
እንደተለመደው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ መግባት እችላለሁ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ተፈቅዷል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የሚዲያችንን ጥሪ ስለተቀበሉ እያመሰገንን ወደ ጥያቄ ስንገባ በአሁኑ ሰዓት መንግስት ለዎላይታ ሶዶ ከተማ የሚሰጣት ቦታ ላይ የዎላይታ ሕዝብ ደስተኛ ያልሆነዉ ለምንድነው ? ደስተኛ ነው ካሉም ሊያርሙን ይችላሉ።
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ደስተኛ እንኳን አይደለም። አንደኛዉ ምክንያት የዎላይታ ሕዝብ ከሚኒሊክ ና ከኃይለሥላሴ ጊዜ ጀምሮም ቢሆን ከተሞቹ የፖለቲካ እስረኛ መሆናቸዉ ያዉቃል። በለዉጡ ማግስት የዎላይታ ሕዝብ በከፍተኛ ደረጃ በማንነቱ የተጨፈጨፈባት አዋሳ እንኳን ብትታይ የዎላይታ ሕዝብ ተገዶ ሄዶ ከሌሎች ጋር የለማት ነች።
ለዘመናት ሕዝቡ በሌሎች አካባቢዎች እያለማ ባዶ እጁን ሲቀር ኖሯል። የሕዝቡ ወደ ሌሎች አካባቢዮች የሚፈልሰዉ በአካባቢዉ የሥራ እድል የሚያገኝበት ከሕዝብ ብዛቱና የመልማት ፍላጎቱ ጋር የሚመጣጠን ትልቅ ከተማ ስለሌለ ነው የሚለዉ አንዱ መከራከሪያ ነው።
እናም የክልል ጥያቄዉንም ብታይ ይሄንን ችግር ለመቅረፍ የሚያስችል ነበረ በአዋሳ፣ መቐለ፣ ባህርዳር እና የመሳሰሉት ከተሞች በኢትዮጵያ ከአዲስ አበባ ቀጥሎ እንደሚቀመጡት ዎላይታ ሶዶንም ከነኝህ ከተሞች ጋር በAbsolute congurence የክልል ቢሮዎች በሙሉ ለማግኘት በቋንቋዉ በከተማዉ ለመጠቀም መሠረተ ልማቶችን ለማግኘት በማለም ጭምር ነበረ።
በተለይም የአዋሳዉ ጥቃት የዎላይታ ሕዝብ ከማንም በላይ የተጨቆነ ሕዝብ ሆኖ እያለ ለሌሎች ቅድሚያ እንስጥ በሚል ፍልስፍና መመራት እንደሌለበት ያስረገጠ ነበረ። እናም ብልጽግና የጫነዉ አዲሱ ክልል ሕዝቡ የጠየቀዉ ክልል ካለመሆኑም በላይ የሕዝቡን ቁስል ያገናዘበ አይደለም። ስለዚህ የብልጽግና ፓርቲ መራሹ መንግስት ይሄንን ጉዳይ አልተረዳምና ሕዝቡ በአሁኑ ሰዓት ብልጽግና ስልጣን ሳይሆን ጨዋታ የያዘ አስመስሎታል እያለ ነው።
በተለያዩ ከተሞች የዎላይታ ሕዝብ ከለዉጡ በፊትም ከደረሱ ጥቃቶች ጋር ተያይዞ ሕዝቡ በእራሴ ቀንቋ የማወራበት ነገ የማልባረርበት የእራሴ ከተማ በእነ አዋሳ፣ ባህር ዳርና መቐለ ደረጃ እንዳለማ መንግስት የሚያስፈልገዉ ያድርግ ቢልም ሰሚ ስላጣ ከፍተኛ ቅሬታ አለ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአሁኑ ሰአት የደቡብ ኢትዮጵያ ባለ ስድስት መቀመጫ ሆኖ መደራጀቱንስ እንዴት ያያሉ ፍትሐዊ ነው ?ለአሰራርስ ይመቻል ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦እኔ ልመልስልህ የምችለዉ ከዎላይታ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ጥያቄ አንጻር ነው። ያም ምንድነው “እኛ ክልል እንሁን” የሚል እንጂ ከእነ እገሌ ጋር ክልል ፈጥሬ ዋና ከተማ ላግኝ የሚል አልነበረም። ስለዚህ የዎላይታ ሕዝብ የሚገባዉን ተከልክሏል፤ መሰል ክልል ለዎላይታ አይነት ብሔር አይመከርም፥ ምክንያቱም ከሀገረመንግስት ግምባታ አቅጣጫ ላይ ባሉ የሚጋጩ ሕልሞች ምክንያት ሲቀጣ እንዲሁም ተንኮል ሲሰራበት የኖረ ሕዝብ ነው።
ይህ ክልል ለተንኮል አጋልጦታል ሕዝቡን። ኢትዮጵያ ብሔራዊ መግባባት ያለባት ሀገር አይደለችም። ከነችግሩም ያለዉ ሕገመንግሥት የሚከበርበት ሕገመንግሥታዊነት ያለበት ሐገር አይደለችም፥ Deep State በ Federal Bureaucracy ዉስጥ በደምብ አለ፥ የድሮ ብሔር ጨቋኝ ስርዓቶች አይነት ፍላጎቶች በመንግስት አካላት ዉስጥ በደምብ ይታያሉ፤ እስከ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ሚኒስትሮች ድረስ አድሏዊ አሰራር የሰፈነበት ነው፥ አግላይነት የሰፈነባት ሐገር ነች። በዚህ ሁሉ ዉስጥ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ፍትሐዊ ነገር ታገኛለች ማለት አይቻልም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ከሰሞኑ የጠቅላይ ሚኒቴር ዶክተር አብይ አህመድ ንግግር የኮሪደር ልማቱ ዎላይታ ሶዶ ከተማ ላይ እንደማይሰራ በመታወቁ ሕዝቡ ዉስጥ ለዉስጥ የበቀል ዱላ እያረፈብን ነው እያለ ነው። ከዚህ በፊትም አየር ማረፊያ ሲጠየቁ “አርባምንጭ ሄዳቹ ኑ” ብለው ነበረ አሁን ሊሰራ ቢሆንም የኢንዱስትሪ ዞንም አንሰራም ብለዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ እዉነትም አንዳንዶች እንደሚሉት ለዎላይታ የተለዬ ጥላቻ ያለዉ ይመስልዎታል?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በግሌ ብዙ ግራ የሚያጋቡኝ ነገሮች አሉ። ይህ ሰዉ ስልጣን የተረከበዉ በሰላማዊ መንገድ ከዎላይታ ተወላጅ ቢሆንም የሚሰሩ ስራዎች ግን በጣም ግራ ያጋባሉ። ለምሳሌ ወይዘሮ ጫልቱ ሳኔ የሚመሩት ሚኒስቴር መስሪያ ቤት ለከተማ ጉዳዮች የበለጠ ቀረቤታ እንዳለዉ እሙን ነው። ሲሰራም ግልጽ መሥፈርት አሰቀምጦ ነው።
ዎላይታ ሶዶ ከአራት የኢትዮጵያ ከተሞች ጋር ተወዳድራ ተመርጣ የሚተገበር የፍሳሽ ፕሮጀክት እንደሚኖር ተገልጿል፤ የከተሞች ቀንም ተከብሮባታል። ይህ የሕዝብ ብዛቱን የከተማዋን የመልማትና የመስፋት አቅሟንም ያገናዘበ ነበር። የጠቅላይ ሚኒሰትር ጽሕፈት ቤት በኩል ፍትሐዊነት በዎላይታና በዎላይታ ሶዶ ጉዳይ ፍትሐዊነት ታይቶ አይታወቅም።
የደቡብ ክልል ለምሳሌ በስፖርት ታሪክም በተሳትፎም በተመልካችም ብዛትም ዎላይታ ሶዶ ሐገር ሳይሆን አፍሪካ ካወቃት ዉሎ አድሯል። በአፍሪካ መድረክ ዎላይታ ዲቻ ሜዳ አጥቶ በአዋሳ መጫወቱ ይታወቃል። በአመራሮች ሸኩቻ የዎላይታ ተወካይ ታግዶ በሌለበት ስቴዲየም ሌላ ቦታ እንዲጀመር በሚዲያ በማስዘገብ ተደርጓል።
የፈደሬሽን ምክር ቤት አመራሮች ለዎላይታ ጥሩ አመለካከት እንደሌላቸዉ የምታዉቀዉ የዶርዜና ቁጫ ማንነትና የራስ አስተዳደር ጥያቄ በመታፈኑ ብቻ አይደለም። በሕዝበ ዉሳኔ የሰሩትን ደባ አይተናል፤ የብሔረሰቦች ቀን አስኮብልለዋል። ብዙ ሴራ አለ። በተለይ በአሁኑ ሰአት በክልልም ሆነ በፈደራል ዎላይታ ሚዛናዊ የስልጣን ድርሻ ስለተነፈገ ከባድ ደባዎች እየተፈጸሙበት ነው። የጠቅላይ ሚኒስትሩን ጉዳይ በግለሰብ ደረጃ ማየት አልፈልግም በሥርአቱ ዉስጥ ግን ለዎላይታ ጥላቻ ያለዉ አሰራር በስፋት ይታያል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ታዲያስ መፍትሔ የሚሉት ምንድነው ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ለመንግሥት ሆነ በዉስጡ ላሉ ጸረ_ዎላይታ ግለሰቦች የምለዉ መርህና ሕገመንግሥት የማይገዛቸዉ አሰራሮች ለዘላቂ ወንድማማችነት አይጠቅሙም። የዎላይታ ብሔረተኝነትን ለማዳከም የሚያልሙም ካሉ በአለም ብሔረተኝነትን ለማዳከም የወሰዷቸዉ እርምጃዎች ዉጤታቸዉ ከተፈለገዉ በተቃራኒ ነው። በአብዛኛው እናም የተበደለን የመካስ አካሄድ ይበጃል እላለሁ።
ከዛ ባለፈ የዎላይታ ሕዝብ አሁንም ከመንደር ጸብና ሽሚያ ለመዉጣት ለክልልነት በሀገራዊ ምክክሩም ሆነ በቀጣዩ ምርጫ በሕገመንግስታዊ መንገድ መፋለም አለበት። የተቃዋሚ ፓርቲዎችም በግልጽ ሕዝቡን ከዚህ ለተንኮል ካጋለጣቸዉ ክልል ነጻ የሚያወጣ የዎላይታን ክልል ጥያቄ በድጋሚ እንደሚያነሱ በግልጽ መቀስቀስ አለባቸዉ እላለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዛሬው የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።