1000016827

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት አንድ በተነሱ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን ጥሪያችንን ተቀብለዉ፣ እንኳን ደህና መጡ ወደ ሚዲያችን።

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ እንኳን ደህና ቆያችሁን። ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያዉ ቤቴ ነው። በድጋሚ ዕድሉን ስለሰጣችሁኝ አመሰግናለሁ።

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ እሺ ቀጥታ ወደ ጥያቄያችን እንግባ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ከዎላይታ ዞን፣ እጅግ በጣም ብዙ ቁጥር ያላቸዉ ሕጻናት፣ አዲስ አበባን ጨምሮ ወደ ብዙ የኢትዮጵያ ትልልቅ ከተሞች ይፈልሳሉ። የአዲስ አበባ ጎዳናዎችን የሞሉት የዎላይታ ሕጻናት እንደሆኑ ይነገራል። ለዚህ መንስኤዉ ምንድነዉ?

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ አዎ ልክ ብለሐል፣ በጣም የሚያሳዝን ነገር ነው። ገና የመጀመሪያ ደረጃ መማሪያ እድሜ ክልል ዉስጥ የሚገኙ፣ እንዳለ በሊስትሮነት፣ በሚዛን፣ በሱቅ በደሬቴነት፣ በቆሎ አዟሪነት፣ በብረታብረት ናየፕላስቲክ ጠርሙስ ለቀማና የመሳሰሉ ሥራዎች ላይ የተሰማሩ የዎላይታ ሕጻናትን በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ማየት የተለመደ ነገር ነው። እኔ ነገሩ አሳስቦኝ ልጆቹንም የተወሰነ ነጥቦችን ለመያዝ ካገዘኝ በሚል አነጋግራለሁ በየቦታዉ።

አብዛኛዎቹ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርታቸዉን አቋርጠዉ የሚመጡት በድህነት ምክንያት ነው። ወላጅ ያላቸዉም፣ አንድ ወላጅ ብቻ ያላቸዉና ወላጅ የሌላቸዉም ይገኙበታል፣ በብዛት ወንዶች ቢሆኑም የሴቶቹም ቁጥር በጣም ብዙ ነው፣ በግምት 30_40% ሴት ሕጻናት ይመስለኛል። የሚሰደዱት በዋናነት ከድህነት የተነሳ ነው፣ በቂ ምግብና ለአንድ ተማሪ የሚያስፈልጉ መሠረታዊ ነገሮችን ስለማያገኙ ነው የሚሰደዱት።

ለልጆቹ በዞኑ እየሰሩ ለመማር የሚመች ሁኔታ የለም፣ ከዞኑ ሕዝብ ብዛት ጋር የሚመጣጠን ትልቅ ከተማ ስለሌለ፣ ወደሌሎች አካባቢዎች በዋናነት ወደ አዲስ አበባ ይሰደዳሉ። ሌላዉ ዎላይታ ዞን ብቻ ስለሆነ ችግሩ በዞን የፖሊሲ አቅም መቋቋም ከሚቻለዉ እጅግ በጣም በላይ ነው። እናም ተመጣጣኝ የመፍትሔ እርምጃ ስለማይወሰድ ችግሩ ተባብሶ እየቀጠለ ነው። ልጆቹ ጓደኞቻቸዉ ትምሀርት አቋርጠዉ ሄደዉ፣ በአዲስ አበባ ሰርተዉ እየኖሩ መሆኑን ስለሚሰሙ፣ ሲርባቸዉና ተስፋ ሲጨልምባቸዉ፣ ስደትን ይመርጣሉ።

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ ልጆቹ ስለሚኖሩበት ሁኔታ ልትነግረን ትችላለህ? በአዲስ አበባስ ቁጥራቸዉን በግምት ማስቀመጥ ይቻላል?

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ያዉ አነኝህ ስደተኛ ሕጻናት ከ14 እና 15 ዓመት በታች ያሉትን ብቻ እንገምት ብንል፣ ከ10ሺዎች እስከ 100ሺዎች ሊደርሱ እንደሚችሉ እገምታለሁ ቁጥራቸዉን። በገቢ ደረጃ እንደየተሰማሩበት ሥራ ይለያያል። ከ100_250 ብር በቀን የሚያገኙ ልጆችን አነጋግሬአለሁ። ምግብም የሚበሉት በጣም በአነስተኛ ዋጋ ከሚሸጥባቸዉ ቦታዎች ሰብሰብ ብለዉ ይበላሉ አጋጭተዉ። አንዳንዶቹ ከየምግብ ቤቱ የተራረፈዉን ይበላሉ። በጎዳና የሚያድሩት ቁጥራቸዉ ቀላል አይደለም፣ አንዳንዶቹ ደግሞ 5 እና 6 እየሆኑ ቤት ተከራይተዉ ይኖራሉ። ኑሮ ከእጅ ወደ አፍ ነው ለምንለዉ እንኳን በቂ ነገር የላቸዉም። የበለጠ የሚያሳዝነዉ ሴቶቹ ሕጻናት በጣም በሚያሳዝን ሁኔታ ለጾታዊ ጥቃት ተጋላጭ ናቸዉ።

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ ይህ ነገር ከሌሎች አካባቢዎች ጋር የሰማይና የምድርን ያህል በሚራራቅ ደረጃ በዎላይታ ሕጻናት ላይ እንዴት ሊበዛ ቻለ ሰደቱ ?

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በእኔ ግምት ዎላይታ በኢትዮጵያ ባለዉ” የሐገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ” አለመግባባት ዉስጥ የተጠመደ ሕዝብ ነው። ለዘመናት ሲቀጣ የኖረ ሕዝብ ነው። የፖለቲካ ስልጣን እንዳይኖረዉ የተደረገ፣ የመዋቅራዊ ተንኮል ሰለባ የተደረገ፣ በሕዝብ ቁጥርና በጀት አለመጣጣም እንዲማቅቅ የተፈረደበት፣ በቀየዉ ልማት እንዳያገኝ የተፈረደበት፣ በተቻለ መጠን በኢኮኖሚ ጫና ከቀዬዉ ተሰዶ አማርኛ ወደሚናገሩ የሐገሪቷ ከተሞች ተሰዶ የተዋሄደ እንዲሆን የሚፈለግ ሕዝብ ነው። መሰል ፖለቲካዊ ተንኮሎች ድምር ዉጤት ይመስለኛል፣ ግን እነኝህን ችግሮች ከግምት ያስገባ ከፍተኛ ጥናትና ምርምር ይፈልጋል፣ ከመንግሥት ፈቃደኝነት ጀምሮ ከፍተኛ የአለም አቀፍ ተቋማትም ድጋፍ ያስፈልጋል።

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ችግሩን መፍታት የሚመለከታቸዉ አካላት እነ ማናቸዉ ? ምን ያህል እንቅስቃሴስ እያደረጉ ነው።

✅ ማሪንዶሶ ጦና፧ በአጭሩ የዞኑ፣ የክልሉ ናየፈደራል መንግሥት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሲሆን፣ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ በሕጻናት ዙሪያ የሚሰሩ ግብረሰናይ ድርጅቶችና አለም አቀፍ ተቋማት ናቸዉ። የዎላይታ ሕዝብም ይህ የልጆቹ ችግር ትኩረት እንዲያገኝ መታገል አለበት። ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ 🙏

⏩ ዎላይታ ታይምስ፦ እኛም ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዛሬው የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ባለፈው በሁለት ክፍል በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን። #WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏