የጀኔቫው ሰልፍ የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ሕብረተሰብ በሚገባ ያሳወቀ መሆኑ ተገለፀ

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና መቀመጫ በሆነችው ጀኔቫ፣ ስዊዘርላንድ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ያካሄዱት ሰላማዊ ሰልፍ በአሁኑ ሰዓት በሀገሪቱ ውስጥ ያለውን ሁኔታና የኢትዮጵያን እውነታ ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚገባ ያሳወቀና በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ለመግባት የሚደረገውን ሙከራ አጥበቆ ያወገዘ በመሆኑ የታሰበለትን ዓላማ በሚገባ ያሳካ እንደነበረ አዘጋጆቹ አስታወቁ።
ከአዘጋጅ ኮሚቴው አባላት መካከል አንዱ የሆነው አቶ ኃይሉ ኡርጌሳ ለአገር ውስጥ ሚዲያወች እንዳስታወቁት፤ በትግራይ ክልል የተካሄደውን ሕግን የማስከበርና የህልውና ዘመቻ ተከትሎ ፀረ ኢትዮጵያ አካላት የሚያካሂዱትን ሃሰተኛ የሚዲያ ዘመቻና ያልተገባ የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት በመቃወም በጀኔቫ የተካሄደው የኢትዮጵያውያኑ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ስኬታማ የሚባል ነበረ።
ጀኔቫ በሚገኘው የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ጽህፈት ቤት ፊት ለፊት በተካሄደው ሰላማዊ ሰልፍ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያኑ የሀገርን ህልውናና ሉዓላዊነት ለማስቀጠል በህወሓት ከሃዲ ቡድን ላይ የተወሰደውን ሕግን የማስከበር የህልውና ዘመቻ ተከትሎ አንዳንድ ፀረ ኢትዮጵያ አካላት የሚያሰራጩት መረጃ ሃሰተኛ መሆኑን አጋልጠውበታል ብለዋል ሲል ኢፕድ ዘግቧል።