
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት የሀገር ሽማግሌዎችንም ጭምር በመግዛት የአንድን ህዝብ ታሪክና ክብር ከማጠልሸት እንዲቆጠብ ተጠየቀ።
በሌላ በኩል በዎላይታ ጉተራ ባለፈው “በምስር ወጥ” ተታለው ህዝብን በማዋረድ በኩራና የሸጠው የሀገር ሽማግሌ ተብሎ ንግግር ያደረገና እንዲናገር ያቀዱ በህግ እንዲጠየቁ የአከባቢው ወጣቶች ጠይቀዋል።
የዳሞታ ሥረ-ወመንግስት ‘ሀ’ ተብሎ የተጀመረበት፣ ታላቁ የዎላይታ ህዝብ ሥልጣኔ የተጠነሰሰበት፣ ንጉስ ሞቶሎሚ የተዋጋበት እና በአቡነ ተ/ኃይማኖት ክርስትና የተቀበሉበት፣ ጥንታዊ የቅድስት ስላሴ ቤ/ክን የሚገኝበት፣ ከ58 ሺህ አመት በፊት የሰው ልጅ መኖር የጀመረበት ሞቼና ቦራጎ ዋሻ፣ በ1279 ዓ.ም አቡነ ተክለኃይማኖት ጠመዝማዛና አድካሚ ዳገት በመውጣት ተመላልሰው ይሰብኩ የነበረበት መንገድ “የጦሳ ፈንግያ” አልፎ ወደ ተራራው አናት በመውጣት ንጉሡንና ሌሎች ክርስትና እንዲቀበሉ ያደረጉበት፣ የዎላይታ ሶዶ ከተማን ቁልቁል እያየ የቆመ፣ የብዙ ቱሪስቶች ቀልብ መግዛት የቻለ፣ ባለ ግርማ ሞገሱ ”ዳሞታ ተራራ” ግርጌ ባለው ጉታራ ቆሞ የሀገር ሽማግሌ ካባ የለበሰና በኩርናውን በምስር ወጥ ለመቀየር የከጀለውን በህግ አለመጠየቅ ማናችንም ከታሪክ ተጠያቂነት እንደማያድን አሳስበዋል።
አንድ ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአከባቢው ሽማግሌ “በምስር ወጥ የታለለው ሽማግሌ” በወቅቱ የተናገረው ምን አንድምታ አለው ብለን ለጠይቅነው ምላሽ ሲሰጥ “እንዲያው ከራሱ ዕድሜ በማይሞላ ከ1974ቱ የኢትዮጵያ አብዮት በኋላ በአከባቢው በተለያዩ መልከዓምድር ይኖሩ የነበሩ በርካታ በቁጥር ትንንሽ የሆኑ ነባር ሕዝቦችን በመጨፍለቅ በመንግሥት የተሰጠ የጋራ ስም መሆኑን እያወቀ በዚህ ዕድሜው ለገንዘብ ብሎ እንዲናገር መደረጉ በክልሉ ከፍተኛ አመራሮች ሆን ብለው የዎላይታ ህዝብ ማንነትና ክብር ዝቅ ለማድረግ እንደሚሰራ ያረጋግጣል” ብለዋል።
በተጨማሪ የአከባቢው ምሁራን፣ ፓለቲከኞች፣ የሀይማኖት አባቶች እንዲሁም በየደረጃው ተሰምነት ያላቸው ግለሰቦች ባለፉት አመታት በዞኑ የፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ ለሀገራቸውና ለአጎራባች ህዝቦች ጭምር በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደረስ ለማድረግ ችላ መባሉ ዛሬ ላይ አቅመ ፓለቲካ ያልደረሱ ግለሰቦች ሁሉ በህዝብ ክብርና ማንነት ላይ ጥቃት እንዲሰነዘሩ መንገድ መክፈቱንም እኚህ አባት አክለዋል።
በሌላ በኩል ይሄንን በህዝብ ማንነት ላይ የተቃጣ የተደራጀ ዘመቻ ነው ያሉት አንድ የፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ “ክልሉን ለህዝብ መብትና ክብር ውግንና ያላቸውን በማስወገድና የፖለቲካ የመደራደር አቅምን በማሳጣት የውስጥ አንድነት እንዳይኖር በማድረግ በኢኮኖሚያዊ ዘርፍም ከህግና አስፈጻሚዎች እውቅና ውጪ የነበረውን ልማት ከልክሎ በኢፍትሃዊነት ለሌላው አሳልፈው እየሰጠ በማህበራዊ ዘርፍም የዎላይታ ሕዝብ ሕልውናውን የምፈታተኑ ቀጥታ በክልሉ ፕረዚዳንት ትዕዛዝ “ዎላሞይ ኑና ሻሜና”፣ “እንተ ኑስ አዋ፥ ኑን እንቴስ ናታ” የመሳሰሉ አደገኛ ስውር አጀንዳዎች በአንድነት ስም ህዝቡ አንገቱን እንድደፋ በየጊዜው እንዲናገሩ በዕቅድ እየተሰራ ስለመሆኑ ማሳያ ነው” በሚል አስረድተዋል።
በመሆኑም በዚሁ አሳፋሪ ድርጊት የተሳተፉ ማንም ቢሆን በይፋ ይቅርታ እንዲጠይቁና በህግ አግባብ ተጠያቂ እስኪሆኑ ድረስ ማንነቱን የሚወድ ሁሉ ድምፁን ከፍ አድርገው ማሰማት እንዳለበት እንዲሁም የክልሉ መንግስት እንደዚህ አይነት የህዝብ ቁጣ ከሚቀሰቅስ አደገኛ ድርጊት እንዲቆጠብ የፈደራል መንግስት ጠልቃ እንዲገባ ጥሪ አቅርበዋል።