
ከ5 ዓመት በፊት ጀኔራሎችና በርካታ ከሻለቃ እስከ ኮሎኔል ደረጃ ያሏቸው የዎላይታ ተወላጅ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን የሉም፡፡ የት ገቡ?
በኢትዮጵያ የተቋቋመው የሽግግር ፍትህ ለእነዚህ ጀኔራል፣ ከሻለቃ እስከ ኮሎኔል ደረጃ ያሏቸው በተጨማሪ ሌሎች በበርካታ ሺዎች የሚቆጠሩ የጦር ወንጀል ሰለባ ለሆኑት የዎላይታ ተወላጅ መኮንኖች ፍትህና ካሳ ለምን አልሰጠም ?

ውድ ተከታዮቻችን ይሄንን እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን የተባበሩትን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ እያመሰገነ ከበርካታዎቹ ጥቂት የ “ለውጡ” ሰለባዎችን ለማሳያነት በዚህ ዝርዝር ዘገባ ላይ መጥቀስ አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል።
በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም የተከሰተውን ለውጥ ለማምጠት በተደረገው ግብግብ በመቶዎች የሚቆጠር ሰዎች ሕይወት እንደበላ ሲነገር እንሰማለን፡፡ ነገር ግን በ”ለውጥ” ፋንታ ነውጥ መጣ፡፡ የሚገርመው ግን ከ”ለውጡ” በኋላ “ለውጡ” ራሱ የበላቸው ሰዎች ስፍር ቁጥር የሌለ መሆኑ ብዙዎች ይረዱታል፡፡ የለውጡ መሪና ተዋናይ የነበሩ መሪዎች ሳይቀር በኋላ በለውጡ ሂደት ተበልተዋል፡፡ ይህ ሁኔታ በደርግ ዘመን “አብዮት ልጇን ትበላለለች” የሚለውን አባባል አስታውሶን አልፏል፡፡
በ “ለውጡ” አንዳንዶች ህይወታቸውን፣ ሌሎች ስልጣናቸውን፣ ሌሎች ቢዚነሳቸውን፣ አንዳንዶች ማዕረጋቸውንና ክብራቸውን አጥተዋል፡፡ አንዳንዶች የስራ ቦታቸውን አጥተዋል፡፡ አንዳንዶች የሚወዱትን ቤተሰብ አጥተዋል፡፡
“ለውጡ” አንዳንዶችን ከመሬት አንስቶ ባለስልጣን፣ አንዳንዶችን ባለሀብት፣ ሌሎችን ታዋቂና ተጽእኖ ፈጣሪ ሲያደርግ በተቃራኒው አንዳንዶችን ከስልጣን ማማ ገፍተሮ ወደ ተራ ሰውነት፣ ከሀብት ማማ ወደተስፈኝነት ጎራ፣ ከአንቱነት ወደ አንተነት ቀላቅሏቸው፡፡
በርካቶችን ደግሞ ከከፍታ ወደ ዝቅታ፣ ከድሎት ወደ ስደት፣ ከሞቀ ቤታቸው አፈናቅሎ አውላላ ሜዳ ላይ አንድጠለሉ አደረጋቸው፡፡ “ለውጡ” አንዳንድ የማህበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ሌሎችን ወደ ጫፍ ገፍትሮ በማግለል ተጠቂና የኢኮኖሚ ተጠቃሚነታቸውንና የፖለቲካ ተሰሚነታቸውን ነጠቃቸው፡፡
በ”ለውጡ” ወቅት ሶስት የጦር ጀኔራሎችና በርካታ ከሻለቃ እስከ ኮሎኔል ደረጃ ያሏቸው የዎላይታ ተወላጅ የጦር መኮንኖች ነበሩ፡፡ ዛሬ ግን የሉም፡፡ የት ገቡ? እስኪ ከበርካታዎቹ መካከል ጥቂት የ “ለውጡ” ሰለባዎችን ለማሳያነት እንመልከታቸው።
ሜጄር ጀኔራል አቤል አየለ፡-
ሜጄር ጀኔራል አቤል በኢትዮጵያ አየር ሀይል የሰው ሀበት አመራር ሃላፊ፤ በለውጡ ወቅት የመከላከያ የተጠባባቂ ጦር ሃላፊ የነበረ ሰው ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት ሲጀመር በኒዮርክ የተባበሩት መንግስታት የኢትዮጵያ ወታደራዊ አታሼ ሆኖ ሲያገለገል ነበር፡፡ በኋላ በጦርነቱ መሃል “ከትግራይ ተወላጆች ጋር ስሞዳሞድ ይውላል” የሚል በቂና ተጨባጭ ባልሆነ መረጃ ስራውን አቋርጦ ሀገር ቤት አንዲመለስ ተደረገ፡፡ ወዲያውም ከመከላከያ ያለምንም ፍርድ እንዲሰናበት ተደረገው ነበር፡፡
ሜጄር ጀነራል አቤል ጡረታ ለመውጣት ገና ስምንት አመት ሲቀረው ነው ከተቋሙ አንዲሰናበት የተደረገው፡፡ ጀኔራል አቤል ይህ ብቻ አይደለም ከሜጀር ጀራል ማዕረግ በላይ በአዲስ አበባ ከተማ የሚሰጥ የመኖሪያ ቤት መስሪያ ቦታ እንዳይሰጥ ተከልክሎ በአሁኑ ሰዓት የሚመላለስበት ተሸከሪካሪ አጥቶ በእግር እየኳተነ ኑሮውን ይገፋል፡፡
ብርጌዴየር ጀኔራል ኢናሶ ኢጃጆ፡-
ብርጌዴየር ጀኔራል ኢናሶ የሰሜን ዕዝ ሲጠቃ የዕዙ የመረጃ ሃላፊ ሆኖ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ጥቅምት 23 ጥቃቱ ሲፈጸም አዲስ አበባ ለስብሰባ መቶ እያለ ነበር ጥቃቱ የተፈጸመው፡፡ የሰሜን ዕዝ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በቂ መረጃ አልሰጠም በሚል በሃሴት ተከሶ ሁለት አመት አስር ቤት ቆይቶ ምንም ጥፋት ሳይገኝበት የፕሪቶሪያው ስምምነት ሲደረግ ተፈታ፡፡
ሆኖም በወቅቱ ስለ ህወሃት የጥቃት ዝግጅት በቂ መረጃ ለመከላከያ ሰጥቶ በበላይ ሃላፊዎች እርምጃ ሳይሰድ በመቅረቱ ጥቃቱ መፈጸሙን ፍርድ ቤት ተከራክሮ ብረታም ከመሰናበት ውጪ ወደ ስራ ተመልሶ በሰራዊቱ ለማገልገል አልታደለም፡፡ ሁለት አመት ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ ታስሮ ካለ ምንም የሞራል ካሳ የስነ ልቦና ጥቃት ሰለባ ሆኖ ቀርቷል፡፡
ሻለቃ መኮንን ሰጋሮ ሻለሞ፡-
መኮንን ሰጋሮ በዎላይታ ጋሱባ ወረዳ ተወልዶ አድጎ ወደ መከላከያ ሰራዊት ተቀላቅሎ የሻለቃነት ማዕረግ ደረጃ የደረሰ ነው፡፡ የህወሃት ጦር ወልዲያን በሚቆጣጠርበት ወቅት “መረጃ እየሰጠ ጦሩን ያስፈጀ ነው” በሚል ከህግ ውጪ በጦሩ ፊት ተረሽ’ኗል፡፡ ከመረ’ሸኑ በፊት “ከህወሃት ታጣቂዎች ጋር ግንኙነት አለው” ተብሎ ተጠርጥሮ ከታሰረ በኋላ ማስረጃ ሲጠፋ ተፈቷል፡፡ ኋላ ግን በጦሩ ፊት እንድረሸን ተደርጓል፡፡ መኮንን ሰጋሮ የአንድ ሴት ልጅና የአንድ ወንድ ልጅ አባት ነበር፡፡
ሻለቃ መኮንን ሻለሞ
ሻለቃ መኮንን ህወሃት ሰሜን ዕዝን ባጠቃበት ወቅት ታግተው በረሃ ከቆዩት በሺዎች ከሚቆጠሩ ወታደሮች መካከል አንዱ ነበር፡፡ በእገታ ወቅት መንግስት መቀሌን ሲደበድብ “ይህ መንግስት ህዝብን እየፈጀ ነው” እያለ ከታጋቾች ፊት ሲናገር አንደነበረ አብረው የነበሩ መኮንኖች ይናገራሉ፡፡ ኃላ መንግስት ትግራይን ሲቆጠጠር ከቴምቤን አካባቢ ከተለቀቀ በኋላ ወደ ሚሰራበት ክፍል ተመልሶ ስራ በጀመረበት ወቅት ነበር “መረጃ እየሰጠ ሰራዊቱን ያስጠቃል” ተብሎ ወልዲያ አካባቢ የተረሸ’ነው፡፡
ሻለቃ መኮንን ከፍርድ ቤት ውጪ የሚደረግ ግድያ “extrajudicial killing” ሰለባ ሆኗል፡፡ በዳኝነት ሂደት የተሰጠ ህጋዊ ስልጣን ሳይኖር ሆን ተብሎ ሰውን መግደል የጦር ወንጀል ተፈጽሞበታል፡፡
የሻለቃ መኮንን ቤተሰቦችና ልጆቹ ያለ ጡረታና የደም ካሳ ሳይከፈላቸው ሜዳ ላይ ቀርተዋል፡፡ ሚስቱ መቀሌ ከተማ በለስ እየቸረቸረች ልጆችዋን ተቸግራ እንደምታሳድጋቸው መረጃ አለ፡፡ ስለ ባለቤቷ አሟሟት የተነገራትም “በውጊያ ተሰውቷል” የሚል ነበር፡፡
በኢትዮጵያ በመንግስት አነሳሽነት የተቋቋመው የሽግግር ፍትህ ለእነዚህ የዎላይታ የጦር መኮንኖችና ሌሎች በሺዎች የሚቆጠሩ የጦር ወንጀል ሰለባዎች ፍትህና ካሳ ያሰጥ ይሁን ወደፊት እናያለን፡፡ ለጊዜው ግን የሀገር ባለውለታ የሆኑትን ያስታወሰው አካል የለም።
ሀቁ ግን፦ “ለውጡ” ሀገራቸውን በቅንነት ያገለገሉ የዎላይታ ወታደሮችንም ዋጋ አስከፍሏል፡፡ በዚያው ልክ ዎላይታ በኢትዮጵያ ፖለቲካና ኢኮኖሚ ያለው ተጽእኖ ፈጣሪነት ስጋት ላይ እንደወደቀና እንዲገለል ማድረጉ እየቀጠለ ነው፡፡ ለዚህ ፅሁፍ እውነተኛ መረጃ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን የተባበሩትን የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በድጋሚ ያመሰግናል። #Ethiopia #wolaitatimes