
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባትን በዎላይታ በይፋ አስጀመሩ።
የኮቪድ-19 መከላከያ ክትባቱ ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩን አቶ እርስቱ ይርዳውን ጨምሮ ከፍተኛ የደቡብ ክልል አመራሮች በተገኙበት በወላይታ ዩኒቨርስቲ ህክምና ጤና ሳይንስ ኮሌጅ ኦቶና ሆስፒታል በይፋ ተጀምሯል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ትናንት በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው በክልሉ ከዛሬ ጀምሮ ለሚሰጠው የኮቫክስ ክትባት 108 ሺ ዶዝ ተዘጋጅቷል።
በመጀመሪያው ዙርም በስራቸው ምክንያት ለቫይረሱ ይበልጥ ተጋላጭ ለሆኑ የጤና ባለሙያዎችና ለዘርፉ ድጋፍ ሰጪ ሰራተኞች ቅድሚያ የሚሰጥ ይሆናል።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ራሳቸው ተከትበው የክትባት ስራውን በይፋ ካስጀመሩ በሗላ ባስተላለፉት መልዕክት እንዳሉት የጤና ባለሙያዎችን ቅድሚያ መክተቡ ሌላውን ዜጋም መታደግና የመከላከል ስራውን ማገዝ ነው።
ባለሙያዎቹ ባለፉት ጊዜያት ለህይወታቸው ሳይሰስቱ ህዝቡን በማገልገልና ህይወቱን በመታደግ ረገድ የከፈሉት መስዋዕትነት የሚመሰገን እንደሆነም ጠቁመዋል።ይህም ባይሆን ኖሮ ጉዳቱ ከፍተኛ ይሆን እንደነበርም ተናግረዋል ።
ችግሩን ወደ ጥሩ አጋጣሚ ልንቀይረው ይገባል ያሉት አቶ እርስቱ ከዚህ አኳያ ሀገራችን ለራሷ ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ድሃ ሀገራት ህዝቦች ተጠቃሚነት ጥረት አድርጋለች ሲሉም ገልጸዋል።
ክትባቱ የመከላከል ስራውን የሚያግዝ ቢሆንም ዋናው ጉዳይ የመከላከል ስራው መሆን እንዳለበትም ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ አሳስበዋል።
አሁን የገባው ክትባትም ከህዝቡ ቁጥር አንጻር በጣም አነስተኛ ነው ያሉት አቶ እርስቱ ትልቁ መሳሪያ ራስን መጠበቅ እና ጥንቃቄ መሆን አለበት ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ሃላፊ አቶ አቅናው ካውዛ
የመጀመሪያው ዙር ክትባትም ቫይረሱን ፊት ለፊት እየተፋለሙ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎችንና ድጋፍ ሰራተኞችን ታሳቢ ያደረገ ነው ሲሉ ገልጸዋል ።ክትባቱ አስትራ ዜኒካ የሚባለው እንደሆነም አስረድተዋል ።
ክትባት በሁለት ዙር የሚሰጥ ሲሆን ከመጀመሪያው ክትባት ከ8 እስከ 12 ሳምንት ባሉት ጊዜያት ውስጥ ሁለተኛው ዙር ክትባት የሚሰጥ እንደሆነም ተነግሯል።
የደቡብ ክልል ህብረተሰብ ጤና ዳይሬክተር አቶ ማሙሽ ሁሴን ከ63 ሺ በላይ የጤና ባለሙያዎች ክትባት እንደሚያገኙ ጠቁመው ይህም በመሆኑ የመከላከል ስራውን ውጤታማ እንደሚያደርገው ተናግረዋል ሲል የክልሉ ኮሙኒኬሽን ቢሮ ዘግቧል።