
“ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳያመልጠን” በሚል ስለጠቆሙት የዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” መጽሐፍ ላይ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና የቀረበ ጥልቅ ሂሳዊ ዳሰሳ… ክፍል 1
“ጸሓፊዉ መግብያዉ ላይ ገጽ 17 የሚከተለዉን ይላል”ሀገር የትርክት ዉጤት ናት። ትርክታቸዉ ከመጻዒ ዕጣ ፋንታቸዉ ጋር የገጠመላቸዉ ሀገራት የሀገረ መንግስት እና የብሔረ
መንግስት ግንባታቸዉን አጠናቀዉ ኢኮኖሚያዊ ፉክክር እና ዕሳቤያቸዉ በሉላዊ የአለም ማኀበረ ፖለቲካ ገዢ እንዲሆን እየተፋለሙ ይገኛሉ።
ሀገራችን ለዚህ የሥነ መንግስት ዑደት ገና ናት። ለምን ቢባል የተቃርኖ ትርክት በኅብር ከማደግ ይልቅ በጨቋኝ ተጨቋኝ ትርክት ማባጀታችን ዋጋ አስከፍሎናል።” የሐገረ መንግስት እና የብሔረ መንግስት ግምባታዉ አለማለቁን አምኖ መጀመሩ ጥሩ ሆኖ፤ በኅብር ከማደግ ይልቅ ጨቋን ተጨቋኝ ትርክት በመምረጣችን ነው ብሎ የተዛባ ድምዳሜ አስቀምጦ ይነሳል። በዚህ ጉዳይ ላይ ብዙ አልልም መጽሐፉን እያነበብን ስንሔት ሐሳቦቹን በየፈርጁ እንገመግማለንና።

ጸሐፊው ክፍል አንድን፣ የኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ትርክት እና ማጠንጠኛዎቹ ብሎ አቅርቧል። በዛዉ ስር ምዕራፍ አንድ ላይ ደግሞ፣ ነፍጠኝ’ነት፣ ትምክተኝነት እና ጠባብነት፣ በተናጠል እያስቀመጠ ምልከታዉን ጽፏል። በገጽ 20 ላይ፣ ነፍጠኝነት ከዐፄ ምኒልክን አገዛዝ ጀምሮ፣ በደቡብና በሰሜን የተለያዬ ትርጉም ነበረዉ፣ ብሎ ጥሩ ነጥብ አስቀምጧል።
በገጽ 21 ላይ በዐፄዉ ዘመን በደቡብ፣ አንድ ወታደር 2 _10 ገባሮች፣ መኮንን ደግሞ 30_80ገባሮች እንደነበሩት ለእዉነታዉ የቀረበ መረጃ አስቀምጧል። ገበሬዉ የዐፄ ሚንልክ ወታደሮች በመሆናቸዉና በአብዛኛው የኦርቶዶክስ ክርስቲያን በመሆናቸዉ “አማራ” ይበላቸዉ እንጂ ሰዎቹ፣ የአማራ፣ የኦሮሞ፣ የትግራይ እና ጉራጌ ገዢ መደቦችሞ የተዉጣጡ መሆናቸዉን ያትታል፣ ያም እዉነትነት ያለዉ ነው፤ ግን የአማራዎቹን መብዛትና የአማርኛ ቋንቋን ሚናም ጨምሮ ቢያስቀምጥ የበለጠ ጥሩ ነበረ። መሬት የሚያገኙት ከባዶ ቦታ ካልሆነም ነበር ነዋሪዮችን በመንቀል እንደነበረም አስቀምጧል፤ ምናልባት የሚጎድለዉ አገላለጹ መለዘቡ ነው እንጂ ለምን በዝርዝር አልተቀመጠም አልልም።
ጸሓፊዉ ከግዜ በሁዋላ ነፍጠኝነት ና ትምክተኝነት ለአማራ ተሰጠ፣ ለማጥቃት አገለገለ ይላል፣ ፍረጃ በመሰረቱ ባይበረታታም፣ ከተጠቀሱት አስተሳሰቦች ጋር የሚያያዝ ፖለቲካ ኢትዮጵያ ዉስጥ እንዳለ እንዴት መካድ ይቻላል? ጠባብነት ለኦሮሞ ፖለቲከኞች ተሰጠ፣ ብሎ አሰቀምጧል፣ በተመሰነ ደረጃ ቢያስማማም፤ የተፈረጁ አካላትም የፈበረኳቸዉን የአጸፋ ፍረጃዎች አይጠቅስም። ጸሐፊው ይህን ያደረገዉ ለኦሮ_ማራ ዲስኩር ምቹ መደላድል ለመፍጠር ይመስላል።
በገጽ 28 በኢትዮጵያ የሥልጣን መሠረት ከተወሰነ ጊዜ በሁዋላ ደቡቡ እየሆነ ሄዷል ይላል፣ ደቡብን የያዘ ያሸንፋል ይላል፣ ትግራይ ለደቡብ ሩቅ ነው ይለናል። በሚገርም ሁኔታ ትግራይን ነጥሎ ከደቡብ ጋር የሥነ ልቡና ሆነ የባህል ቅርበቱ የሰለለ ነዉ ይላል። ግራ የሚያጋባዉ፣ ትግራይን ከስልጣን ለማራቅ የሔደበት ርቀት ነው፣ ለመሆኑ የአማራና የትግራይ ባህል ተቀራራቢ እና ተወራራሽ መሆኑ እንዴት ጠፋዉ እና ትግራይ ከደቡብ ስለምትርቅ ያለስልጣን ትኑር ?
የሚያሸንፈዉ ለደቡብ የሚቀርበዉ ከሆነ፣ ትግራይ ሽንፈቷን ትቀበል? ወይስ ሁሉንም አሸናፊ ና የሥልጣን ባለቤት የሚያደርግ መንገድ ትፈልግ? ህወሓት መራሹ ኢህአዴግ ስልጣን የያዘዉ የትኛዉን የደቡብ ኃይል ይዞ ይሆን? እንደዉም ቅርበቱ ያኔ ለብዓዴን አልነበረም? ጸሓፊዉ በአቢሲኒያዊ ፉክክርና እልህ ዉስጥ ገብቶ ዘባርቋል።
እዛዉ ገጽ ላይ፣ በአንድ ወቅት ኢሕዴን የብሔረሰብ ጭፈራ ሲያሳይ፣ ህወሓት ለስልጣን ማስጠበቂያ የመረጠዉ መንገድ ፣ ታጋዮችና የትግራይ ሕዝብ ነዉር ና ከባህል ያፈነገጠ መሰለዉ፣ ብሎ አስደንግጦን ሳይበቃዉ ቀጥሎ፣ ስለዚህ ኦሮሞና አማራን ማጋጨት እና ማግለል የስልጣን ማስጠበቂያ ተደረገ፣ ብሎ ከባድ እዳ የሚያስከትል ብሎም እያስከተለ ያለ ትርክት ፈብርኳል። ለመሆኑ እንደዚህ አይነት ከባድ ተጽዕኖ ያለዉ ሐሳብ የጠጅ ቤት ወሬ ይመስል፣ ያለ ማስረጃ ይቀርባል? የብሔረሰቦችስ ጭፈራ ህወሓት ለስልጣን ማስጠበቂያ የፈበረከዉ ነው ? በቀኃሥ እና በደርግ ጊዜ የነበረዉስ የብሔረሰብ ጭፈራ የምን ማስጠበቂያ ጭፈራ ይሆን? መቸስ እነሱም ብሔረሰቦችን እየሰበሰቡ ያስጨፍሩ ነበረ።
ጸሓፊዉ ምዕራፍ ሁለት፦ ሰንደቅ አላማና የተቃርኖ ትርክት ብሎ ያስቀመጠዉ ክፍል ከሞላ ጎደል ጥሩ ሆኖ፣ ከአቢሲኒያ ነገስታትን ብቻ ሳይሆን የአህመድ ግራኝን አርማም ለማካተት ሞክሯል፣ ያም ለማካተት የተደረገ ጥረት ነውና እናበረታታለን። የተቀሩ ሕዝቦች ታሪክ ከባንዲራ ጋር የተያያዘ ታሪክ ይኑረዉ አይኑረዉ ጸሐፊዉ ምንም ሳይል አልፉል።

አሁን ላይ ያሉትን ሐሳቦች በሶስት ከፍሎ ቢያስቀምጥም ያ እሱን ትዝብት ላይ የሚጥለዉ ነው። የአሁኑን ባለኮከቡን ባንዲራ የሚቃወሙ ጎራዎች አንድ አይነት ቢሆኑም ሆን ብሎ ለማብዛት በሚመስል አኳሐን የይሁዳ አንበሳ አርማና አርማ የሌለዉ የሚፈልጉ ይላል።
ከዛ ባለፈ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ሁሉም የተቀበለዉ ከሆነና አርማዉ በኢትዮጵያ የሐይማኖትና የብሔሮች እኩልነትና በጋራ የመኖሮ ተስፋ የሚያመላክት የኮከብ አርማ ጉዳቱ ምን እንደሆነ አሳማኝ ምክንያት አላስቀመጠም። ነፍጠ’ኛና የታሪክ አፍራሽ እየተባባሉ መፈራረጅን ለመተቸት የሄደበት የ false equivalence ያስተዛዝባል። ጸሐፊው ኮከቡን የማስቀዬር ፍላጎቱን መደበቅ ቢፈልግም ፣ አልተሳካለት።
ምዕራፍ 3 የጭቆና ሥሪትና ትርክቱ ዳንኤል የብሔሮች ጥያቄ የኢትዮጵያ ልዩ ክስተት እንዳልሆነ፣ በአለም ደረጃ የፖለቲካ ንቅናቄዎች፣ የግጭትና የአለም ጦርነቶች ሰበብ፣ በከፍተኛ ደረጃ ከ1980ዎቹ ወዲህ የተጻፈበት ርዕሰ ጉዳይ፣ ታዳጊ (ያላደጉ ይላል እሱ) እና በቅኝ ተይዘዉ የነበሩ ሀገራት ብቻ ሳይሆንእንደ ካናዳ፣ ፖርቱጋል፣ እንግሊዝ፣ ቤልጅየም ያሉ ሀገሮች ዋና ጉዳይ መሆኑን ገልጾ ይጀምራል፣ ከጭፍን ማጥላላት ወጥቶ ይህን እዉነት ማስቀመጡን አድንቀን ሳንጨርስ ግን ዩጎዝላቪያን ጨሶቪየት ኅብረትንና ከቼኮዝላቫኪያን የበተነ ጉዳይ ነው ብሎ ደህና የጀመረዉን የአንቀጹን ሐሳብ ይበትናል።
ለመሆኑ እነዚህን ሐገራት የበተነዉ የብሄር ጥያቄ ነው ወይስ የተያዘበት መንገድ? መበተንስ ከተባበሩት መንግስታት ቻርተር እንኳን ብንነሳ በጎ ነገር ሊሆን አይችልም?ዳንኤል የብሔረሰብ ጥያቄ በምዕራቡና በምስራቁ አለም በተለያዬ መንገድ እንደሚፈታ አስቀምጦ፣ የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ፣ ወደምስራቁ አጋድሎ የቻይናንና የሶቢየት ኅብረት መንገድ መሆኑን ይጠቅሳል።
በዘመናዊት ኢትዮጵያ የብሔረሰቦች አስተሳሰብ ሀገር በቀል ሳይሆን ከዉጪ የተቀዳ ነው፣ጰበማለት ግልጽ ያልሆነ ሐሳብ ያስቀምጣል። ጰለመሆኑ አስተሳሰብ እንደ ፈጦና ዳማከሴ የግድ ሐገር በቀል ሊሆን ይገባል? ሐገር በቀል አስተሳሰብስ እንዴት ያለ ይሆን? ተማሪዮቹ በነበራቸዉ ዉስን እዉቀት በሀገራቸዉ የነበረዉን ጭቆና ለመፍታት ሞከሩ እንጂ፤ ያልነበረን ጭቆና እንደ ልቦለድ የፈበረኩ ለማስመሰል ለምን አስፈለገ?
የዋለልኝ ጥያቄ የተማሪዎች እንቅስቃሴ፣ የኢትዮጵያን ዘመናዊ ፖለቲካ ስለበየነ፤ ከዛ የተለዬ ትንታኔና መፍትሔ ሲቀርብ አይታይም የሚለዉ ዳንኤል፣ የኢትዮጵያ መንግስት አተያይ በፖለቲካችን ሲገልጽ፣ አንደኛ፣ ሶስት ሺ ዘመን ታሪክ ያላት፣ ሚኒሊክ የሚወደስባት እና ስለጭቆና የማይወራባት። ሁለተኛ፣ ሚኒልክ በቀኝ ግዛትና በወረራ የፈጠራት። ሶስተኛ፣ በመሐል የምትገኝ ይላል፣ እራሱን የሶስተኛው ጎራ አባል ማድረጉ ይመስላል፤ የጎራዉን ምልከታ ባያብራራም፣ የመጀመሪያውን ጎራ ሐሳብ በሌላ ጎራ ሽፋን ለማምጣት የተደረገ ጥረት ይመስላል።
ገጽ 50 አካባቢ በኢትዮጵያ የብሔር፣ የመደብና የሁለቱም ጭቆና ነበረ የሚሉ አተያዮች እንደነበሩ ይገልጽና የብሔር ጭቆና ጉዳይ እስካሁንም እንደተቀጣጠለ የቀጠለዉ አስተሳሰቡ ስልጣን ና ሚዲያ ስለያዘ ነው ይላል።
የሕዝብ የልብ ትርታ ስለሆነስ አይደለም? የማያዳግም አስተማማኝ ምላሽስ ተሰጥቶታል? ወጥ ፓርቲ ነኝ የሚለዉ ብልጽግናስ በብሔር ጭቆና አስተሳሰብ ነው የተደራጀዉ ? ሚዲያዎች ስለብሔር ጭቆና እያወሩ ነው የሚዉሉት ወይስ ከአማርኛ ዉጪ የሚወራዉ ሁሉ የብሔር ጥያቄ ነው ? ኢትዮጵያ ዉስጥስ ሚዲያዎች የተያዙት በብሔረሰብ መብት አቀንቃኞች ነው ? በዎላይታ የሕዝበ ዉሳኔ ዉጤት ለማዛባት ኢትዮጵያ ቴሌብዥን በዋዜማዉ የተዛባ ዘገባ አሰራጭቶ በብሔር መብትና በሕገመንግስቱ ላይ ሽንት መሽናቱን ዳንኤል አልሰማም ይሆን?
የሚኒሊክ የደቡብ ወረራና መስፋፋት ያስከተለዉ ኩርፊያና መገፋት አለ የሚሉ ምሁራን አሉ፣ ብሎ ሓሳቡን እንደማይገዛዉ በዘዴ ያስቀምጣል። ኢትዮጵያ ን ከቀይ ባህርና ከአባይ ዉጪ ለማድረግ ቀኝ ገዢዎች እነ እንግሊዝ፣ ጣልያንና ፈረንሳይ ጋር የተደረገዉ ትግል አንዱና ዉጫዊ የሀገረ መንግስት ግንባታ ጥረት ሲሆን፣ ሁለተኛው የመጀመሪያው ለማክሸፍ ሚኒልክ ወደ ደቡብ፣ ምስራቅ ና ምዕራብ ሄዶ የማካተትና የማጽናት ሥራ ሰርቷል ብሎ ሐሳቡን አስቀምጧል። እነማን እንደተካተቱና እነማን እንደጸኑ ለይቶ አላስቀመጠም።
የዎላይታዉን አይነት የሚኒልክ ወረራና ጭፍጨፋ ማካተት ብሎ ሊያልፈዉ ነው … ከላይ የጠቀሰዉንም የነሚኒሊክ ምክንያት በማስረጃ አላስቀመጠም። በደሎችና ቅያሜዎች በዚህ ወቅት የተፈጠሩት ነፍጠኝነትም እንደመዘዝ የመጣዉ፣ በወቅቱ የተወሰኑ ማኅበረ ሰቦች የሥልጣንና የመሬት የበላይነትን በማግኘታቸዉ የተነሣ የተገፉ ማኀበረ ሰቦች “የተገፋነዉ በማንነታችን ምክንያት ነው “የሚለዉን ማሰብና በዚያም መታገል ጀመሩ፣ በማለት እዉነትም አንዳንዶች እንደሚሉት የተረት አባትነቱን ዳንኤል አስመስክሯል።
የበለጠ የሚያሳስበዉ ጠቅላይ ሚኒስትር ተብዬዉ “ዳንኤል ጻፈ፣ ሳይሆን ተጠበበ ማለቱ” ነው፣ ይሄ ምን ማለት ምን እንደሆነ ገብቶት ይሁን? ስለጪሰኝነትስ? ስለለከት የለሽ በደሎችስ? ሁለተኛ አማርኛን ብቸና ብሔራዊ ቋንቋነት፣ የኦርቶዶክስን በመንግሥት ሥር መሆን፣ የኤርትራን ፈዴረሽን ፈረሳን፣ የመከላከያና የሐገር ዉስጥ ሚኒስቴር የሥርዓቱ አገልጋይነትን እንደ ችግር ያስቀምጣል፣ የማድበስበስ ነገሮች ቢኖሩም የተጠቀሱ ችግሮች በግሌ የምስማማባቸዉ ናቸዉ።
ሶስተኛ፦ የተሣትፎ ጥያቄን ያስቀምጣል ያስማማል። አራተኛ፦ ማርክሲዝም መስፋፋቱ ነው ይላል ፣ በርግጥ ይህም የራሱ አስተዋጽኦ ማበርከቱ አይካድም። ዋናዉ መታወቅ ያለበት ተማሪዮቹ በማርከስ ሆነ በስታሊን መነጽር ሐገራቸዉን ተመልክተዉ፣ የታያቸዉን እዉነታ አስቀመጡ እንጂ፣ ልቦለድ ደረሱ እንዴ? በአሜሪካና በአዉሮፓ የኢትዮጵያ ተማሪዮች ሕብረቶች የብሔር ጥያቄን ወደ መቀበል ቀስ በቀስ መምጣታቸዉን ጸሓፊዉ በቁጭት ማስቀመጡ ትዝብት ላይ ይጥለዋል። ሕወሓት፣ ኦነግና ሻዕቢያን በአንድ ላይ አስቀምጦ ኢትዮጵያን እንደ ቅኝ ግዛት አይተዉ መፍትሔው መገንጠል ነው ማለታቸዉን አስቀምጧል።
ነገር ግን የሕወሓትና ኦነግ ማኒፈስቶ ክለሳ እስከ ሽግግር መንግስት ተሳትፎ፣ ፈደሬሽን ተቀብለዉ ብዙ ጥረት ማድረጋቸዉን ዳንኤል ማንሳት አልፈለገም። የኢህአፓ ና መኢሶንን ልዩነትም፣ በጥሩ ሁኔታ አትቷል። ደርግ በአፈጻጸም ካልሆነ በቀር በርእዮተ ዓለምና በመርሕ ደረጃ ከኢሕአዴግ የተለዬ የብሔረሰብ ጭቆና አተያይ ያለዉ አይመስልም፣ ብሎ ከባድ ስህተት አስቀምጧል።
በመጀመሪያ ስልጣን ሲይዝ ደርግ የፖለቲካ ሐሳብ ነበረዉ? ፓርቲስ ነው ? ደርግ ተስፈንጣሪ ብሎ የፈጃቸዉን እነ የዎላይታዉን ሰለሞን ዋዳ በእጅ ብልጫ መረሸን ጀምሮ፣ ብዙ የብሔር ጥያቄ የሚያነሱትን መፍጀቱን ዳንኤል አያዉቅም ይሆን? የኤርትራስ ጉዳይ፣ አማን አንዶምን የገደለዉ ደርግ ለምን ነበር? በአስር ሺዎች በደርግ ዘመን የተፈጁበት የኤርትራ ጉዳይ፣ ከኢህአዴግ ጋር እንዴት ይመሳሰላል? ምናልባት ደርግ ሐገር በእዉር ድምብር ሲመራ ከርሞ የብሔረሰቦች ጥናት ኢንስቲቲዩት አቋቁሞ ካስጠናቸዉ ሰነዶች ኢህአዴግ አንዱን አማራጭ ምናልባትም ተመሳሳይ ቋንቋ የሚያወሩ ሕዝቦች አንድ ላይ ይደራጁ የሚለዉን ጥናት መቀበሉን ማለት ፈልጎ ከሆነ እንጃ።
በተረፈ በደርግ ጊዜ የነበሩ ቡድኖች መነጋገር አለመቻላቸውን ይተቻል፤ ያ ጥሩ እይታ ነው፥ ለዛሬ አለቃዉ ቢያማክረዉ ደግሞ የበለጠ ጥሩ ነው፣ በስልጣኑ ዘመን በለዉ በለዉ ብሎ አማክሮ፣ የሥልጣን ጸሐያቸዉ ሲጠልቅ፣ እኛ ተዉ ብለነዉ መንግስቱ አልሰማ አለን እንደሚሉት የደርግ ሰዎች ለማታል እንኳን እንዳይመቸዉ ዳንኤል የእርስ በርስ ጦርነቶቹን ከጻጻሱ በላይ በሚያስብል ደረጃ በፕሮፖጋንዳና በፍረጃ አየመራ ነው፤ ይሁን ብቻ።
ሕወሓት /ተሐአት ከመነሻዉም የአማራን ብሔር ጨቋኝ አድርጎ በ1968 ባወጣው ማኒፈስቶ ማስቀመጡን ሚያወሳዉ ዳንኤል የሕወሓት መሪዎች በተደጋጋሚ የአማራ ገዢ መደብ ነው የጨቆነን ያሉትን መጥቀስ አልፈለገም። የኢሕዴን አቋም ላይ በተለይ የነፍጠ’ኛዉ ሥርአት በዋናነት ከአማራ ብሔር የወጣ ነው፣ የሚለዉን እንደ አጠቃላይ ብሔራዊ ፍረጃ የሚያዬዉ ዳንኤል፣ ጨቋኝና ተጨቋኝ ብሔር አለ የሚሉ ቡድኖች ስልጣን ይዘዉ የተዛባ ትርክት መፍጠራቸዉ በቀለኝነትን ወልዷል፣ ለጭቆና እዉቅና መንፈግ ደግሞ ጽንፈኝነት አስፋፍቷል ይላል።
በአንድ በኩል እራሱ ዳንኤል ለጭቆና እዉቅና የሰጡትን እየተቸ እንዴት እንዲህ እንደሚል ግልጽ አይደለም። የብሔር ልሂቃንና ምሁራን ሁኔታውን አጥርተዉ ስላልተረዱ ጭቆናን መታገልን ትተዉ፤ ጨቁኖኛል ያሉትን ሥልጣን ላይ ያለን ግለሰብ ወይንም ብሔር ሲታገሉ ነበር ይላል፣ ጭቆናን ያመነጨዉንና ፈጻሚ ና አሰፈጻሚ የሆነዉን ጨቋኝ ትታቹ ጭቆናን ታገሉ ማለት ምን ማለት ይሆን? ዳንኤል ስልጣንን እንዴት ይረዳል ?
ምን አልባት ብሔሮች በጅምላ ከአገዛዞች ጋር መፈረጃቸዉን ለመቃወም ነው እንዳንል አባባሉ እንደዛ አይመስልም። አገዛዞች የሚያሳዩት ዉግንናና በሕዝቦች ዘንድ የሚታዬዉ የየኛ መንግስት ነው ስሜትም፣ አብሮ መታዬ የለበትም ወይ? ከአብዮቱ ዋዜማ ጀምሮ የተፈጠሩ የብዝሓ ማንነት ያላቸዉ ፓርቲዎች በላይ የብሔሮቹ አሸናፊ ሆነዉ የወጡበትን ምክንያት ሲጠቅስ ዳንኤል፣ አንድ፦ ለማኅበረሰቡ ከርዕዮት ይልቅ ብሔር ስለሚቀርበዉ ነው ብሎ ከፖለቲካ ሀሁ ጋር የሚጋጭ ሐሳብ ያስቀምጣል፣ ለመሆኑ የብሔር ድርጅቶችስ ርዕዮተ አለም አልነበራቸዉም?
ሁለተኛ ፦የተማሪዮች ንቅናቄ እታገላቸዋለሁ የሚላቸዉ ኢምፔሪያሊዝም ና ፊዉዳሊዝም ለማኅበረ ሰቡ ሩቅና የማይገቡት ስለሆነ ነው ይላል። በርግጥ ማኅበረሰቡ ከገባዉ ፊዉዳሊዝምን ሊያዉቅ እንደሚችልም በምናልባት ያስቀምጣል፣ ለመሆኑ ፊዉዳሊዝም የብሔር መስመር እንደነበረዉ ዳንኤል አያዉቅም? ሕዝቡስ የሚገባዉን፣ የሚያዉቀዉን ችግር ለሚፈቱለት ድርጅቾች ቦታ መስጠቱ ለምን ያስወቅሰዋል?
ሶስተኛ፦ከአለም አቀፋዊነት አካባቢያዊነት መብለጡ አይገርምም ያለዉ ያስማማል፣ እስከ globalization ዘመን ድረስ ብናይ ገዢ ሐሳብ ነው። አራተኛ ፦ thesis(ሐቲት)፣ antithesis (መድፍነ ሐቲት)፣ synthesis (ሥምረተ ሐቲት) (መደመር ሥምረተ ሐቲት ነው ይላሉ እርሳቸዉ)። ይህ ክፍል ላይ በግሌ አማርኛን ጨምሮ የብሔሮች ና ብሔረሰቦች ቋንቋ እንዲያድግ ፍላጎት ስላለኝ ጸሐፊዉ academic ቃላትን በአማርኛ ስላቀረበ አመስግነነዉ አንድ ሁለት ጥያቄዎችን ጣል አድርገን ይሄንን ክፍል እንዝጋ።
ሕብረብሔራዊ አንድነት ከመደመር በፊት አልተቀነቀነም? ሌሎች ሥምረተ ሐቲታችን ነዉ የሚሉትን በጅምላ በመድፍነ ሐቲትነት ፈርጆ፣ ብቸኛ ሥምረተ ሐቲት አቅራቢ ለመምሰል መሞከር አያስተዛዝብም ወይ? መደመርስ በንድፈ ሐሳብ ተቀምጧል የሚባለዉና በተግባር የሚሰራዉ ይገናኛል? በተጨባጭስ አገዛዙ የሚሰራዉ ለኦሮ_ማራዊነት ወይስ ለሕብረብሔራዊነት?
ገጽ 66 ላይ ምእራፍ 4: የማንነት ብያኔና አለመግባባት በሚል ርዕስ አቅርቧል። በዚህ ክፍል ዉስጥ ዳንኤል ኢትዮጵያ ዉስጥ ለማንነት መገለጫ የዋሉትን ነገሮች ተሻጋሪና የማይሻገሩ ብሎ ለሁለት ይከፍላል፤ የሚሻገሩትና የማይሻገሩት ምንን እንደሆነ ባያስቀምጥም። ከመጀመሪያው ስር ሃይማኖት፣ ጾታ ርእዮተዓለምና ሀገር አስቀምጦ በሁለተኛው ሥር የብሄርና የአካባቢ ማንነቶች ያስቀምጣል።
እነኝህን ጎራዎች የሚያገናኙ ያላቸዉን አራት ነገሮችን ጠቅሷል ፍልሰት፣ ንግድ፣ የሃይማኖት ትምህርት እና ጦርነት ናቸዉ ይላል። እነዚህ እንቅስቃሴዎች ዉስጥ በአንድ አካባቢ ወይም ማኅበረ ሰብ ተጠብቀዉ የኖሩና የተጋሩ ማንነቶች ተፈጥረዋል የሚል ጭብጥ ያለዉ ሐሳቡን አትቷል። ዳንኤል ማንነትን፣ በባህል ቦታ እያስገባ በድፍረት የሚጽፈዉ ከ primordial የማንነት ብያኔ ግንዛቤ በመነሳት ይመስላል።
ከነችግራቸዉም ቢሆን በዚህ ክፍል ያነሳቸዉ ነጥቦች መሐል በተለይ በአካባቢ፣ በብሔራዊ፣ በሀገራዊ፣ በቅይጥ ማንነታቸዉ መገለጽ የሚፈልጉ ሰዎችን በሙሉ የሚያቅፍ ሥርዓት ከጥንት እስከዛሬም አልፈጠርንም የሚለዉ ሐሳቡ ቦታ ተሰጥቶት ቢመረመር አይከፋም። ሀገራዊ ማንነትን በአማርኛ ተናጋሪነት መወከልና እንዲሻገርና እንዳይሻገር የሚያደርገዉ ፖለቲካ መሆኑን በመሳት ብሔራዊ ማንነትን ከነቋንቋዋዉ መትሮ መገደብ ተገቢ አይመስለኝም።
ሌላዉ ዳንኤል በዚህ ክፍል Establishment ን እደፈጣሪ ሥራ የማየትና የማይቀየሩ አድርጎ የመገንዘብ ችግር ይታይበታል፣ ፓለቲካ የፈጠራቸዉን፣ ፖለቲካ ሊቀይር ይችላል።
ገጽ 70_81 ምዕራፍ 5፦የጋራ ታሪክ አለን? የለንም ? ሙግት፥ በሚል ርዕስ ስር ጽፏል።
ሰደመድም አንድ ገዢ ሐሳብ አስቀምጧል፣ የኢትዮጵያ ታሪክ ግን የአካታችነትና የብያኔ ችግር አለበት፣ በማለት ፤ይሁን እንጂ ዳንኤል አሁንም የአብሲኒያ የታሪክ ወንዝ ላይ በመንገድ የሚቀላቀሉ ትንንሽ ጅረቶች ያስባል፣ ማስረጃዎች ሞልተዉናል የሚለዉ በአጼ እገሌ ታሪክ የእገሌ ብሔር ሰዉ ተጠቅሶ ነበረ ሊለን መሆኑ ነው።
የዘዉግ ፖለቲከኞች የብሔር ጭቆና በብሔሮች ላይ ደርሷል ብለዉ፣…እርስ በርሳቸዉ መናከስ ጀምረዉ፣ በሂደት ወደ ሕዝቡ በመግባት ንጹሐንን ወደ ማባላት አሳድገዉታል፣ ይላል። ጨበቤቱ እራሱን ከዘዉግ ዉግንና እና አተካራ ነጻ ማድረጉ ነው፣ ትግራይን ከደቡባዊ አዉስትራሊያ በጣት የሚቆጠሩ ሰዎች ሲቀሩ፣ እንደጠፋዉ ታዝሜንያ ሕዝብ ማጥፋት አለብን፣ በአደባባይ ሲል እንዳልከረመ፣ አልንበረከክም ከማንም አላንስም ባይነትን የሚገልጸዉንና የትግራይ ማንነት አካል የሆነዉን ዎያኔነት፣ ኢትዮጵያን የተጣባ በሽታ ነው፣ ከታሪክ እና ከሰዉ ሕልሊና እንፍቃለን ሲል እንዳልከረመ፣ ጽንፈኛ እና ነዉጠኛ ዘዉጌነቱን በኢትዮጵያ ሽፋን የሚያራምድ መሆኑን የምናዉቅ እኛ ለማያዉቅሽ ታጠኝ እንላለን።
በተቀሩ ገጾች የዘከዘካቸዉ አረፍተ ነገሮች ነባር አግላይ ታሪክ ላይ የብሔሮችን ታሪክ ቀነጫጭቦ በመጨመር የመቀጠል ፍላጎት እንዳለዉ ያሳያሉ። ምናልባት አንድ ጥሩ ያገኘሁት የራሱ ሀሳብ ባይሆንም፣ በተካልኝ ወልደማሪያም ከተጻፈው መጽሐፍ ፣የኢትዮጵያዉያንን የቦታ እንቅስቃሴ፣ ቅድመ 19ኛዉ መክዘ እና ድኅረ 19ኛዉ መክዘ ብሎ ከፍሏል የሚለዉ ግሩም ነው። በተለይ ድኅረ 19ኛዉ መክዘ፣ በኃይል፣ ጨበት እዛዝና በተደራጀ የሦስተኛ ወገን ፍላጎት የተደረጉ የሕዝቦች እንቅስቃሴ ነው ያለዉ የምስማማበት ነው፣ ዳንኤልን እዚህ ጋር ቢያንስ ለመጽሐፍ ጥቆማዉ ማመስገን ይኖርብናል።
ሌላዉ ታሪክን የምንመለከትበት መነጽር እንደሚያጣላን መግለጹም ጥሩ ነው፣ ምናልባት የጋራ መነጽር የመፈብረክ ከባድ ሥራ፣ ካልሆነም በየራሳችን መነጽር እያየንም እንዴት በሰላም መኖር አለብን የሚለዉ ላይም ማሰብ አለብን ይሆናል።
ዳንኤል በተደጋጋሚ ልዩነቶቻችንን በጎራ ለይቶ የማስቀመጥ ሙከራዉ የተሳካለት አልመሰለኝም፣ ብዙ ግዜ በሁለት ጎራ ይከፍልና እራሱን ሶስተኛ ሐሳብ አቅራቢ አድርጎ ማሳየት ይፈልጋል። በዚህ ክፍል ለምሳሌ “ታላቋ ኢትዮጵያ ትርክት” እና “ተገዳዳሪ ትርክት” ይላል። ቢያስ፣ ተገዳዳሪ ትርክቶች፣ ቢል ይሻላል፣ ብዙና የተለያዩ ስለሆኑ።
ከዛ ባለፈ እራሱ የፖለቲካ ስልጣን እንደያዘ ፖለቲከኛና የሀገሪቷን ታሪክ ጠብቄ አሸጋግራለዉ የሚል ፖለቲካዊ አላማ ጭምር አንግቦ ሲንቀሳቀስ የከረመ ማህበር ዉስጥ በሐይማኖት ካባ ተወሽቆ እንደቆዬ ፖለቲከኛ፣ ታሪክ የፖለቲካም መሳሪያ ጭምር በሆነበት ፣ጫናም ከተለያዬ አቅጣጫ እንዳለበት መጥቀስ ነበረበት፣ የፖለቲካ ችግሮች ጋር በጋራ እንጂ በተናጠል ሊፈታ እንደማይችልም አለመግለጹ የራሱን intellectual integrity ድሮም ጥያቄ ዉስጥ የነበረዉን የባሰ ጥያቄ ዉስጥ የሚከት ነው።

ይህ ርዕስ በተጨማሪ ከፍተኛ የዘርፉ ምሁራንን ተሳትፎ የሚፈልግም ስለሆነ፣ የእነሱም ተሳትፎ አስፈላጊነት ላይ አጽንኦት በመስጠት፣ ዳንኤል በክፍሉ የጠቀሳቸዉ ብዙ የማይዋጡልኝ ሀሳቦች ቢኖሩም ዋና ዋና ዎቹን ስላነሳሁኝ በቂ ይመስለኛል። ዳንኤልም ጭምር ያመነበት የታሪካችን ጎዶሎነት ግን በብዙ አቅጣጫ ሀገራችን ኢትዮጵያን ጎዶሎ ማድረጉን ሳልጠቅስ አላልፍም፣ ለሕዝቦች መናናቅና መለያዬትም፣ አንዱ ትልቅ መነሻ ነው እላለሁ።
ገጽ 82_86፦ ምዕራፍ 6፣ የቋንቋ ተቃርኖ … ይላል ሀገረ መንግስቱን ከብዙ ቋንቋዎች ጋር ትስስር አለዉ ብሎ ከአቢሲኒያ፣ ከአህመድ ግራኝ፣ ከሀረርና ኦሮሚያ አካባቢዮች ድረስ ጠቃቅሶ የቋንቋ ብዝሐነትን የገለጸበት በቂ ባይሆንም፣ ለማካተት ሞክሯል። ቀጥሎ አንድ ጥሩ ነጥብ አንስቷል”የቋንቋ ብዝኃነትን ማስተናገድ የኢትዮጵያን ነባራዊ መልክ መቀበል ነው።” በማለት ይህንን ወድጄዋለሁ።
ግን ቀጥሎ ደግሞ ፣ “ቢያንስ ክልሎች ሁለት ሦስት ቋንቋዎችን የሥራና የትምህርት ቋንቋዎች እንዲያደርጉ የግድ ማለት ያስፈልግ ነበረ። “ይላል የግድን ምን አመጣዉ፣ በዉይይት ና ድርድር አይሻልም? የመጨጫን አባዜ መሆኑ ነው ? ዳንኤል ምናልባት ደቡብ ኢትዮጵያ ላይ በቅርቡ እርሱ የሚገኝበት መንግስት ዎላይትኛ ተጨማሪ የሥራ ቋንቋ እንዲሆን የዎላይታ ካድሬዎቻቸዉ ጠይቀዉ መከልከሉን የሰማ አይመስልም።
ትግራይ ከሁለት አማርኛን ቀንሳ፣ ሳሆና ኩናምኛ ጨምራ ሶስት የሥራ ቋንቋ ማድረጓን ዳንኤል እንዴት ይመለከት ይሆን ? በግሌ አማርኛ መቀነሱን አልደግፍም፣ ምክንያቱም በዎልቃይት የሚገኙ አማሮች የትግራይ ክልል ነዋሪ ስለሆኑ ቋንቋቸዉ ሊካተት ስለሚገባ። ዳንኤል በዚሁ መጽሐፉ ሰሜን ጎንደር ብሎ በቅንፍ ዎልቃይትን ጠቅሷል።
የፈደራል የሥራ ቋንቋዎችን ማብዛትና በትምህርት ቤቶች ብዙ ቋንቋዎች በትምህርት ይሰጡ ያለዉ የምደግፈዉ ሐሳብ ነው። የዎላይትኛን ጉዳይ ብናይ በአዲስ አበባ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዎላይታዎች ቢኖሩም ትምህርት በዎላይትኛ አለመሰጠቱ ሐገሪቷ እየሰራች የቀጠለችዉን ወንጀል የሚገልጽ ነውና ሐሳቡ የሚደነቅ ነው።
ቀጣይ ክፍል ይቀጥላል ...”
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዛሬው የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት “ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳያመልጠን” በሚል ስለጠቆሙት የዳንኤል ክብረት “የትርክት ዕዳና በረከት” መጽሐፍ ላይ የቀረበ ጥልቅ ሂሳዊ ዳሰሳ… ክፍል 1 በፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) የቀረበ ሲሆን የዚሁ መፃህፍ የመጨረሻው ክፍል ሂሳዊ ደሳሳ በቀጣይ እንደምናቀርብ በአክብሮት እንገልፃለን። #WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia