ሀሰተኛ መረጃዎችንና የጥላቻ ንግግሮችን ለማስቀረት የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ ማድረግ ከጀመረ ወዲህ በህግ የበላይነት ላይ አበረታች ለውጥ እየተስተዋለ መሆኑን የዎላይታ ዞን ዓቃቤ ህገ መምሪያ ገለፀ ።
በመምሪያው የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዋና ሥራ ሂደት የህግ የበላይነትን በማረጋገጥ ዘላቂ ልማት ለማረጋገጥና ሰላማዊ አካባቢ ለመፍጠር በትኩረት እየሠራ መሆኑን የዋና ሥራ ሂደቱ አስተባባሪ አቶ አሸናፊ ቶራ ተናግረዋል ።
በሀገራችን ሆነ በዓለም ደረጃ የህግ የበላይነትን ማረጋገጥ ለዜጎች እኩልነትና ጉልበተኛው ጉልበት የሌለውን ባለ ሥልጣንም ሥልጣን የሌለውን ሰው መብት እንዳይደፈጥጥ በማድረግ ለሁሉም ሰው በእኩል እንዲዳኙ የሚያስገድድ የህግ መርህ ነው ።
ይህን መርህ በማረጋገጥ ለሁሉም ዜጎች ሰላማዊ የሆነ አካባቢ በመፍጠር ልማትን ለማስቀጠል ዜጎች የሀገራቸውን ህግጋት በማወቅና በመጠበቅ ከተጠያቂነት እንዲድኑ ለማድረግ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት የዞኑ ዓቃቤ ህግ መምሪያ ሲሰጥ እንደቆየ በመምሪያው የልዩ ልዩ ወንጀል ጉዳዮች ዋና የሥራ ሂደት አስተባባሪ የሆኑት አቶ አሸናፊ ቶራ ገልፀዋል ።
አቶ አሸናፊ ቶራ ከዜና ክፍላችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት ባለፉት ሦስት ወራት ውስጥ በሀሰተኛ መረጃ ስርጭትና የጥላቻ ንግግር ለማስቀረት የወጣውን አዋጅ ተግባራዊ ለማድረግ በተለያዩ የሚዲያ አውታሮች በተለይም በፌስቡክ ላይ ህገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ግለሰቦች ወደ ህግ በማቅረብ የእርምት እርምጃ ሲያስወስድ እንደቆየ ተናገረው ወደፊትም የሀገር ህልውና ፣ የህዝብ ደህንነትና አንድነት እንዲሁም ልማት ሥራዎች ምንም እንቅፋት ሳያጋጥማቸው እንዲቀጥሉ ለማስቻል ከዞናችን የሚነሱ ሀሰተኛ የፌስቡክ ገፆች ላይ የሚለቀቁ የጥላቻ ንግግርና ሀሰተኛ መረጃዎችን የሚያሰራጩ አካላትን በበቂ መረጃና ማስረጃ በማረጋገጥ ወደ ህግ ለማቅረብ ከኢትዮ ቴሌኮምና ብሄራዊ መረጃና ደህንነት ኤጄንሲ ጋር በቅርበት እየተሠራ ነውም ብለዋል ።
የህግ የበላይነት ዋና ዓላማ ዜጎችን መቅጣት ሳይሆን ህግን በማክበር የራሳቸውንም ሆነ የሌሎችን መብት በመጠበቅና በማስጠበቅ ሰላምን በማስፈን ልማትን ማረጋገጥ ነው ያሉት አቶ አሸናፊ ማንም ይሁን ማን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ የህግ የበላይነትን አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ ወንጀል ሰርቶ ከተገኘ ወደ ህግ ቀርቦ ተገቢውን ቅጣት እንደሚያገኝ መታወቅ አለበትም ብለዋል ።
ከ6ኛው ሀገራዊ ምርጫ ጋር ተያይዞ ዜጎች ሀሳብን በነፃነት የመግለጽ መብት ላይ ገደብ ያልተበጀ ይመስል ማንም እየተነሳ የሌሎች ግለሰቦችን ፣ድርጅቶችን ፣ቡድኖችንና ኃይማኖቶችን መልካም ዝና በሚያጎድፉና መብታቸውን የሚደፈጥጥ ፤ ክብራቸውን የሚያዋርድ የጥላቻ ንግግሮችና ህዝብን ፣ግለሰብንና መንግሥትን ወደ ብጥብጥ የሚመሩ የሀሰት መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲቆጠቡ መምሪያው ያልተቋረጠ ትምህርት ለመስጠት ያገኘውን አጋጣሚ ሁሉ ሲጠቀም እንደቆየው ሁሉ ወደፊት አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።
በዞናችን የህግ የበላይነትን በማስፈን ልማትን ለማስቀጠል እንዳይቻል በህዝቦች አንድነት ላይ ፤ በዜጎች ሰላም ላይ እንዲሁም በሀገረ መንግሥት ህልውና ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ የሚያሳርፉ የጥላቻ ንግግሮችን በሚያሰራጩ የማህበራዊ ሚዲያ ተጠቃሚዎች ላይ ከማስጠንቀቂያ እስከ ቀላል እስራት የሚደርስ ህጋዊ እርምጃ ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል ሲል የዞኑ ኮሙኒኬሽን መምሪያ ዘግቧል።