
በአሁኑ ወቅት በበርካታ የዓለም አቀፍ ድርጅቶች ውስጥ በቦርድ ሰብሳቢነትና አባልነት እያገለገሉ የሚገኙት የቀድሞ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ተቋሙ የቦርድ ሰብሳቢ አድርጎ መሾሙን ይፋ አድርጓል።
አቶ ኃይለማርያም የዚሁ ተቋም የስምንት አመት የቦርድ ሰብሳቢነት ጊዜያቸውን ካጠናቁቀው የምስራቅ እና ደቡብ አፍሪካ የጋራ ገበያ ዋና ፀሀፊ እና የቀድሞ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ምክትል ሊቀመንበር ከነበሩት ኬንያዊው አምባሳደር ኢራስተስ ምዌንቻን በመተካት በቦርድ ሰብሳቢነት የተሾሙ ስለመሆኑም ተነግሯል።

ተቋሙ የእሳቸው ቦርድ ሰብሳቢነት ሹመት በተመለከተ በይፋዊ ዌብሳይቱ “በሀገራዊ እና አህጉራዊ ደረጃዎች ልምድ ያለው ከፍተኛ የፖለቲካ መሪ እንደመሆኖ፣ የአቶ ኃይለማርያም እውቀት እና ልምድ ተቋሙን በአዲሱ የሰባት ዓመት ስትራቴጂ ለመምራት ቁልፍ ሚና ይጫወታል፥ የአቶ ሀይለማርያም በአፍሪካ ውስጥ ባሉ እንቅፋቶች እና ዕድሎች ላይ ያለው ሰፊ እውቀት፣ ልምድ እና ግንዛቤ ያላቸው በመሆኑ ለተቋሙ ቀጣይ ምዕራፍ ውጤታማ ጉዞ በዋጋ ሊተመን የማይችል ልዩ መሪ ያደርጓቸዋል” በሚል ገልጿቸዋል።
ትኩረቱ የዲጂታላይዜሽን አቅምን ለመጠቀም፣ የአፍሪካ ላኪዎች ዝቅተኛ የካርበን ንግድ ፈር ቀዳጅ እንዲሆኑ ድጋፍ እናደርጋለን፣ ከምግብ ዋስትና ጀርባ ያሉትን ዋና የንግድ ጉዳዮችን ለመፍታት እና ሁሉን አቀፍ ንግድን በማበረታታት የንግድ ልውውጥን በማሳደግ እና የንግድን ቀጣይነትና አሳታፊነት በማሳደግ ሰፊ የስራ እድል ፈጠራን፣ ድህነትን መቀነስ እና የተሻሻለ የኢኮኖሚ እድገትን ለማምጣት አላማ ያደረገ ግዙፍ ተቋም እንደሆነም ተገልጿል።
የተቋሙ ዓላማ በአፍሪካ የንግድ ልውውጥና ዕድገት ለማሳደግ የተቋቋመ ሲሆን በቤልጂየም፣ በቢል እና ሜሊንዳ ጌትስ ፋውንዴሽን፣ በካናዳ፣ በዴንማርክ፣ በአውሮፓ ህብረት፣ በፊንላንድ፣ በፈረንሳይ፣ በአየርላንድ፣ በኔዘርላንድስ፣ በኖርዌይ፣ በዩናይትድ ኪንግደም እና በዩናይትድ ስቴትስ የሚደገፍ ነው።

በተጨማሪም ከመንግሥታዊ ድርጅቶች ጋር እንዲሁም ከአፍሪካ ኅብረት (AU)፣ ከአፍሪካ አህጉራዊ ነፃ የንግድ ቀጠና ሴክሬታሪያት፣ ከምስራቅ አፍሪካ ማህበረሰብ (ኢኤሲ)፣ ከምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ)፣ ከምስራቅ የጋራ ገበያ እና ደቡብ አፍሪካ (ኮሜሳ)፣ ከደቡብ አፍሪካ የጉምሩክ ዩኒየን (SACU)፣ ከብሄራዊ መንግስታት፣ የግሉ ሴክተር እና የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ጋርም ቀጥታ በቅርበት እንደሚሰራ ከተቋሙ ዌብሳይት ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
የተቋሙ ዋና መሥሪያ ቤት በናይሮቢ ኬንያ የሚገኝ ሲሆን ቅርንጫፍ ቢሮዎቹ በብሩንዲ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ማላዊ፣ ሞዛምቢክ፣ ሩዋንዳ, ሶማሌላንድ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ኡጋንዳ እንዲሁም በዛምቢያ ሆኖ በመላውን አፍሪካ እየሰራ የሚገኝ እንደሆነም ተገልጿል።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ሃይለማርያም ከዩኒቨርስቲ አመራርነት ጀምረው በተለያዩ ደረጃዎች በአመራርነት የመሩ፣ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ያገለገሉና በአፍሪካ ሆነ በአለም አዲስ ክስተት በራሳቸው ፈቃድ ስልጣንን በሰላማዊ መንገድ በማስተላለፍ ሳያርፉ በሀገሪቱ ሆነ በአለምአቀፍ መድረክ ባካበቱት ጥልቅ እውቀት፣ ልምድና ተፈላጊነት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወኑ ይገኛሉ። #WolaitaTimes
በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ የተጠናቀረ ዘገባ ነው