1000016684

በህዝብ በጋራ ጉዳይ ላይ ተሰባስበው ለመማማር እርግማንን እንዴት እንበጥሰው❓በተለይም የዎላይታው ሹም ሽር ዘመቻ ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር መቼ መፍትሔ ያገኛል❓

ደቡብ በተለይም በዎላይታ የአመራሮች ሹም ሽር ዜና በሽ ነው። እንዲያውም ሹም ሽር በማድረግ ውድድር ቢኖር የዋንጫ ተሸላሚ ሳይሆን አይቀርም። በአከባቢው ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር ተዘንግቶ የሹም ሽር ዜና ከመብዛቱ የተነሳ አብዛኛው ሰው አመራር ለምን ይሾማል ለምንስ ምን ሰርቶ ወረደ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ትቶ በተቀየረበት ጊዜ ሁሉ በእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫ ድንኳን ጥሎ ዝግጅት ማውጣት ለጥቂት ቀርቷል።

በዛሬው ዕለትም የዞኑ ምክርቤት ዞኑ በዘርፈብዙ ችግር በገባችበት ወቅት ያለአንዳች ተጠያቂነትና ምክንያት የግለሰቦች ሹም ሽረት ዘመቻ ስለመቀጠሉ ይፋ አድርጓል።

በክልሉ በየትኛውም አከባቢ ተግባራዊ ያልሆነ በተለየ መንገድ በዎላይታ የአመራሮች ሹም ሽረት ማብዛት፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለአከባቢው ልማት በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ በኢኮኖሚ ሆነ ፓለቲካ ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ያመዘኑ እንደሆነ አንድ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህርና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተው ነበር።

በአከባቢው የህዝብ በደል የወለደው ትግል ከህፃን እስከ አዋቂ አሰልፈው የነበረው ጉዞ በጥቂቶቹ ላይ በግለሰብ ደረጃ የህይወት መስዋዕትነት፣ የአካል መጉደል፣ ከስራ መፈናቀል፣ የፍትህ መጓደል፣ ስደትና እስራት ቢያተርፍም ለሰፊው ህዝብ ጥቅም ዛሬም ነገም ከጎኑ ለመቆምና ሊካራከርለት የሚችል ትውልድ እንዲፈጠር በጎ ሚና መጫወቱ ባይካድም ወደ ዋናው አላማ ሳንደርስ መሀል ላይ አቋርጠው ዝምታ መምረጥ ተገቢ አይደለም የሚሉ ድምፆች በተደጋጋሚ ይደመጣሉ።

አሁን አሁን የትናንቱ እስራትና መገፋት ለህዝብ ውግንና በማሳየታችን ደርሷል የሚሉ ተዘናግቷል። ከዛ እስራትና መከራ በግለሰብ ደረጃ ስለወጣን በህዝባችን ላይ ከትናንቱ የባሰ አድሏዊ አሰራር በግልጽ ተግባራዊ እየሆነ እንዴት ዝም እንላለን ? የትናንቱ መከራና እስራት በየግላችን ጥቅም የሚያስጠብቁ ዕድል እስኪናገኝ ነው እንዴ? ትናንት በደስታ፣ በሀዘን እንዲሁም በዛ ሁሉ ውጣውረድ አብሮ የተሰለፈውን ህዝብ ለማን ትተን ነው አብዛኞቻችን ዛሬ ላይ ዝምታ የመረጥነው ⁉️

ትግሉ ፕሮፌሰር ታከለ ታደሰን አውርደን ዩንቨርስቲውን ከደረጃ በታች አድርገው ለማዘጋት እየሄደ ያለው ዶክተር ጉቼ እንዲመጣ ነበር እንዴ? አቶ ተስፋዬ ይግዙን ከአከባቢው አሸሽተነው በምትኩ የህዝብ አደራ ተሸክመው ዝምታ በመረጡ አቶ ገብረመስቀል ጫላ ተክተን ዝም ለማለት ነው እንዴ የነበረው ⁉️

በተጨማሪም ትግሉ በእነሱ ዳግም እውነት ወጥቶ መምጣት መቃወም ሳይሆን እነ ዳጋቶ፣ አሰፋ፣ አሸናፊ፣ ጥበቡ፣ ያለው፣ ጎበዜ፣ ሚካኤል እና ሌሎች በግለሰብ ደረጃ ወደ ስራ እስኪመለሱ ነበር እንዴ?

ቆይ የትግላችን የመጨረሻው ግብ በየማህበራዊ ሚዲያ እኔ አቦስቶ፣ ቀይመስቀል፣ ማረሚያና ግብርና ኮሌጅ ታሰርኩ በሚል በየቀኑ እንደ ዋናውን የህዝብ ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ያደረገ ሰው ለመኩራራት ነበር እንዴ ወገኖቻችን ⁉️ የመጣንበትን መንገድ እንመልከት እንጂ ዋናው ግባችን ምን ነበር ? ለህዝብ መከራ፣ እስራትና ስደት ማየት የሚያኮራ ቢሆንም ያንን አላማ ዛሬ ላይ የት አደረስነው? ወደየት አድርሰን ነው የጀግና ጀግና የምንጫወተው ⁉️በሚል ሁላችንም ራሳችን መጠየቅ እንዳለብን አሳስበዋል።

በመሆኑም እውነተኛና ሀቀኛ የህዝብ ጥያቄዎች እንዲመለሱ በምናደርገው ጉዞ ውስጥ ውሸትና ጠልፎ የመጣል እንቅስቃሴ ማካተት፣ ከህዝብ ጥቅም ይልቅ የራስ ጥቅም ብቻ አብዝቶ መጮህና የተፈለገው ሲገኝ ዝምታ መምረጥ፣ በየደረጃው የሚገኙ ህዝብን በመንግሥት ደረጃ ስልጣን ያላቸውን ወደ ህዝባቸው እንዲቀርቡ በሚያስችል መንገድ ከመስራት ይልቅ የበለጠ እንዲርቁ ዘመቻ በመክፈት በእርስበርስ ጥላቻ በሚፈጠረው አንድነት ማጣት ምክንያት ለሶስተኛ ወገኖች ጥቅም አሳልፎ እንዲሰጥ ማድረግ፣ ትኩረታችንን በዋናው ህዝብ ጉዳይ ማድረግን ትተን በትግል ሂደቱ ላይና በሚከሰቱ ጥቃቅን ጉዳዮች ምክንያት እርስበርስ መናናቅና የትግሉን አቅጣጫ ወደ ግለሰቦች በማድረግም አላማችንን መሳት ይጠቀሳሉ።

እርስበርስ አለመደማመጥና ለታላላቆቹ በተለይም ልምድ ያላቸው በህዝብ ጉዳይ ላይ ሀሳባቸውን እንዲገልጹ እንዲሁም አበርክተዋቸውን እንዲያወጡ ማድረግን መዘንጋታችን ዛሬ ላይ ከላይ በጥቂቱ የተጠቀሱ የቤታችን ጉድለቶች አንድነትን በማጣታችን ምክንያት ገናና የነበረው ህዝብ በከፍተኛ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፓለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ይገኛልና ቆም ብለን አስተውለን በቁጭት የመጣንበትን መንገድ ገምግመን መፍትሔ ሊናበጀው ይገባል የሚለው አንገብጋቢ ጉዳይ እንደሆነም ይጠቁማሉ።

በተለይም ሁሉም እያለን በሀሳብ ልዩነት ምክንያት በስልጣን ባሉት እና ከስልጣን በወረዱት ላይ የምናደርገው፣ እርስበርስ ክፍፍል በሚያሰፋ አኳኃን ጠልፎ የመጣል የትግል አካሄድ እነሱን በሚተኩ ግለሰቦች ላይም አሉታዊ ጫና በመፍጠር ከህዝብ ጥቅም ይልቅ ለግላቸውና ለሾመው ፓርቲ ብቻ እንዲያገለግሉ፣ በእርስበርስ ጭቅጭቅና ጥራጥሬ መሀል ሶስተኛ ወገን ጠልፎ እንዲጥል፣ በህዝብ ላይ የተደቀነው ዘርፈብዙ አንገብጋቢ ጉዳዮች በወቅቱ መፍትሔና ትኩረት እንዳያገኙ እንዲሁም ከአካባቢያችን ተተኪና ልምድ ያለው አመራር እንዳይወጣ የሚያደርግ አደገኛ ልምምድ እየፈጠረ ነውና በጊዜ የለንም መንፈስ የትግል አካሄዳችን ከሀገሪቱ ነባራዊና ወቅታዊ ሁኔታ አንፃር በተገቢው መመርመርና ማስተካከል ያስፈልጋል።

በፊት የነበሩ ልዩነቶችን በውይይትና እርቅ ዘግተን ያለጥላቻ በጋራ ተጋግዘን መጓዝ ይበጀናል፥ የትናንቱ ልዩነትና ቁርሾ እንተወውና በጋራ አላማ አንድነት ተሰልፈን ለህዝባችን ብቻ ሳይሆን ሌሎች በተመሳሳይ መንገድ ለሚጎዱም ባለፈው ለማካሄድ ታቀደው የነበረው የእርቅና የሰላም መድረክ የሚመለከተው ሆነ ተስፋ ተጥለው የነበረው እውን እንዲሆን እናስተባብር! አለበለዚያ በቡድን ጨዋታ መሀል ዳኛው ሶስተኛ ወገን ሆነው ስቃያችንን ያበዛል” የሚሉ ሀቀኛ ድምፆች እየተደመጡ ነው።

እነኚያ ሀቀኛ ድምፆች ምናልባት ከላይ የተጠቀሱ መሠረታዊ ሀሳቦችን አንዳንድ ሌሎች ወገኖች “እንዴት የዎላይታ ህዝብ ልዩ አድርጋችሁ ታቀርባላችሁ” ለሚሉ ምላሽ አላቸው “አዎ የዎላይታ ህዝብ ጉዳይ ልዩ ነው። አዎ የዎላይታ ማህበራዊ፣ ፓለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ቀውስ ከየትኛውም ሀገራቱ ክፍል የተለየ መልክ ያለው ነው። አዎ የዎላይታው ችግር በሀገሪቱ ትግራይ በተካሄደ እና በአማራ ክልል እየተካሄደ ከሚገኘው እርስበርስ ጦርነት የበለጠ የባሰ ነው” ይላሉ።

“በሀገሪቱ በተደረጉና እየተደረጉ ባለው ጦርነት ከየትኛውም ብሄር በበለጠ ከፊት ተሰልፈው መስዋዕትነት እየከፈሉ የሚገኙት ከዎላይታ ስለመሆናቸው መከላከያ ሚኒስትር ስለቁጥራቸውና መስዋዕትነታው ምስክር ነው። በሀገሪቱ ከተሞች በየጎዳናው በአባታቸው በእናታቸው አቅፍ ሆነው ማደግና መማር የሚገባቸው ህፃናት፣ ወጣቶችና ሴቶች በአከባቢው ምንም የስራ ዕድል ባለመፈጠሩ ምን እየሰሩ እንደሆነ ለፈጣሪ ብላችሁ አልተመለከታችሁም እንዴ? በዎላይታ ከመንግሥት ዩንቨርስቲዎች በዲግሪ ከተለያዩ ኮሌጆች በዲፕሎማ የተመረቁ ከ200 ሺህ በላይ የተማሩ ስራአጥ ወጣቶች ስለመኖራቸው የማያውቅ ኢትዮጵያዊም አለ እንዴ⁉️” በሚል ይጠይቃሉ።

አክለውም “ለመሆኑ ትናንት ከአንድ ሰው ዕድሜ በፊት ከራሱ የተደራጀ ሀገር የነበረው በኢትዮጵያ ስር ከሌሎች ጋር በእኩልነትና በፍትሀዊነት የሚገባውን ተከልክሎ የሚገባኝ ይሰጠኝ እያለ እየጮኸ የሚገኘው መደመጥ የለበትም እንዴ❓ አዎ የዎላይታ ህዝብ በደልና ከክብሩ ዝቅ ብለው እየኖረ ያለበት ሁኔታ ልዩ ያደርገዋል። የህዝብ ትግሉና የሁልጊዜ ሙግት መነሻም ለሌላው ካለው ጥላቻ የመነጨ ሳይሆን በሀገሪቱ ህግ ጥላ ስር የሚገባውን ክብርና ጥቅም ለማስጠበቅ ነው” በሚልም ለጥያቄዎቹ ምክንያታዊ ምላሽ ይሰጣሉ።

በተለይም ዎላይታ ዞን “ደቡብ ኢትዮጵያ” በሚል የተዋቀረ ትንሹ ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል መዋቅር በሚኖሩበት ወቅት የገዥው ፓርቲ ወይንም የመንግስት መሪነት ሚና ነበራቸው፥ በነበረው አደረጃጀት ውስጥ ከህዝብ ቁጥርና ተያያዥ እውነታ አንፃር ውክልና ተገቢ ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን በትንሹ ክልል ያንን ጭምር በማጣት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ቀውስ በተጋለጠበት ወቅት ጠንካራ አንድነት እና አመራር የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ መሆናችንን ማወቅ አስፈላጊ እንደሆነም ተሰምሮበታል።

ያም ሆነ ይህ በህዝብ በጋራ ጉዳይ ላይ ተሰባስበው ለመማማር እርግማንን እንዴት እንበጥሰው? በተለይም የዎላይታው ሹም ሽር ዘመቻ ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር መቼ መፍትሔ ያገኛል ? የሚለው እስካሁን ምላሽ ያላገኘ የቤት ስራ ሆኖ ቀጥሏል።

ዘገበው በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቤታሎ የተጠናቀረ ነው