
“ሰሞኑን በአጠቃላይ ዎላይታ መዋቅር እየተካሄደ ካለው ሹም ሽር ዘመቻ ጀርባ ማን አለ? የሹም ሽረት አብዮት ምን አላማ አለው ?” የህዝብ እንቆቅልሾች ሆነው ዘልቋል።
እንደሚታወቀው የዎላይታ ዞን በሀገሪቱ ከየትኛውም አከባቢ በላይ ወደ 2 መቶ ሺህ የሚጠጋ ከታወቁ ከፍተኛ ዩንቨርስቲዎችና ኮሌጆች የተመረቁ የስራ አጥ ወጣቶች የሚገኙበት፤ ፓለቲካዊ ቁውስ በፈጠረው ችግር ህፃናት በጨቅላ ዕድሜያቸው በሀገሪቱ ጎዳናዎች ሁሉ የስቃይ ህይወት እየገፉ ይገኛሉ። የወጣቱ ተስፋና የስራ ዕድል አማራጭ በግዴታም በውዴታም ውትድርና ብቻ እየሆነ ነው። በአከባቢው በመንግስት ትኩረት ተሰጥቶት የወጣቶች የስራ ዕድል የሚፈጥሩ እንዱስትሪና ሌሎች ተቋማት ባለመሰራቱ ችግሩን ከጊዜ ወደ ጊዜ አባብሶታል።

ከዚህም የተነሳ ሴቶችና ወንዶች አስቸጋሪውን ሞትና ስቃይ ፊትለፊት እየተጋፈጡ ወደተለያዩ ስደት ሀገር ያቀናሉ። ዕድል ቀንቷቸው ከሞት ተርፈው ወደ አረብ፣ ደቡብ አፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት የገቡ የተቀረውን ቤተሰቦቻቸውን በቻሉት መጠን ያግዛሉ።
የህዝብ መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በተመለከተ ለበርካታ ዓመታት አብዛኛው ይሰራል ተብሎ ቃል የተገባ ይሁን መሠረት ድንጋይ የተጣለበት ፕሮጀክት ከማስጀመሪያ ፎቶ አላለፈም። ህዝብ እየሆነና እየታዘበ ባለው ተስፋ ቆርጠው Nu Deriyaaba Xoossi erees (የእኛን ነገር ፈጣሪ ያውቃል) በሚል ዝምታን መርጧል።

ሌላው ደግሞ በአከባቢው ከህዝብ ተጠቃሚነት አንፃር ምን ለውጥ ያመጣል ተዘንግቶ በግልጽ እየታየ ባለው ሁኔታ በክልሉ በየትኛውም አከባቢ ተግባራዊ ያልሆነ በተለየ መንገድ በዎላይታ የአመራሮች ሹም ሽረት መብዛት፣ የንግዱ ማህበረሰብ እንዲሁም ባለሀብቶችን የማሳደድና ተረጋግተው እንዳይሰሩ የሚወሰዱ እርምጃዎች ለአከባቢው ልማት በጎ ሚና ከመጫወት ይልቅ በኢኮኖሚ ሆነ ፓለቲካ ተሳትፎ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ለማድረስ ያመዘኑ እንደሆነ ይነገራል።

በተለይም የብሄሩ ተወላጆች ከፌደራል፣ ከክልል እንደሁም ከዞን ጀምሮ በተመደቡበት ኃላፊነት ቦታ ተረጋግተው እንዳይሰራ በመደረጉ ይባስ ብሎ “ደቡብ ኢትዮጵያ” በሚል የተዋቀረ ትንሹ ክልል ከመደራጀቱ በፊት በትልቁ ከ56 ብሄር ብሄረሰቦች በላይ አብሮ በአንድ ክልል በነበረው አደረጃጀት ውስጥ ከህዝብ ቁጥርና ተያያዥ እውነታ አንፃር በመንግሥትና በገዢ ፓርቲ መርነትም ተገቢ ውክልናና ተጠቃሚነት የነበረ ቢሆኑም አሁን በትንሹ ክልል የነበረውን ጭምር በማጣት ለማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፓለቲካዊ ቀውስ የተጋለጠው ከዚህ የሚመነጭ እውነታ እንደሆነ አይካድም።
የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በተለይም ባለፉት ስድስት አመታት በዞኑ የተከሰቱ ቁልፍ ጉዳዮችን በእያንዳንዱ ቀን ትዝብትና ይፋዊ ዘገባ ያሳለፈ በመሆኑ አሁን ላይ በዎላይታ አጠቃላይ መዋቅር ላይ እየተካሄደ ካለው ሹም ሽር ዘመቻ ጀርባ ማን አለ? የሹም ሽረት አብዮት ምን አላማ አለው ? የሚለውን በጥልቀት ይረዳል።

ለጊዜው ከሹም ሽር ጀርባ ማን አለ የሚለውን ጥያቄ ትተንና ወደኃላ በመጣውና በሄደው ላይ ትንታኔ ከመስጠት ይልቅ እውነተኛ ለህዝብ የሚበጀው አካሄድ የትኛው ቢሆን ይሻላል በሚለው ትኩረት ቢደረግ እንመርጣለን።
በአጭሩ የጥሎ ማለፍ ፓለቲካ አይጠቅመንም። ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ መወገድ አለበት። ምናልባት ትናንት ሁላችንም እንደ ግለሰብ እንደ ህዝብም በሌላኛው ቡድን ጉዳት ደርሶብናል። ያ ሌላኛው በሄደበት መንገድ ዛሬም ዳግም እንሄዳለን ማለት ተገቢ ወይንም ትክክለኛ አይመስለንም። ምክንያቱም አካሄዱ ጥሎ ማለፍ ጨዋታ አይነት ከሆነ የወደቀው አይተኛም፦ መልሰው ቡድኑን ይዞ መምጣቱ አይቀርም።
በግልጽ እያየን ባለነው ሁኔታ አንፃር በመሀል ደግሞ አንገብጋቢ ጥያቄ ያለውና ለልማት የተጠማ ህዝብ ይጎዳል። ከዚህ ሁሉ ከእልህ የቡድን ጨዋታ ለመውጣት በፊት የነበሩ ልዩነቶችን በውይይትና እርቅ ዘግተው ያለጥላቻ በጋራ ተጋግዘው መሄድ እንደሚያዋጣ ብዙዎች ይስማሙበታል።
ህዝቡ በእልህ የቡድን ጨዋታ ምክንያት “በፓለቲካ አካሄድ ልዩነት ምክንያት ብቻ ዳርና ዳር ሆነው የሚገኙ ወገኖች ወደ አንድነት፣ መደማመጥ፣ መተባበር እንዲሁም በጋራ ጉዳይ በሆኑ የህዝብ የልማት ፍላጎቶች ላይ የበኩላቸውን እንዲወጡና በአንድነት በመሰለፍ በጎ ሚና ሊወጡ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንዲደርሱ ለማድረግ ሰብሳቢዎችን በእግዚአብሔር ተስፋ አድርጎ እየጠበቃቸው ይገኛል።
የመጣንበት መንገድ በህዝብ ዘላቂ ጥቅምና ዋስትና ሲባል ሁሉም ከእልህ፣ ከጠልፎ ከመጣልና ከሴራ ፖለቲካ ወጥቶ ሕዝቡን ማዕከል በሚያደርጉ ጉዳዮች ላይ ስምምነት እንዲፈጥር እንዲሁም ህዝቡ ላይ የተጋረጠበትን አደጋ በጋራ ቋሞ መመከት እንዲቻል አስቀድሞ የውስጥ አንድነት ማጠንከርና ከጎረቤት እና ከሁሉም የሀገሪቱ ሕዝቦች የነበረውን ጤናማና ዘመናትን የተሻገረ መስተጋብር አጠናክሮ ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ምክክር ያስፈልጋል።
በመሆኑም የዎላይታ ታይምስ እንደ አንድ በአከባቢው ጉዳይ ላይ በቅርበት እንደሚሰራና ኃላፊነት እንደሚሰማው ሚዲያ ከላይ በአከባቢው የታዘበውን መሠረታዊ ችግር የጠቆመ ሲሆን የአከባቢው ተወላጅ መብት ተሟጋቾች፣ ፓለቲካኞች፣ ምሁራን፣ ባለሀብቶች፣ ወጣቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት በሙሉ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት ተወያይተውና በጋራ ተመካክረው መፍትሔ ማበጀት እንዳለበት ጥሪ ያቀርባል።
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው