
እንደሚታወቀው የዎላይታ ህዝብ ከራሱ ከተደራጀ ሀገርነት ወደ ኢትዮጵያ ከተቀላቀለ በኃላ በስሙ የሚጠራ የዞን መዋቅር እንኳን ተከልክለው በ1993 ዓ.ም በርካቶች የህይወት መስዋዕትነት፣ የአካል ጉዳተኝነት፣ ከስራ መፈናቀል፣ እስራትና ስደት መስዋዕትነት ከከፈሉ በኃላ የዎላይታ ዞን መዋቅር ማግኘቱ ይታወቃል።
አሁን ላይ በተለያም በዎላይታ ሶዶ ከተማ የሚገኙ የውስጥ ለውስጥ አስፓልት፣ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ፣ የዎላይታ ጉተራ አዳራሽና በሌሎች አከባቢዎችም የተሰሩ ተጨባጭ ልማት ስራ የተሰራው የዞን መዋቅር ከተዘረጋ በኃላ በህብረተሰቡ ተሳትፎ ታክሎበት የተሰሩ ስለመሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ።
በተለይም ልማት ጠምቶ ለነበረው ህዝብ በትንሹም የመዋቅር ነፃነት በማገኘቱ እንዲሰራ ዕድል የተገኘው የህዝብ ውግንና ያላቸው አመራሮች ተረጋግተው የሚሰሩበት ጊዜ በመስጠቱ እንደሆነ የዋና አስተዳዳሪዎች የአመራር ዘመን ቆይታ ስንመለከተው ምስክር ሊሆን ይችላል።
በአከባቢው ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር ተዘንግቶ የሹም ሽር ዜና ከመብዛቱ የተነሳ አብዛኛው ሰው አመራር ለምን ይሾማል ለምንስ ምን ሰርቶ ወረደ የሚለውን መሠረታዊ ጥያቄ ትቶ አመራር በተቀየረበት ጊዜ ሁሉ በእንኳን ደስ አላችሁ መግለጫ ተጠምዷል።
በግልጽ እየታየ ባለው ሁኔታ በክልሉ በየትኛውም አከባቢ ተግባራዊ ያልሆነ በተለየ መንገድ በዎላይታ የአመራሮች ሹም ሽረት መብዛት፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለአከባቢው ልማት በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ በኢኮኖሚ ሆነ ፓለቲካ ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ያመዘኑ እንደሆነ አንድ የዎላይታ ሶዶ ዩንቨርስቲ መምህርና የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ አስረድተው ነበር።
በተለይም የብሄሩ ተወላጆች ከፌደራል፣ ከክልል እንደሁም ከዞን ጀምሮ በተመደቡበት ኃላፊነት ቦታ ተረጋግተው እንዳይሰራ በመደረጉ ይባስ ብሎ “ደቡብ ኢትዮጵያ” በሚል የተዋቀረ ትንሹ ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል በነበረው አደረጃጀት ውስጥ ከህዝብ ቁጥርና ተያያዥ እውነታ አንፃር በመንግሥትና በገዢ ፓርቲ መርነትም ተገቢ ውክልናና ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን በትንሹ ክልል የነበረውን ጭምር በማጣት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ቀውስ የተጋለጠው ከዚህ የሚመነጭ እውነታ እንደሆነ አይካድም።
ለማጠቃለል የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ከታች በስም ዝርዝራቸው ባስቀመጠው መረጃ ላይ እንደምንመለከተው ዎላይታ የዞን መዋቅር በይፋ ካገኘ ወዲህ 13 ግለሰቦች ያስተዳደሩ ሲሆን በአከባቢው በተሰራው ተጨባጭ ልማት አንፃር ስንመለከተው የመጀመሪያዎቹ 6ቱ አስተዳዳሪዎች የሰሩት ከእነሱ በኃላ ያስተዳደሩ 6 (+1) የሰሩት እጅጉን ለመላው ህዝብ ግልጽ በሆነ መንገድ ይገመታል።
ዎላይታ በዞን መዋቅር ከተደራጀ ወዲህ በዋና አስተዳዳሪነት የመሩት ዝርዝር 👇
- አቶ ማሞ ጎደቦ 1993 ዓ.ም
- አቶ ፍሬዉ አልታዬ 1993 _1996 ዓ.ም
- አቶ አማኑኤል ኦቶሮ 1996_2000 ዓ.ም
- አቶ ኃይለብርሃን ዜና 2000_2003 ዓ.ም
- አቶ ተስፋዬ ይገዙ 2003_2005 ዓ.ም
- አቶ ኢዮብ ዋቴ 2005_2009 ዓ.ም
- ዶ/ር አሥራት ጤራ 2009_2010 ዓ.ም
- ዶ/ር ጌታሁን ጋረደዉ 2010 ዓ.ም
- አቶ ዳጋቶ ኩምቤ 2011_2012 ዓ.ም
- ዶ/ር እንድሪያስ ጌታ 2013 ዓ.ም
- አቶ አክሊሉ ለማ 2014_2015 ዓ.ም
- አቶ ሳሙኤል ፎላ 2016 ዓ.ም
- አቶ ጴጥሮስ ወ/ማሪያም ከነሃሴ 2016 ዓ.ም ጀምሮ ….
በመሆኑም የዎላይታ ታይምስ እንደ አንድ በአከባቢው ጉዳይ ላይ በቅርበት እንደሚሰራና ኃላፊነት እንደሚሰማው ሚዲያ ከላይ በአከባቢው የታዘበውን መሠረታዊ ችግር የጠቆመ ሲሆን የአከባቢው ተወላጅ መብት ተሟጋቾች፣ ፓለቲካኞች፣ ምሁራን፣ ወጣቶች፣ ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተወያይተውና በጋራ ተመካክረው መፍትሔ ማበጀት ይጠበቅባቸዋል።
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው