
አብዛኛው የፓለቲካ ጉዳይ አቀንቃኞች መንግሰት ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሰጥ የህዝብ ተጠቃሚነት የመጨረሻ አድረገው ይደሰታሉ፣ አቋማቸውንና ሙግት አቁሞው ዝም ይላሉ ( ሹመት፣ ከእስር የሚወዱትን ስፈታ፣ በንግግር …ወዘተ ) ይሄ ከምን የሚመነጭ ነው? መፍትሔውስ❓በአካባቢው በፓለቲካ የቆዩ ባለልምድ በቀላሉ መንግሥትን በህዝብ ጉዳይ ላይ ማሳመን የሚችሉትን በማግለል ማሳተፍና እውቅና መስጠት ብዙም አልተለመደምና ለዚሁ ነገር ከአከባቢው አመራሮች ጀምሮ ምን ይጠበቃል❓ በየወቅቱ የተከሰቱ የአመራሮች እንዲሁም ሌሎች በህዝብ ጉዳይ ላይ በቅርበት የሚሰሩ ግለሰቦች ልዩነታቸውን ትተው በአንድ መድረክ ሲነጋገሩ አይታዩም፥ እንዴት ቢናደርግ ነው የሚሻለው❓ከፌደራል፣ ከክልል ጋር ያለውን ጤናማ ግንኙነት አጠንክረን ህዝባችን የሚገባውን እንዲያገኝና ተደማጭነት ከፍ እንድል እንዴት ማድረግ ይቻላል? ለዚሁ ሁሉ ችግር ኃላፊነት የሚወስደው ማነው? ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቅብናል❓በሚሉ ቁልፍ ምላሽ በሚሹ ጉዳዮች ላይ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ “የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ” በተነሱ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው አቅርቧል። ዝግጅቱ በሁለት ክፍል የቀረበ ሲሆን ሲሆን የዛሬው ሁለተኛ ክፍል እንደሚከተለው ቀጥታ ቀርቧል።
⏩ ዎላይታ ታይምስ፦አብዛኛው የዎላይታ አከባቢ ፓለቲካ አቀንቃኞች መንግሰት ጊዜያዊ መፍትሔ ሲሰጥ የህዝብ ተጠቃሚነት የመጨረሻ አድረገው ይደሰታሉ፣ አቋማቸውንና ሙግት አቁሞው ዝም ይላሉ (ሹመት፣ ከእስር የሚወዱትን ስፈታ፣ በንግግር …ወዘተ) ይሄ ከምን የሚመነጭ ነው? መፍትሔውስ❓
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ ያልከዉ ነገር ይስተዋላል። ለሕዝብ ታግሎ የታሰረና የተንከራተተ አመራር ከእስር ተፈተው ወደ ሥራ ሲመለስ (ከነበረዉ ያነሰ ቢሆንም ስልጣኑ ) አትደሰቱ ማለት አይቻልም። ምሁራን ከሥራ ገበታ ተፈናቅለዉ ሲሰቃዩ ከርመዉ፣ ወደ ሥራ መመለሳቸዉ አስደሳች ነው ። ነገር ግን መጀመሪያም ሕገወጥ ሥራ የሰራዉ መንግስት እነዚህ እርምጃዎች የሚወስደዉ፣ የፈለገዉን የፖለቲካ ዉሳኔ ካስፈጸመ በሁዋላ ከመሆኑም ባሻገር፤ ተጸጽቶም ሆነ፣ የአካሄድ ለዉጥ ለማድረግ አስቦ አለመሆኑን ማወቁ አስፈላጊ ነው። ሕዝቡ ያነሳቸዉ ጥያቄዎች አለመመለሳቸዉን መዘንጋት አያስፈልግም።
የብልጽግና መራሹ መንግስትም አንድ መገንዘብ ያለበት ነገር፣ በነዚህ ጉዞዎች የዎላይታ ሕዝብ ከቅርጫፍነት የዘለለ ሚና በሌለዉ የዎላይታ ብልጽግና ላይ እምነቱ በከፍተኛ ሁኔታ መሸርሸሩንና ዎሕዴግ እና ዎብን የተሻለ ድምጼን ያስተጋባሉ ብሎ እያሰበ መምጣቱን መካድ አይቻልም። ቀድሞ በተሻለ የሥልጣን እርከን ሆነዉ ለሕዝብ ስለወገኑ የታሰሩ አመራሮች ተፈትተዉ፣ አሁን ብዙም እርባና የሌላቸዉ ሹመቶችን ሲያገኙ ሕዝቡ የሚደሰተዉ እንደ ቀድሞዉ ሊሟገቱለት እንደማይችሉ ስለማያዉቅ ሳይሆን፤ ብያንስ ያለሥራ መንከራተታቸዉ በመቆሙ ተደስተው ነው። ከዛ በተረፈ ሕዝቡ የብልጽግና ፓርቲ ቀልድ ሰልችቶታል፣ እንደ ትግራዩ ሁሉ በኦሮሚያና በአማራ ያለዉ ግጭት እንዲቆም ይፈልጋል።
የፖለቲካ ጥያቄዎቼ አልተመለሱም ብሎ ነው ሕዝቡ የሚያምነዉ፣ የዎላይታ ብልጽግናዎችም በፓርቲው ተደማጭነት አላቸዉ የሚል እምነት የለዉም ሕዝቡ፣ የሕዝቡን ሁኔታ ለሚከታተል ሰዉ ይህን መታዘብ አይከብደዉም። አሁን ሐገራዊ ምክክር በተባለዉም አንዱ አሳሳቢዉ ጉዳይ ይሄዉ ዎላይታ በነማን ይወከል የሚለዉ ነው። ብልጽግና ኦሮ_ማራ መር ወጥ ፓርቲ በመሆኑ እንደ ኢህአዴግ በደቡብነትም ሆነ በተለይ በዎላይታነት የመደመጥ ጉዳይ አይታሰብም። በዎላይታ ላይ ፓርቲው የሚያደርሰዉ የተለዬ ጫና ሌላዉ ምክንያት ነው። ዎሕዴግ እና ዎብን ደግሞ በእነ ፕሮፌሰር መረራ ጉዲናዉ ኮከስ በኩል፣ በሐገራዊ ምክክሩ እንደማይሳተፉ ከኦፈኮ፣ ኦነግ ና ኦብነግ ጋር ሆነዉ አስታዉቀዋል። ብልጽግና ፓርቲ አቋሙን የማይቀይር ከሆነ ዎላይታን በፓርቲ ደረጃ የሚወክል የለም ማለት ነው። ስለዚህ ለዚህ የሚሆን ግዚያዊ ንቅናቄ በዎላይታ ምሁራን ቢሰባሰብና የሕዝቡን ጥያቄ በጥናት ተመሥርቶ እያደራጀ ቢቆይ የተሻለ ይመስለኛል።
⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦ በአካባቢያችን በፓለቲካ የቆዩ ባለልምድ በቀላሉ መንግሥትን በህዝብ ጉዳይ ላይ ማሳመን የሚችሉትን በማግለል ማሳተፍና እውቅና መስጠት ብዙም አልተለመደምና ለዚሁ ነገር ከአከባቢው አመራሮች ጀምሮ ምን ይጠበቃል❓
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ያንን በተመለከተ አሁንም ችግሩ መንግሰት በዎላይታ ላይ የሚያደርሰዉ የተለዬ ጫና ይመስለኛል። በእነ ዳጋቶ ጊዜ የቀድሞ አመራሮች፣ የተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ ምሁራን፣ የሐይማኖት አባቶች ና ወጣቶች እንዲሰባሰቡ ተደርጎ፣ እዉቅና መስጠትም ተካሂዷል። በዞኑ ከተደረገዉ መፈንቅለ መንግስት በሁዋላ መሰል ነገሮች ቀርተዋል። አለማክበርና አለመከባበር ከእዉቀት ማጣት ይመጣልና ሕዝብን ለማንቃት በተለይ Opinion leaders ጠንክረዉ መሥራት አለባቸዉ፣ አንዳንድ ጭቁን ብሄሮችን የሚንቁ ሊህቃንን ተንኮለኛ ወሬ ተቀብለዉ የሚያስተጋቡ ወገኖቻችንም አሉና። በነገራችን ላይ በእናንተ ሚዲያ በኩል ለሕዝቡ ይፋ የወጣ አንድ በእንድ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ተክለወልድ አጥናፉና ገብረ መስቀል ጫላ የተጻፈ ደብዳቤ አይቼ ነበር። በዎላይታ ዞን የ Reconciliation መድረክ እንዲካሄድ ይጠይቃል፣ ያ ሁላችንም እንደምናዉቀዉ መንግስት በዎላይታ ሕዝብ ላይ ባደረሰዉ ኢ_ሕገመንግሥታዊ ጫና አመራሩን በዋናነት ለሁለት እንደተከፈለ ይታወቃል፣ ጫናዉን እንዴት እንጋፈጥ የሚለዉ አለያይቷቸዋል። እኔ በግሌ እነዚህ የቀድሞ አመራሮች እንዳሉት የተገፋፉ አመራሮችንና ሊህቃንን የማስታረቁ ጉዳይ ጊዜ ሊሰጠዉ የሚገባ ጉዳይ አይደለም፣ በአስቸኳይ መደረግ አለበት። ለሕዝቡ ሲባል በጋራ መቆም ያስፈልጋል።
⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦በአካባቢያችን በየወቅቱ የተከሰቱ የአመራሮች እንዲሁም ሌሎች በህዝብ ጉዳይ ላይ በቅርበት የሚሰሩ ግለሰቦች ልዩነታቸውን ትተው በአንድ መድረክ ሲነጋገሩ አይታዩም፣ ይሄ አካሄድ በህዝብ ጉዳይ ላይ ሶስተኛ ወገን ጠላት እጁን እንዲከት አላደረገም ወይ? እንዴት ቢናደርግ ነው የሚሻለው❓
✅ ማሪንዶስ ጦና፦እኔ ይሄንን ጥያቄ መመለስ የምፈልገዉ ከዎላይታ አንጻር ነው። ሲጀመር የዎላይታ አመራር እንዲከፋፈል ያደረገዉም ሆነ የ Reconciliation መድረክ እንዳይካሄድ ያደረገዉ እራሱ ብልጽግና ነው። ከዛ ዉጪ የአጎራባች ሊህቃን ሆነ ሌላ ሩቅ ሶስተኛ ወገኖች በእኛ ጉዳይ ላይ የሚፈተፍቱት፣ እራሱ ብልጽግና ፓርቲ ሕዝቦችን እኩል ስለማያይ ነው። የሚሻለዉ ደግሞ ወንድማማቹ የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝብ አንዱ በአንዱ ጉዳት ዘላቂ ጥቅም ማስጠበቅ እንደማይችል አዉቆ በጋራ መስራት አለበት። ብልጽግና በሁሉም አቅጣጫ የደቡብ ኢትዮጵያን ሕዝብ የፖለቲካ አቅም ገድሏል። ይህን ያደረገዉ ሕዝቡን ከፋፍሎ ነው ፣ለዚህ መፍትሔዉ በጋራ መታገል ነው። በተለይ በአሁኑ ሰዓት ብልጽግና በክልሉ ከፍተኛ ሕዝብ ቁጥር ያለዉን የዎላይታ ሕዝብ የሚያገልለዉ አካሄዱ ክልሉን አስሮ መያዙን ማስተዋል ና በጋራ መታገል ያስፈልጋል።
የአንዳችን ጉዳት የሁላችን ጉዳት ከሆነ፣ በጋራ ጥቅማችን ዙሪያ እዉነተኛ ሶስተኛ ክልል መሥርተን፣ በሚሊተሪ፣ በበጀት፣ በዲፕሎማሲ፣ በፖለቲካ ሥልጣን ድርሻ፣ ከኢትዮጵያ የሚገባንን ድርሻ የምናገኝ ወሳኝ ኃይል የምንሆንበት ቀን እሩቅ አይደለም። ያንን ቁመና ከገነባን ጦርነቶችን ሳይቀር የሚያስቆሙ ሐሳቦችን እስከማመንጨት ልንደርስ እንችላለን። ለሐገሪቷም ከልማትና አካታችነት አንጻር ምሳሌ የሆነ ክልል መፍጠር እንችላለን።
⏩ ዎላይታ ታይምስ ፦ ከፌደራል፣ ከክልል ጋር ያለውን ጤናማ ግንኙነት አጠንክረን ህዝባችን የሚገባውን እንዲያገኝና ተደማጭነት ከፍ እንድል እንዴት ማድረግ ይቻላል ? ለዚሁ ሁሉ ችግር ኃላፊነት የሚወስደው ማነው ? ከእያንዳንዳችንስ ምን ይጠበቅብናል ❓
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ የኢትዮጵያ ችግሮች ብዙ ቢሆኑም፣ በዋናነት ብዙ ችግር ኃላፊነት መዉሰድ ያለበት ብልጽግና ፓርቲ ነው፣ በሐገርም በክልልም ብቸኛ ተጠያቂ ባይሆንም። ግንኙነት ላልከዉ በአሁኑ ሰዓት ብልጽግና መራሹ መንግስት ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልልም ጋር ሆነ ከዎላይታ ዞን ጋር ያለዉ ግንኙነት ጤናማ ነው የሚል እምነት የለኝም። ክልሉ ከተመሠረተበት መንገድ ጀምሮ ትልቅ ችግር አለ። የዎላይታ ሕዝብ የደቡብ ሕዝቦች በወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አመራርነት በከፍተኛ እርከን እንዲወከሉ ብዙ የታገለ፣ ብዙ ፈንጂዎችን የጠረገና የተሰደበ ሕዝብ ነው። ያንን ሕዝብ አግልሎ መሔድ ጤናማ ግንኙነትን አያሳይም። ይህ ማለት ግን ተስፋ የለም ማለት አይደለም፣ መንግስት አሳታፊ እርምጃዎችን መዉሰድ፣ የሕዝብን ጥያቄዉች ማዳመጥና መመለስ እንዲሁም ሕገመንግሥታዊና ሰላማዊ የፖለቲካ አካሄዶችን ከተከተለ ዎላይታ እና ደቡብ ኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆኑ፣ኢትዮጲያም ተስፋ አላት።
ከእያንዳንዳችን የሚጠበቀዉ ደግሞ ከአባቶቻችን የወረስነዉን ሰላማዊ እና ሕገመንግሥታዊ ትግል አጠናክሮ ማስቀጠል ነው። አመሰግናለሁ 🙏
⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ እኛም ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ የቀረበው ዝግጅቱ በሁለት ክፍል የቀረበ ሲሆን ምናልባት የመጀመሪያ ክፍል ዝግጅት ( https://wolaitatimes.com/?p=4681) ያልተከታተሉ በአስተያየት በተቀመጠው አድራሻ ገብተው ማግኘት እንደሚችል በአክብሮት እንገልፃለን።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ቃለምልልስ ነው