GridArt_20240911_205120059

ከዳሞታ ተራራ እስከ አድዋ ባድሜና ሽራሮ ዎላይታዎች ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት የከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት የሚተርክ አዲስ መፅሀፍ በደራሲ ዋዱ ዳና ተፅፈው ለገበያ መቅረቡ ተገልጿል።

“የአባቱን ታሪክ እስከጠበቀው የልጁ ይሆናል፤ ካልጠበቀው ግን የባዳዎቹ ታሪክ ይሆናል። ታሪክ ከሰነፍ ትውልድ ደጅ ይዘረፋል፤ ዘራፊዎቹ ተዘጋጅተውበት በመሆኑና ኃያላን ስለሆኑ አንዳንዴ ሄደህ የአባትህን ታሪክ ለባዳ መርቀህ ሰጥተህ ትመጣለህ።” – “ሕመምተኛው ዘማች” በሚል ርዕስ ከተፃፈው አዲስ መፅሐፍ ገጽ 16 የተወሰደ ሀሳብ ነው።

ደራሲው ከዚህ በፊት “ውስብስቡ መንገድ” እና “ዎዜ” የተሰኙ መፃህፍትን በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የተፈጠረው ጦርነት፤ በሌሎች አካባቢዎች የተከሰቱ ፖለቲካዊ ትኩሳቶች እና የዎላይታ ህዝብ ከለውጡ መምጣት ጋር ተያይዞ የገጠመው የፖለቲካ ፈተና ከመፃኢ እድሉ ጋር ተሰናስሎ የቀረበበትን ለአንባቢያን ማብቃቱ ይታወሳል።

በፖለቲካና የመንግስት አስተዳደር ውስጥ የዳበረ ልምድ ባካበቱት ብስለት በተሞላው አገራዊ ጉዳዮች ቅኝታቸው የሚታወቁት ደራሲው በአዲሱ “ሕመምተኛው ዘማች” መፅሀፍ ከዳሞታ ተራራ እስከ አድዋና ካራማራ፣ ባድሜና ሽራሮ ዎላይታዎች ለሀገር ክብርና ሉዓላዊነት የከፈሉት ታላቅ መስዋዕትነት እጅግ በሚጣፍጥ ቋንቋ ከሽነው አቅርበዋል።

መጽሐፉ ከደራሲው ቀደምት ሥራዎች በተለየ መንገድ በልበወለድ መልክ እያዋዛ፣ እያዝናና እያስተማረ ባለፉት ሥርዓቶች ዜጎች ለሀገራቸው ብለው የከፈሉትን መራራ መስዋዕትነት የሚያወሳ በመሆኑ ለአሁኑና ለመጪው ትውልድ ሀገራቸውን እንዲወዱ፣ እንዲያውቁና እንድጠብቁ መልዕክት የሚያስተላልፍ ድንቅ ረጅም ልበወለድ እንዲሁም የገሃዱ ዓለም እውነታ ፍንትው አድርጎ የሚያሳይ መጽሐፍ እንደሆነም ከተላከልን መረጃ ለማወቅ ችለናል።

በድጋሚ Hashshu Ooratta Layttawu Saro Gattees 🙏
መልካም አዲስ ዓመት 🙏
ዓመቱ የሰላምና የፍቅር ይሁንልን🙏 Wolaita Times

በናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው