርጉልኝ” ካሉ 4 ወር አልፏል፤ የተጠየቀው 130 ሚሊየን ብር ብቻ የካሳ ገንዘብ ቢሆንም አመራሮቹ በእርስ በእርስ ሽኩቻ ተወጥሮ ልማት ጥለው ሚዲያ ላይ ለመታየት ከመሯሯጥ ይልቅ አንዳች የረባ ነገር እየሰሩ አይደለም በአውሮፕላን ማረፊያ እጦት ምክንያት ከተማችን በርካታ ልማት እያጣች መሆኑም ግልጽ የፓለቲካ ሴራ አካል ነው” በሚልም ቁጭቱን ገልፀዋል።

እኚሁ የፓለቲካ ጉዳዮችን በቅርበት የሚከታተለው አሁን ያለውን ሁኔታ ከብዙ መነሻዎች በመነሳት ሲገልፅ “እንዲያው ደቡብ ኢትዮጵያ የተባለ ክልል በልዩነት የዎላይታ ህዝብ ጥቅምና ዕድገት ወደኃላ ለመጎተት የተመሠረተ እየመሰለኝ ነው፣ ለምሳሌ በቅርቡ ካራት፣ ጂንካ፣ ሳውላ ፈርጅ 1 ከተማ እንዲሆኑ ሲወሰን የክልል ማዕከላት ቢሮ አሏቸው ተብሎ ነው። በሁንተናዊ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና በሕዝብ ብዛት አረካና ቦዲቲ ከእነዚያ የተሻሉ ሆነው ግን ፈርጅ 2 ተብለዋል። በዚህም በግልፅ የህዝብ ጥቅም የማሳጣት ፕሮጀክት በተሳካ ሁኔታ እየተካሄደ ያለ መሆኑን ያስተዋሉት ጥቂቶች ናቸው። ሁኔታው እንዲህ ከቀጠለ ይህች የአስተዳደርና የፖለቲካ የተባለችው ማስተዛዘኛም እንደምትከስም አልጠራጠርምና ከወዲሁ መንቃት አለብን” ሲል ጥልቅ ትዝብቱን አካፍለዋል።

እንደሚታወቀው በዎላይታ ሕዝብ ላይ ለዘመናት በተደጋጋሚ በተለያዩ ቦታዎች ይደርሱበት የነበሩ በርካታ በደሎች ጫፍ በመውጣታቸውና የቀድሞ ደቡብ ክልል መፍረስ ሲጀምር ዎላይታዊያን ከዚህ በኃላ “የራሳችንን ቤት እንገነባለን” በማለት ቆርጠው ተነስተው አላማው እውን እንዲሆን ሁሉንም የኅብረተሰብ ክፍል ያሳተፈ ዘርፈ ብዙ ትግል ከማድረግ ባሻገር በሕግ አግባብ የቀረበው የዎብክመ ምስረታ ጥያቄ በቀድሞ የደቡብ ክልል መንግሥት ተከልክሎ ይግባኝ ለፌዴሬሽን ም/ቤት ቢቀርብም ከሕግ አግባብ ውጭ ታፍኖ ተከልክለው ጉዳዩ በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች አማካይነት ወደ ፍርድቤት ተመርቶ እስካሁን ምላሽ እየተጠባበቀ ይገኛል።

ከዚያ ሁሉ መስዋዕትነትና የትግል ጉዞ በኃላ የዎላይታ ዞን ም/ቤት የዎላይታ ክልል ጥያቄን በመሻር ከሌሎች አጎራባች ሕዝቦች ጋር በጋራ እንደራጃለን የሚል ውሳኔ ወስነው የህዝብ ጥያቄን ለዓመታት የነፈጉ የቀድሞ ደቡብ ክልል ም/ቤትና የፌዴሬሽን ም/ቤት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ በማድረግ ነጭ እርግብ “በማሸነፏ” አዲሱ ክልል እውን መሆኑ ይታወሳል።

ሆኖም ግን “ክልሉ ከተመሰረተ ማግስት ጀምሮ ከተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የሚጻፉ ህጋዊ ደብዳቤዎች ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግሥት ብለው ከሥር ዎላይታ ሶዶ የሚሉ ደብዳቤዎች በከተማዋ ስም አድራሻ እየተላከና እየደረሰ ባለበት የፕሬዝዳንት ፅህፈት ቤት ጨምሮ የክልሉ የፓለቲካና የአስተዳደር መዋቅር ማዕከል በመሆን ይፋ ተደርጎ አገልግሎት እየተሰጠበት በሚገኘው ከተማ ላይ የተወሰኑ መዋቅሮች ቢሯቸውን ለመገንባት ከዞኑ መሬት በመውሰድ እንቅስቃሴ እያደረጉ ቢሆንም ቀሪዎቹና ዋናዎቹ በክራይና ቀድሞ በዞኑ በጀት በተገነቡ ቤቶች ላይ በመሆን ለምን ዝምታ መረጡ?” የሚሉ ድምፆችም ከየአቅጣጫው ከፍ ብለው ይደመጣሉ።

ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ባለፈው ይፋ ባደረገው ምርመራ ዘገባችን “የአዲሱ ክልል ከህዝብ ፍትሃዊና ዕኩል ተጠቃሚነት አንፃር ምሁራንና የአከባቢው ነዋሪዎች ምን ይላሉ?” በሚለው አንድ የክልሉን ፓለቲካ በቅርበት የሚከታተል ምሁር ስንጠይቅ “ፍትሀዊ እና ተመጣጣኝ መንግስታዊና ፖለቲካዊ ዉክልና ባለማግኘቱ አንኳር በሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሆነ ፖለቲካዊ ጥቅሞችን ለማስገኘት እንዲሁም የልማት ፍትሃዊነት ለማስጠበቅ ግልፅ እና አሳታፍ የህግ ሥርዓት ተዘርግቶ እንድመራ መግባባት ተፈጥሮ መስራት ሲገባ በአሁኑ ወቅት ከዚያ እውነታ በተቃራኒው ተጨባጭ የሴራ እንቅስቃሴ መኖሩን መጠቆሙ ይታወሳል።


Wolaita Times 🙏 በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው