
እንደተለመደው የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት በተለያዩ ሀገራዊ ጉዳዮች ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ ከፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ጋር ቆይታ አድርጎ ዝግጀት አሰናድተው እንደሚከተለው አቅርቧል ተጋበዙልን🙏
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንግዳችን እንደወትሮው ጥሪያችንን ተቀብለዉ እንኳን ደህና መጡ። ያዉ ባለፈዉ እንዳሉት የሚዲያችን ቤተሰብ ስለሆኑ ቀጥታ ወደ ጥያቄ መግባት እችላለሁ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ተፈቅዷል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም፦ ከሰሞኑ የዎላይታ ብልጽግና አመራሮች በአዳማ ከተማ በነበረዉ የከፍተኛ አመራሮች ስልጠና ላይ ጊፓታን ማክበራቸዉና በመሃላቸዉ “ጸብ አለ” ተብሎ በአደባባይ ሲታሙ የነበሩ እነ ተስፋዬ ይገዙና ዳጋቶ ኩምቤ በጋራ እየተሳሳቁ ምግብ ሲበሉ የሚያሳዩ ፎቶ ግራፎች በትናንትናው ዕለት ወጥተዋል የእዉነት እርቅ ይመስልሃል?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በመጀመሪያ በዎላይታ ባህል ጊፓታ የእርቅ በዓል መሆኑ ይታወቃል። እርቅ የሚለዉን ቃል ወደ ፖለቲካ መቀየር አለብን፤ ያም ያለፈዉን መገምገምና መስማማት ለአሁን የጋራ መረዳት መፍጠር ለወደፊት በጋራ ለመሥራትና ለመታገል መሥማማት ይመስለኛል። በዚህ ደረጃ ጥልቀት ያለዉ ነገር የተደረገ አይመስለኝም። ነገር ግን አንድ ጥሩ ነገር ልዩነቱን የፈጠረዉ ከበላይ አካል በዎላይታ ሕዝብ ላይ የሚደረገዉ ኢ_ሕገመንግሥታዊ ጫናና አፈና መሆኑ ነው። ይህንን አፈናና ጫና በምን መልኩ እናስተናግደዉ የሚለዉ ነው።
እንግዲህ ያ ብዙዎችን እንደለያየ ግልጽ ነው። ቀጥሎ በግልም በቡድንም የደረሱ ግፎች የዛ ጫና ዉጤቶች ናቸዉ። ዋናዉ ነገር እገሌ እንዲህ አደረገኝ፣ በእነ እገሌ አሰደበኝ፣ በእነ እገሌ አሳሰረኝ፣ እገሌ አቤልጅ ኔትወርክ ፈጠረ፣ እገሌ ጎሰኛ ሆነ፣ እገሌ ከመንግስት ጋር በሚያጋጭ መንገድ ሄደ የሚለዉ አይደለም።

ዋናዉ ነገር ለምን በጋራ አልቆምንም? ለምን ተሰብስበን እስከመጨረሻዉ በአንድ ሕዝባዊ አቋም አልጸናንም? ለምን ተከፋፈልን? ለምን በተናጠል ለመጓዝ ወሰንን? ለምን መጠላለፍን እንደአማራጭ ወሰድን? የነዚህ ጥያቄዎች መልስ ሁሉንም ጥፋተኛ የሚያደርግ ይመስለኛል።
ችግሩ በጣም መሠረታዊ በሚባለዉ የሕዝብ ጉዳይ ላይ መለያየታችን ነው። መስዋዕትነትም ካለ በጋራ መክፈል ነበረብን፤ እስከመጨረሻዉም በጋራ እየተወያየን መጓዝ ነበረብን። መጠላለፍን እንደ አማራጭ ማየት አልነበረብንም የሚል አቋም ነው አስታራቂዉ። በዚህ ከተስማማን ይቅርታ መጠያየቁና ሕዝቡን ለመካስ በጋራ መሥራቱ ከባድ አይመስለኝም። አንዱ ሌላዉ ላይ ያደረጋቸዉ ቀሪ ጉዳዮች ከሳቅና ጨዋታ ፍጆታነት አያልፉም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በቅርቡ ከፌደራል የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ፕረዚዳንት ሆነው ተሹመው የመጡት አቶ ገብረመስቀል ጫላ በዎላይታ የ “Reconciliation” መድረክ ይካሄዳል ብለዋል። እዉነትም ከዚህ በፊት የተራራቁ አመራሮችና የመብት ተሟጋቾች ከታረቁ በአሁኑ ሰዓት ከባድ ችግር ዉስጥ ለሚገኘዉ ለዎላይታ ሕዝብ ምን ይፈይዳል ብለን እንጠብቅ ?
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ፋይዳዉ ዘርፈ ብዙ ሊሆን ይችላል፥ ካልሆነም ቢያንስ ሌላ የሰላማዊና ሕገመንግስታዊ የትግል ምዕራፍ ሊወልድ ይችላል። ልዩነቱ ከብልጽግና ጀምሮ ተቃዋሚዎችን ነክቶ ገለልተኛ ሊህቃንንም ያቀያየመ በመሆኑ የ “Reconciliation” መድረክ ሐሳብ ሕዝባዊ ተቀባይነት ያገኘ ነው። ከመድረኩ በሁዋላ እንግዲህ በጋራ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመሥራት መስማማት ይጠበቃል።
በዞናችን በፍጹም አፈና ስር የወደቀዉ ሚዲያና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ለሁሉም ክፍት መሆን አለበት። ተቃዋሚ ፓርቲዎች በነጻነት መደራጀትና ከሕዝቡ ጋር እንዲገናኙ መፈቀድ አለበት፥ ሚዲያዎች የሕዝብ እንደመሆናቸዉ የሙያ ስነምግባርና የየራሳቸዉን Editorial Policy ተከትለዉ በነጻነት መሥራት አለባቸዉ። የተሰደዱ፣ የተሰቃዩ ፖለቲከኞችና ጋዜጠኞች አሉ። መሰል አሰራሮች መክሰም አለባቸዉ፥ መክሰማቸዉም ይፋ መደረግ አለበት።
በፖለቲካ ጉዳዮች የዎላይታ ብልጽግና ቅርንጫፍ ብቻ መሆኑ አስቸጋሪ ቢሆንም ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች በጋራ በዞኑ ማስፈጸም ከቻለ ትልቅ እርምጃ ነው። ያንን ማድረግ ከቻሉ የበላይ አካላት በዎላይታ ሕዝብ ላይ የሰሩትንና እየሰሩ ያሉትን ደባ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያጋልጣሉ ብዬ አስባለሁ። ሕዝቡን የማንቃት ሥራ ቢያስፈልግም አሁንም ሕዝቡ ያለዉ ግንዛቤ ቀላል የሚባል አይደለም።
ብያንስ ዞኑን ሕግና ሥርአት ተከትለዉ በጋራ ካስተዳደሩ፣ የዞን፣ የክልል እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸዉን ተጠቅመዉ የሕዝቡን ጥያቄዎች የማያነሱበት ምክንያት የለም።
ኢ_ሕገመንግሥታዊ አሰራሮችን የማይጋፈጡበት እና የማይታገሉበት ምንክያት የለም። ዞኑን በማስተዳደር ጉዳይ ላይ ምሁራንን ሰብስበዉ ማማከር የማይችሉበት ምክንያት አይኖርም። ባስፈለገ ሕጋዊ መንገድ ሁሉ ሕዝቡ አብሯቸዉ የማይታገልበት ምክንያትም የለም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ የበላይ አካላት እነዚህን ነገሮች የሚፈቅዱ ይመስልሃል ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ መብትኮ ለምኖ የሚሰጥህ የለም። ታግለህ ነው የምታስከብረዉ። ከልካይ ነኝ ባይም ከመጣ በጋራ እንታገል ነው እኔ የምለዉ። የዎላይታ ሕዝብ አሁን ባለዉ መልኩ ታፍኖ የሚኖር ሕዝብ አይደለም። አጼዎቹን እንኳን እየጠየቀ እየታገለ የኖረ ነው። የዎላይታ ሕዝብ በጋራ ሲቆም ምን ማድረግ እንደሚችል ራሱም፣ ወዳጅም በፈቃዳቸዉ የሚጠሉንም አንዳንድ አካላትም የሚያዉቁት ሀቅ ነው።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዛሬው የፓለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ከላይ በተነሱ ጉዳዮች ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፓለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።