1000020920

በዎላይታ አከባቢ በየጊዜው በተለያዩ ደረጃ የሚገኙ አመራሮች መፈላለግና ፍጥቻ የፈጠረው፦ እንደ ህዝብ በፌደራል ሆነ በክልል ፖለቲካዊ ተሰሚነት ማጣት፣ ኢኮኖሚያዊ አድሎና ማህበራዊ ቀውስ መቼና እንዴት ይፈታል? እንዲሁም የውሃ ሽታ ስለሆነው የእርቅ መድረክ በተመለከተና በተያያዥ ጉዳዮች ላይ እንደወትሮው ሁሉ ፕሮፈሰር ማሪንዶስ ጦና ከዎላይታ ታይምስ ሚዲያ ቆይታ በማድረግ ለጥያቄዎቹ እንደሚከተለው ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋልና ቀጥታ ወደዛ 👇

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሰላም ብለናል ፕሮፌሰር።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሰላም ብያለሁ ቤተሰቦቻችን።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ መልካም። በዎላይታ ዞን ባሉ አመራሮች መሐል የተሻለ አቅም ያላቸዉ ሲንቀሳቀሱ ያለመደሰትና፣ በጋራ ዘገም ያለ እንቅስቃሴ ማድረግ አለብን የሚል ፍላጎት ያላቸዉ አሉ የሚሉ ሰዎች አሉ በዚህ ላይ ምን የሚሉት ነገር አለ? የዚሁ አካሄዳቸው እንደ ህዝብ ያደረሰው ተፅዕኖ ምንድነው ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ በጋራ መንቀሳቀስ ጥሩ ነዉ። ዘገምተኛነት ግን ጥሩ አይደለም። ሁሉም አመራር በየ ሴክተሩ የተጣለበትን ሓላፊነት መወጣት፣ ከሥሩ ያሉትን ማስተባበር፣ እንዲሁም ከሌሎች ሴክተሮች ጋርም የመተባበር ኃላፊነት አለበት። አንድ የዎላይታ ተወላጅና የክልሉ ከፍተኛ ባለስልጣን በዎላይታ ቴለቪዥን ሲናገር የሰማሁት ነው።

ስብሰባዉ እነ አቶ ገብረመስቀል ጫላና አቶ ጴጥሮስ ወልደማርያም በዎላይታ የዉስጥ ገቢን አሟጦ ስለመሰብሰብ ዉይይት መድረክ የመሩበት ነው። እናም እንደ ይሄው አመራሩ ገለፃ “በደምብ የሚንቀሳቀስ አመራር ካለ መፈረጅ አለ፤ ስለዚህ በጋራ መንቀሳቀስ ያስፈልጋል” ይላል።

አንዳንድ የዎላይታ ዞን ካድሬዎች በጣም አስገራሚ ናቸዉ ስልጣን ለመያዝ የሚፈልጉት ሕዝቡን ለማገልገል ሳይሆን ለደሞዝና ጥቅማጥቅም ነው። ስልጣን ሲይዙ የሚደሰቱትም አንዳች ለዉጥ ለማምጣት እድል በማግኘታቸዉ ሳይሆን ለገንዘብ ነው። ጠንክሮ የሚሠራ አመራር ካለም የሚያስጠቁራቸዉ ስለሚመስላቸዉ ይፈርጁታል። የአመራሩ ወቀሳ የሚነግረን ያንን ነው። ስለዚህ አንድነት ጥሩ ሆኖ የተጣለበትን ኃላፊነት በተሻለ ሁኔታ የሚወጣ ሰዉ መበረታታት አለበት፦ ማንም ይሁን ማን።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በዎላይታ ዞን በቅርቡ ሰፋ ያለ ሹም ሽር ተደርጓል ያንን እንዴት ያዩታል?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በዞኑ በቅርቡ ከወትሮዉ ሰፋ ያለ ሹም ሽር ተደርጓል። ተስፋ ሰጪ ነገሮችም ያሉበት ይመስላል፤ ክፍፍል አያስፈልግም ስንልም ገግመዉ ነገሮችን ሲያከሩ የነበሩ፣ ተገፍተዉ የነበሩ፣ ወጣቶች እድል የተሰጣቸዉ ይመስላል። ነገር ግን እነኚህ ሁለት ነገር ማወቅ አለባቸዉ።

አንደኛዉ፦ አሁን ባለዉ ነባራዊ ሁኔታ አምነዉ ስልጣን እስከያዙ ድረስ በተጨባጭ ከነበሩት የተሻለ የሚቆጠር ነገር መሥራት አለባቸዉ። ከቀድሞዎቹም ጋር ያላቸዉ ልዩነት ስልጣን ከያዝን የተሻለ መሥራት እንችላለን የሚል ብቻ ይሆናል። ጣራቸዉም ሕገመንግሥት ሳይሆን አገዛዙ የፈቀደዉ የመጫወቻ ሜዳ ነው። ፖለቲካቸዉ ግን የመንደርና የቀበሌ መሆኑ እርግጥ ነዉና በነሱ ላይ የምንጥለዉ ትልቅ ተስፋ አይኖርም። ለወንበሩ ብቻ ከሆነ ጩሄታቸዉ ማለቴ ነው።

ሁለተኛዉ፦ አይ እኛ ጣራችን ሕገመንግሥቱ ነው ከሆነ የሚሉን በግሌ በጣም የምደግፋቸዉ ይሆናል ምክንያቱም በክልልም ሆነ በፈደራል ያለዉን ኢፍትሐዊነት መጋፈጥ ስለሚጀምሩ የሞተ ፖለተካ ላይ ነፍስን ስለሚዘሩ። ያኔ የቀድሞዎቹን እንኳን ከሰሱ ብለን እናጨበጭብላቿለን። ያለ ምንም ጥርጥር መላዉ የዎላይታ ሕዝብ ይደግፋቸዋል ከጎናቸዉም ይሰለፋል። በተረፈ ለሁሉም መልካም የሥራ ዘመን እንመኛለን። እኔ በግሌ በጣም የሚያስጠላኝ ነገር መጠላለፍ ነው። ያንን አስወግዱ፣ ተናበቡ፣ በጋራ ሥሩም ማለት ፈልጋለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደዉ የመከፋፈሉን ነገር ካነሳን አይቀር ይህ ነገር በቅርቡ በ “Reconciliation” መድረክ መፍትሔ ያገኛል ተብሏልና እንደዉ የነገሩ ሰፋት ቀላል ባይሆንም ሁሉንም አመራር ይመለከታል ማለት እንችላለን?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ በርግጥ ችግሩ ሰፊ ቢሆንም ክፍፍልን የማይደግፉ ጎራም ይዘዉ በዛ ደስተኛ ያልሆኑ የነበሩ ይመስለኛል። ሕዝቡን በክፍፍልና በጎራ ደስቸኛ አይደለም። በተረፈ ስልጣን ማንም ቢሆን የያዘ ቢኖር ወንበር ከማሞቅ ባለፈ ተጨባጭ ነገር መሥራት ይኖርበታል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአሁኑ ሰዓት በዞኑ ለዉጥ አለ ብለዉ በልበ ሙሉነት የሚናገሩ አሉ፣ እኛ እነዛን ነገሮች በምን እንመዝን ይላሉ?

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ባለፈዉም ብያለሁ፦ የታፈኑ ነገሮችን ነጻ ማዉጣት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንቅስቃሴ አለመገደብና ማሳተፍ፣ የተሰደዱ ጋዜጠኞች አሉ እና ሚዲያዉን ነጻ ማዉጣት፣ ባሉ ሕጋዊ መንገዶች ከዞን፣ ክልልና የፈደራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕዝቡን ሁሉንም አይነት ሕጋዊ ጥያቄዎች በነጻነት ማንጸባረቅ፣ በዞኑ ተጨባጭ ለዉጦችን ማምጣት፣ ምሁራንን ማሰባሰብ፣ በመልካም አስተዳደር ረገድ ሕዝቡ የሚመሰክርላቸዉን ለዉጦች ማምጣት፣ በተለይ በአሁኑ ሰአት Innovative አመራር በየዘርፉ ያስፈልጋል። የሕግ የበላይነትን ማስፈን ያስፈልጋል።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።

✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።

🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።

ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ የፖለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።

WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia

በጋዜጠኛ ናትናኤል ጌቾ ቃለመጠየቅ ተደርጎ የተዘጋጀ ዘገባ ነው