
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ዎላይታ ዞን በተለይም በቦሎሶ ቦምቤ፣ ቦሎሶ ሶሬ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ ወረዳዎች የወባ ወረርሽኝ መከሰቱን ከስፍራው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
አንድ የአከባቢው ነዋሪ ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ሁኔታውን ሲገልፅ “ከሰኔ ወር ጀምሮ በቦሎሶ ሶሬ ወረዳ ጥዮ፣ ጫማ እና ማጣላ ሂምቤቾ ቀበሌዎች ህብረተሰቡ በወባ ወረርሽኝ እየተሰቃየ ነው” በሚል ገልጸዋል።
በዚህ ወባ በሽታ የተጠቃውን ቤተሰብ አባል ሶስት ጊዜ ወደ ሀኪም ቤት መውሰዱን የገለፀው አስተያየት ሰጪው በአከባቢው ባለው ጤና ጣቢያ ማስገባቱን ተናግሮ በቂ ህክምና አቅርቦት ባለመኖሩ ወደሌላ ሀኪም ቤት መውሰዱን አስረድተዋል።
“በሚያሳዝን ሁኔታ በአከባቢው ዘንድሮ በወባ በሽታ ተጠቅተው ከሁለት ጊዜ ያላነሰ ሀኪም ቤት ያልገባ ሰው የለም፥ አሁን ደግሞ ብዙ ሰዎች በቂ ህክምና ባለማግኘታቸው እየሞቱ ነው እባካችሁ ይሄንን የህዝብ ስቃይ ይፋ ተደርጎ ትኩረት እንዲያገኝ አድርጉ” ሲል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ተማፅነዋል።
ሌላኛው በኪንዶ ኮይሻ ወረዳ በማንኣራ ቀበሌ ወላጅ እናቱንና ወንድሙን በወባ በሽታ ወረርሽኝ ታመው በአከባቢው የህክምና አቅርቦት ባለመኖሩ በሌ ከተማ የመጀመሪያ ሆስፒታል ቢያመጣቸው እናቱን ማዳን እንዳልቻለ በመግለፅ በቀበሌያቸው ባለፍው ሰኔ እና ሐምሌ ወር እናቴን ጨምሮ 7 ሰዎች በወባ በሽታ ሞተዋል፥ አሁንም ህክምና ማግኘት ስላልቻሉ ታመው በቤታቸው የሚገኙ ሰዎች እንዳሉ አስረድተዋል።
በቦሎሶ ቦምቤ ወረዳ አንድ ጤና ጣቢያ ባለሙያ በማገልገል ላይ የምትገኝና ስሜ አይጠቀስ ያለች የህክምና ባለሙያ” በጤናው ዘርፍ መረጃ በየጊዜው ሪፖርት የሚደረግ ቢሆንም መንግሥት አስፈላጊውን የጤና ግብዓት እያቀረበ ወረርሽኙ ለምን ተከሰተ የሚል ተጠያቂነትን ለመሸሽ ሲባል በወረርሽኝ የተጠቁ ህብረተሰብ ክፍሎች በሽታና ሞት በበላይ አካላት እንዲሰወሩ ተደርጓል” ስትል ለዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ገልፃለች።
በተጨማሪም በአከባቢው በርከት ያሉ አዋቂዎችና ህፃናት በሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች ህክምና የሚከታተሉ፣ የሞቱ እንዲሁም ወደ ጤና ተቋማት መምጣት ያልቻሉት በየቤታቸው እንዳሉ በመግለፅ በወረርሽኙ ምክንያት እየተሰቃዩ የሚገኙ ዜጎችን ለመታደግ መንግስት፣ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጂት፣ ሚዲያዎችና ጉዳዩ የሚመለከተው ሁሉ በአስቸኳይ እንዲደርስላቸው ጥሪ አቅርባለች።
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በዎላይታ የህብረተሰቡን ጤና “አስቀድሞ ለመከላከልና ለመቆጣጠር” በሚል በመቶ ሚሊዮኖች ከዓለምአቀፍ ተራድኦ ድርጅቶች የሚመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ እየዋለ በመሆኑ የወባ፣ የኩፍኝ እና ሌሎች የወረርሽኝ በሽታዎችን መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ እያደረገና በርካቶች እንዲሞቱ እያደረገ ስለመሆኑ በዎላይታ ዞን በተለያዩ መንግስት ሆስፒታሎች የሚሰሩ ዶክተሮች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
በዞኑ በአብዛኛው ሆስፒታሎችና ጤና ጣቢያዎች የበሽታ መቆጣጠርና መከላከል ስራ አስቸጋሪ ከማድረጉ ባለፈ ከዞን ባለሙያዎች ጭምር ወረርሽኝ ወደተከሰተበት አከባቢ በጊዜው ለመሄድ የተመደበው ገንዘብ ለሌላ አላማ በመዋሉ በየአካባቢው የሚከሰቱ ወረርሽኝ ለመቆጣጠር አስቸጋሪ እያደረገ እንደሆነም የጤና ባለሙያዎች ያደረሱት መረጃ ያመለክታል።
ሰሞኑን በዞኑ በተለይም በቦሎሶ ቦምቤ፣ ቦሎሶ ሶሬ እንዲሁም በሌሎች አንዳንድ ወረዳዎች ስለተከሰተው የወባ ወረርሽኝ በተመለከተ ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የሚመለከታቸውን አካላት ለማግኘት ያደረገው ጥረት ያልተሳካ ቢሆን ምላሽ እንዳገኘን እንመለስበታለን። #Ethiopia #Wolaita
በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው