
“ፋኖ በለስ ቀንቶት አዲስ አበባ ቢደርስስ? “እኔ ፋኖ ተሰማራ ሳይሆን ፋኖ ተደራደር እላለሁ” – ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ለዚሁ እና ለተያያዥ ጉዳዮች ምላሽ አላቸው፥ ዘገባውም እንደሚከተለው ቀርቧል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ ሚዲያ፦ ሰላም ብለናል ፕሮፌሰር።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ ሰላም ብያለሁ ቤተሰቦቻችን እኔም።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአማራ ክልል እየተካሄደ ባለዉ ጦርነት ከሰሞኑ አዳዲስ ዘመቻዎች ከሁለቱም ታዉጀዋል፣ ችግሩ በሰላም ይሆን በጦርነት ይቋጫል በቅርቡ ማለት ይቻላል?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ አይመስለኝም። ፋኖ አንድ ወጥ አደረጃጀት እስካልፈጠረ ድረስ የአማራ ክልሉ ግጭት በቀላሉም በቅርቡም የሚያልቅ አይመስለኝም። የኢትዮጲያ መከላከያ ሠራዊት ቃል አቀባይ የሆኑት ኮለኔል ጌትነት ከአማራ ክልል አንድ ባለስልጣን ጋር ሆነዉ በሰጡት መግለጫ በጣም የተጠና ነው ያሉት አዲሱ የመከላከያ እርምጃ የሚያበቃሙ የክልሉ ሰላም ሲመለስ ነው ብለዋል።
በሌላ በኩል ደግሞ ከፋኖ መሪዎች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለትና በጎጃም አካባቢ የሚንቀሳቀሰዉ ዘመነ ካሴ”ዘመቻ 100 ተራሮች” የሚባል ዘመቻ መጀመራቸዉን ተናግሯል ከሰሞኑ። በአማራ ክልል 324 በስም የሚታወቁ ተራሮች እንዳሉ መረጃዎች ይጠቁማሉ። በወታደራዊ ሳይንስ ደግሞ ተራሮች እንደ ወታደራዊ ገዢ መሬት የሚታዩበት ሁኔታ አለ። የጎጃም ፋኖም ከዚህ በመነሳት ይመስላል በተራራ የተዘየመ ዘመቻ ያወጀዉ። የሁለቱም ዘመቻ ያስቀመጡትን ግብ ያሳካል የሚል እምነት የለኝም።
የተለያዩ ምንጮች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ደግሞ ከሰሞኑ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች ከባባድ ዉጊያዎች እየተደረጉ ነው። የእርስ በርስ ጦርነት ነውና በሁለቱም ወገን ያለዉ እልቂትና ጉዳት የኛ ስለሆነ በጣም አሳዛኝ ነው። ችግሩን ለሰላም ሩቅ ያደረገዉ ዋነኛው ችግር ፋኖ አንድ ወጥ አመራር የሚመራዉ አለመሆኑ ለጦርነትም ለሰላምም የማይመች ሁኔታን ፈጥሯል።
ግጭቱ በመደበኛ ሰራዊት መቆጣጠር ወደ ማይቻልበት አቅጣጫ የመሔድ እድሉ ሰፊ ነው። ያም ቢሆን መንግስት የአማራን ክልል እንዲለቅ ቢያደርገዉ እንጂ የተለዬ የሚፈጥረዉ ነገር የለም። አሁንም የሚሻለዉ ፋኖ የጋራ አመራር ፈጥሮ ለድርድር ቢቀመጥ ነው።
ፈደራል መንግስቱን ከክልሉ ማስወጣት መቻል ለፋኖ ቀጣይ ዝግጅት ምቹ ሁኔታ ሊፈጥር የሚችለዉን ያህል አዲሲ የፋኖ ጠላቶችን ሕብረት ሊፈጥር ይችላል። ከዛም ብሶ ፋኖ ክልሉን እንደያዘዉ እነሱም ክልላቸዉን የሚይዙ ሌላ ተጨማሪ ኃይሎችን ሊፈጥርም ይችላል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ጦርነቱ ከተካረረ ምን አይነት ነገሮች ሊከሰቱ ይችላሉ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ጦርነቱ እየከበደ ከመጣ በመሐል ሐገርም በስመ ኦሮማራ የተያዙ ወንበሮችም ወደተለያዬ በኦሮማራ ለተገፉ ሊህቃን ሊተላለፍ ይችላል። የጅምላ እስሩ ያልተጠበቁ ሰዎችንም ማካተት ሊጀምር ይችላል። እስርና ማሳደዱ ወደተለያዩ የግል ዘርፎችም ሆነ ሐይማኖት ተቋማት እንዲሁም ወደ ሚዲያዎች ሊያመራ ይችላል።
እስካሁን “ጃዉሳ”ተብሎ እንደ ዘራፊ የተፈረጀዉ ቡድን በሽብርተኝነት ሊፈረጅ ይችላል። በተለይ የፈደራል መንግስት ኦሮ_ማራን አዉግዞ ሌላ የተገፉ አካባቢ ሊህቃንን ስልጣን በማጋራት በአደባባይ የፈደራል ሥርዓቱንና የብሔረሰቦችን መብት ለማስጠበቅ እንደሚዋጋ ሊያዉጅ ይችላል።
ሲጓተት የከረመዉ የፕሪቶሪያ ስምምነት በፍጥነት ወደተሟላ ትግበራ እንዲሄድ ሊደረግ ይችላል። የአማራ ሕዝብ በመላዉ ኢትዮጵያ ከወንድም ሕዝቦች ጋር አብሮ የሚኖር እንደመሆኑ ብዙ አላስፈላጊ ግጭትና ማሳደድ ሊደርስበት ይችላል። በተለይ መከላከያ ላይ የሚደርስ ሞት ወደተለያዩ አካባቢዎች መርዶዉ ሲመጣ ጥላቻን ያባዛል።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ፋኖ በለስ ቀንቶት አዲስ አበባ ቢደርስስ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ፋኖ በጦርነት በለስ ቢቀናዉ እና አዲስ አበባ ቢደርስ እንኳን እንደ 1983 ህወሓት ኢትዮጵያን መቆጣጠሩ ዘበት ነው። ምክንያቱም በተለያዩ አካባቢዎች በጣም የተጠናከሩ ታጣቂ ኃይሎች መፈጠራቸዉ አይቀሬ ነውና። ሕወሐት ትግራይን ተቆጣጥሮ ነው ያለዉ በኦሮሚያ በሚሊየኖች ኦነሰ ታጣቂዎች ማደራጀቱ አይቀርም በተለያዩ የደቡብና ሱማሌ አካባቢዎችም አካባቢዎች የሚቆጣጠሩ ታጣቂዎች መፈጠራቸዉ አይቀርም። የሚፈጠረዉ ቀዉስም እጅግ በጣም ከባድ ነው የሚሆነዉ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ በአሁኑ ሰአት ግጭቱ ከፋኖ አንጻር በጦርነት ከሚቋጭ በድርድር ቢቋጭ ይሻላል የሚያስብሉ ምክንያት ምንድነው ?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ በተለይ መረጃ በበቂ ሁኔታ እየተሰራጨ ባለመሆኑ የተደበቀዉ የክልሉ ሕዝብ መከራ ስለሚራዘም ጦርነቱን መቀጠሉ አይመከርም። ደግሞ የአማራ ክልል ሊህቃን በኢትዮጵያዊነት እራሳቸዉን ስለሚገልጹ ኢትዮጵያን ለማዳን እዋጋለሁ የሚለዉ የፈደራል መንግስት የክልሉን ልህቃን ድጋፍ ሙሉ በሙሉ ሊያጣ አይችልም።
ሌላዉ ደግም ፋኖ በሌሎች ክልሎች ትርጉም ያለዉ ደጋፊ የማግኘት እድሉ እጅግ በጣም ጠባብ ነው። እናም ለፋኖ የሚሻለዉ በጋራ መደራጀትና መደራደር ነው። በአሁኑ ሰዓት በሐገሪቷ ከፋኖም ሆነ ከፈደራል መንግሥት ጋር ከፍተኛ ልዩነት ያላቸዉ አድፋጭ ኃይሎች ብዙ ናቸዉና ኢትዮጵያን ለመቆጣጠር የፈደራል መንግስቱን ማሸነፍ በቂ ነው ብሎ ማሰብ ቂልነት ነው።
እነኝህ ኃይሎች ከጦርነቱ ኪሳራ እንጂ የምናገኘዉ ትርፍ የለም ብለዉ ስለሚያስቡ መገመት እንደምንችለዉ ከሁለቱ ዉጪ የሚገኙ ኃይሎች ግምባር ሊፈጥሩ ይችላሉ። እናም ከፋኖ በፊት ከፈደራሉ መንግስት ጋር የተጣሉ የፖለቲካ ኃይሎች ብዙ ናቸዉና ፋኖም ብዙ ባያካብድና ካለኔ ከፈደራል መንግስቱ የሚገዳደር የለም ባይል ይመከራል። እኔ ፋኖ ተሰማራ ሳይሆን ፋኖ ተደራደር እላለሁ!!!! ድርድር አይቀሬ ስለሆነ አሁኑኑ ቢካሄድ ደግሞ ብዙ ወንድምና እህቶቻችንን እናተርፋለን።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ ምናልባት ከፈደራል መንግስቱስ በኩል ጦርነቱ እንዲራዘም የሚያደርጉ ጉድለቶች አይኖሩም?
✅ ማሪንዶስ ጦና፦ ይኖራል። በደምብ እንጂ። ለምሳሌ በመከላከያ የሚፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በአጣም አደገኛ ናቸዉ። እኔ አርፌ ብቀመጥም እኔ፣ ቤተሰቤ፣ ሕዝቤ ይገደላል። ስለዚህ መታገል አለብኝ የሚሉ ሐቀኛ ኃይሎች ወደ ትግል እንዲገቡ ያደርጋል።
በተቀረዉ ኢትዮጵያ በአማራ ሕዝብ ላይ የሚደረግ ሕገወጥ ጫና ካለም አስቸጋሪ ነው። ወደ ጦርነቱ የሚቀላቀሉ ሰዎችን ቁጥር ይጨምራል። ሌላዉ መንግስት ሕገመንግስት የሚያከብር የሰላም ስምምነት ለመፈራረም ዝግጁ መሆኑን ደጋግሞ ማሳወቅ አለበት።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ እንደወትሮው ሁሉ ፈቃደኝነት አሳይተው በተነሱ ጉዳዮች ላይ ዝርዝር ማብራሪያና ትንታኔ ስለሰጡን በሚዲያችን እንዲሁም በውድ ተከታዮቻችን ስም እናመሰግናለን።
✅ ፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና፦ እኔም አመሰግናለሁ።
🎙💻 ዎላይታ ታይምስ፦ መልካም። ዳግም በሌላ ጉዳይ እንደምንገናኝ ተስፋ እናደርጋለን።
ማሳሰቢያ ለአንባቢያን፦ የዎላይታ ታይምስ ሚዲያ በዚሁ የፖለቲካ ወጌሻ እንግዳ ዝግጅት ላይ ጠለቅ ያለ ልምድና ክህሎት ካለው ፖለቲካ ጉዳዮች ተንታኝ በፕሮፌሰር ማሪንዶስ ጦና ( የብዕር ስም ) ያቀረበ ሲሆን ከዚህ በፊትም በተለያዩ ትኩረት በሚሹ ጉዳዮች እንዳቀረበ የሚታወስ ነው። በቀጣይም በሌሎች ጉዳዮች እንደምንመለስ በአክብሮት እንገልፃለን።
WolaitaTimes , በህብረተሰብ ውስጥ🙏 እናመሰግናለን🙏 #Ethiopia #Tigray #Amhara #Oromia
በናትናኤል ጌቾ ተዘጋጅቶ የቀረበ ዘገባ