1000017263

የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ መግባት እችላለሁ ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ተፈቅዷል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መንግስት በቅርቡ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን፣ አቋቁሞ እየተንቀሳቀሰ ነው፣ ይሄን እንዴት ያዩታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ኢትዮጵያ ምክክር እንደሚያስፈልጋት ሐገር ያወቀዉ ጸሐይ የሞቀዉ ጉዳይ ነው። ነገር ግን መንግስት ከኮሚሽነሮቹ መረጣ ጀምሮ በተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚቀርቡ ቅሬታዎችን ቸል ማለቱ ከባድ ስህተት ነው። ብልጽግና በዚህ አግላይ መንገድ በመሄዱ በአሁኑ ሰዓት ኦነግ፣ ኦፈኮ፣ ኦብነግ እና ሁለቱ የዎላይታ ፓርቲዎች ማለትም ዎህዴግ እና ዎብን እንደማይሳተፉ አሳዉቀዋል። ህወሓት የፕሪቶሪያ ስምምነት ከተተገበረ እሳተፋለሁ በማለት የራሱን አቋም ገልጿል።

እንግዲህ እነኝህ ትልልቅ ፓርቲዎች በኢትዮጵያ ፖለቲካ ያሉትን ልዩነቶች ትርጉም ባለዉ ደረጃ የሚወክሉ ናቸዉ የእነሱ አለመሳተፍ አለ ጥያቄ ሐገራዊ ምክክሩን ጎዶሎ ብቻ ሳይሆን ሌላ የተጨማሪ ቀዉስ ምንጭ እንዳያደርገዉ እሰጋለሁ። በተለይ በዚህ አግላይ አካሄድ ተኬዶ ሕገመንግሥት መነካካት ሌላ የማያባራ ቀዉስ እንዳያመጣ ያሰጋኛል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የዎላይታ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ካልተሳተፉ፣ የዎላይታ ብልጽግና ቅርንጫፍ የሕዝቡን ጥያቄዎች በራሱ መስመር የሚወክልበት ቁመናና አስቻይ መንገድ አለዉ ብለዉ ያምናሉ ?

✅ ማሪንዶስ ጦና፦ አላምንም። ሲጀመር ብልጽግና ወጥ ፓርቲ በመሆኑ ቅርንጫፎች በራሳቸዉ ተሰባስበዉ አቋም የሚይዙበት አግባብ የለም። ፓርቲዉ አቋሙን በየቋንቋዉ ከመተርጎም የዘለለ ሚና የላቸዉም፤ እንደዞን ይቅርና እንደ ክልልም አቋም የሚይዙበት አግባብ የለም።

ስለዚህ ያ አንደኛዉ ምክንያት ሲሆን ሁለተኛዉ ደግሞ ብልጽግና ፓርቲ በራሱ ለዎላይታ ጤናማ አስተሳሰብ ያለዉ አለመሆኑን በብዙ ማሳያዎች መጥቀስ ይቻላል። የዎላይታ ተወላጅ የሆነ ሰዉ ለሐገር ሰላም ብሎ በፈቃዱ ከጠቅላይ ሚኒስትርነት ካነሳ በሁዋላ የብሄሩ ተወላጅ ሰዉ በዲፕሎማሲያዊ ፖለቲካዊም ሆነ ወታደራዊ ስልጣን ላይ ቦታ እንዳያገኝ አድርጓል፥ 40ሺ የመከላከያ አባል ዎላይታዎችን ቀንሷል፥ ሕዝቡ ሲጠቃ ሰብአዊ መብቱን አላስከበረም፤ የክልል ጥያቄዉን አፍኗል፤ በዞኑ መፈንቅለ መንግስት አድርጓል።

በተጨማሪም የክልል ጥያቄዉን ለማፈን አንድ አመት የክልል ምክር ቤት እንዳይሰበሰብ አድርጓል እዚህ ጋር ማንሳት ያለብን ከተደማጭነት አንጻር ጠቅላይ ሚኒስትር የነበረ ሰዉ ብሄር በክልል ምክር ቤት እንኳን የማይደመጥበት ነው፣ በጉልበት አዲስ ክልል ሕዝቡ ላይ ተጭኗል፣ በፈደሬሽን ምክር ቤት የሐሰት ክስ ሕዝቡ ላይ ተፈብርኳል።

ሌላዉ ብልጽግና ዎላይታን እንደ ቋሚ ጠላት ፈርጆ እንደሚንቀሳቀስ የሚያሳየዉ፣ በፊት ከሕወሓት እና ከኦነግ ሸኔ ጋር ይሰራሉ ብለዉ በማጎሪያ ያሰሯቸዉን አመራሮቾ፣ ምሁራንና የተቃዋሚ ፓርቲ ሰዎችን ፍርድ ቤት በነጻ ማሰናበቱ ሳያንስ በቅርቡ ደግሞ ከፋኖ ጋር ይሰራሉ የሚል ዶክመንተሪ ተሠራጭቷል። ከዛ ዉጪ በክልልም ሆነ በፈደራል ተመጣጣኝ የሥልጣን ዉክልና ዞኑን ነፍጓል።

መቼስ እንዲህ የሚያደርግ ፓርቲ ራሱን መልሶ በመገምገም ካላስተካከለ በስተቀር የዎላይታ ሕዝብ ጥቅም የሚያስጠብቅ ሐሳብ ያቀርባል ብሎ ማሰቡ ሞኝነት ነው። ተቃዋሚ ፓርቲዎች የተሻለ አማራጭ ይመስሉኛል። ዎላይታን መሠረት አድርገዉ የተቋቋሙ በመሆኑ የተሻለ ለሕዝባችን ድምጽ ሊሆኑ ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ። አለመሳተፋቸዉ ለሐገርም ለዎላይታም ትልቅ ጉድለት ነው። እንዲሳተፉ መንግስት የማሻሻያ እርምጃዎችን መዉሰድ አለበት።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የተመረጡ የሕብረተሰብ ተወካዮችንስ እንዴት ያያሉ? ብልጽግናስ ኮሚሽኑ ላይ ማሻሻያ እስከመጨረሻው ካልወሰደ ዎላይታ አይሳተፍም ማለት ይቻላል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ምን መሰለህ እነዚህ የሕብረተሰቡ ተወካዮች የሚባሉት ከእድርና ከእቁብ የተሰበሰቡ ናቸዉ። እንደ ተሳትፎ ክፋት ባይኖረዉም፤ በሐገሪቷ እየተጋጩ ያሉት ግን እድርና እቁቦች አለመሆናቸዉን ሁላችንም እናዉቃለን።

ብልጽግና ደግሞ እንደወትሮው ሁሉ በያዘው አቋም ሂደቱን ሊቀጥል ይችላል። ያ ከሆነ ክፍተቱን ለመሸፈን በዎላይታ በኩል የሚሳተፍ ጊዜያዊ የምሁራን ንቅናቄ መቋቋም አለበት የሚል እምነት አለኝ። እንደ ሐገር የሚበጀዉ ግን ሂደቱ ታርሞ ተቃዋሚዎችም ቢሳተፉና በጫካ ያሉ ወገኖቻችንም ቢሳተፉ መልካም ነው። ስለተሰጠኝ ዕድል አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እኛም ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እናመሰግናለን። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዛሬው የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ባለፈው በሁለት ክፍል በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እየገለፅን ለአዲሱ ዓመት ዋዜማ እንኳን በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን እንላለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ