1000017558

የሲመተ ጵጵስና ስነ ስርዓት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነ ኢየሱስ ሱራፌል እና ሌሎች በተገኙበት በዛሬው ዕለት በክብር ተከናውኗል።

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ አቡነ ደጀኔ ሂዶቶን አዲሱ “የሶዶ ሀገረ ስብከት ጳጳስ” ብለው መሰየማቸውን ቫቲካን ሰኔ 12 ቀን 2016 ዓ.ም.ማወጁን መዘገባችን ይታወሳል።

አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ በካቶሊክ ቤተክርስቲያን በመንፈሳዊ እና በማህበራዊ አገልግሎታቸው የሚታወቁ ሲሆን የሀገር ስብከቱ ጳጳስ ሆነው ሲሾሙ ከአከባቢው የመጀመሪያውም እንደሆኑም ተነግሯል።

አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ በአሁን ወቅት የሶዶ ሀገረ ስብከት ዋና ሐዋሪያዊ አስተዳዳሪ እና የቆንቶ አባ ፓስካል ቴክኒክ እና ሙያ ኮሌጅ ዲን ሆኖ እያገለገሉ ነበር። የክህነት አገልግሎታቸውን በዎላይታ ውስጥ በሚገኘው በታላቁ ዱቦ ሉርድ ማርያም ደብር የጀመሩት አቡነ ደጀኔ ከዚህ በፊት በዱቦ፥ በቆንቶ፥ በአዲስ አበባ እና በውጭ አገር በካናዳ አገልግለዋል። የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርታቸውንም ካናዳ በሚገኘው ዩኒቨርሲቲ ተቀብለዋል።

“ቤተክርስቲያኗ ከአካባቢው በርካታ በመንፈሳዊና በትምህርት ዝግጅታቸውም እውቅ አገልጋዮች እያሏት ሀገር ስብከቱን እንዲመሩ ዕድል ያልሰጠች ቢሆንም አሁን በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ አቡነ ደጀኔ ሂዶቶን ጳጳስ አድርጋ መሾሟ የሚደነቅና ሌሎች ሀይማኖቶችም ሊከተሉ የሚገባ ተምሳሌታዊ እርምጃ ነው” በሚል በእምነቱ ተከታዮች ጭምር ተደንቋል።

የእሳቸው መሾም ዜና ለዎላይታ ካቶሊካዊያን ትልቅ ደስታ የፈጠረ ሲሆን የታሪክ ምንጮች እንደሚገልጹት ካቶሊክ እምነት ወደ ዎላይታ አከባቢ የገባበው በ1920ቹ አከባቢ በአሁኑ ቦሎሶ ሶሬ ወረዳ በዱቦ (አረካ) አድርጎ በታዋቂው ፈረንሳያዊ ካቶሊካዊ ካህን በአባ ፓስካል አማካኝነች ነበር።

በሌላ በኩል የሶዶ ሀገር ስብከት ከመንፈሳዊ አገልግሎት ባሻገር ከረጅም ዓመታት ጀምሮ በዎላይታ አከባቢ እና በዙሪያዋ በትምህርት፥ በጤና እና በማሕበራዊ አገልግሎቶች በቢሊዮን ብር የሚቆጠር ገንዘብ በመመደብ የተለያዩ የልማት ስራዎችን እያከናወነ የሚገኝ እንደሆነ መረጃዎች ያመለክታሉ።

የአቡኔ ደጄኔ የሲመተ ጵጵስና ስነ ስርዓት ለማስፈጸም በቦታው የተገኙት የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ ካርዲናል ብርሃነኢየሱስ ሱራፌል የዎላይታ ሕዝብ በሀይማኖት ልዩነት ሳይከፋፈል ገና ዎላይታ መግቢያ በር ከሆነችው ከድምቱ ከተማ ጀምሮ ያሳዩት አክብሮት ካቶሊክ ቤቴክርስቲያን አገልግሎቷ “የሁሉም በሁሉም መሆኑን ያመላከተ ነው” በሚል ለተደረገው ደማቅ አቀባበል አመስግነዋል።

ከአከባቢው በታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ በርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፖፕ ፍራንሲስ አቡነ የሀገረ ስብከት ጳጳስ ሆነው እንዲያገለግሉ ቫቲካን በማወጁ በዛሬው ዕለት በይፋ በዓለ ሲመት አድረገው አገልግሎት ለጀመሩት አቡነ ደጀኔ ሂዶቶ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ መልካም የአገልግሎት ዘመን እንዲሆንላቸው ይመኛል። #WolaitaTimes